Tuesday, June 09, 2015

ኢትዮጵያ አይሲቲን በበለጠ ለመጠቀም የሚያስችላት ደረጃ ላይ ደርሳለች

(ግንቦት 30/2007, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እያስገኘ ያለውን ፋይዳ በበለጠ መጠቀም የሚያስችላት ደረጃ ላይ መድረሷን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።




በአገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መንደር ወይም ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ድብረጽዮን ገብረሚካኤል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  “አገሪቱ  ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖሊቲካዊ፣ ማህበራዊ ፋይዳዎችን በመገንዘብ በበለጠ መጠቀም መቻሏን ማየት የተጀመረበት ደረጃ ላይ ደርሳለች”። ዜጎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች በስራ ላይ ውለዋል ነው ያሉት።

ከ270 በላይ የተለያዩ ኢንፎርሜሽናልና ትራንዛክሽናል አገልግሎቶች መልማታቸውንም በተመሳሳይ ጠቅሰዋል። ቴክኖሎጂ ፓርኩ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጎልብቶ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ  እንዲሆን ለማድረግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ተስማሚና ምቹ የሆነ ስፍራ እንዲሆን ለማድረግና በዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ፓርኩ በቦሌ ለሚ ማረፉም ለንግዱ ማህበረሰብ፣ ለዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ቅርብ በመሆኑ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይልና የምርምር ስራዎች በስፋት ለማግኘት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት። ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በመሆኑም አመቺ የንግድ እንቅስቃሴ በመፍጠር በኤክስፖርት ለሚሰማሩ ድርጅቶች በቀላሉ ምርቶቻቸውን ለማንቀሳቀስ እንደሚረዳም እንዲሁ።

የአገር ውስጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ኩባንያዎችና ምርምር ተቋማት የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ኩባንያዎቹ አረንጓዴ ኃይልን እንዲጠቀሙ እንደሚደረግም ጠቁመዋል ሚኒስትሩ። ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፓርኩ የሕንድን ተሞክሮ በመቀመር የተገነባ መሆኑንም ነው ያወሱት። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት ፓርኩ አገሪቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መደረሻ  ለማድረግ ይጠቅማል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ተገንብተው በተጠናቀቁ ህንጻዎች ላይ ከተመዘገቡት 20 ኩባንያዎች ውስጥ ውስጥ ከ15 በላይ የሚሆኑት የአገር ውስጥ  ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ናቸው ነው ያሉት።

ከዚህ ባሻገር አቅሙ ላላቸውና አስፈላጊ መስፈርቶችን ላሟሉ ለሶስት አገር በቀል ድርጅቶችና ለአራት የውጭ ድርጅቶች በፓርኩ ውስጥ ቦታ እንዲሰጣቸው ተደርጓል። በፓርኩ ውስጥ ገብተው ለሚሰሩ ኩባንያዎችም  ፈጣን  የብሮድባንድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የፋይበር ኬብል ዝርጋታ መከናወኑን ተናግረዋል። 

በ200 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ፓርኩ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትና ልማት ላይ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች የሚሰሩበት የቢዝነስ ዞንና በዘርፉ የማኑፋክቸሪንግና የመገጣጠሚያ ድርጅቶች የሚሰሩበት የመገጣጠሚያና የማከማቻ ዞንን ያከተተ ነው።

በተጨማሪም ለፓርኩ ማህበረሰብ የሚያስፈልጉ ማህበራዊ መሰረተ ልማቶች የሚገኙበት የንግድ ዞንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዙ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምርምርና ስርፀት የሚካሂዱ ድርጅቶችና ለስልጠና ማዕከላት መስሪያ የዕውቀት ዞን በውስጡ ይዟል።

በፓርኩ የአዋጭነት ጥናት መሰረት ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር በተለይ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ በሚሰራበት ቦታ ላይ ሚኒስትሩ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት   

No comments:

Post a Comment