Saturday, June 06, 2015

በመርካቶ ሸራ ተራ የእሳት አደጋ ደረሰ

(ሰኔ 3, 2007  , (አዲስ አበባ))--በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ገበያ በተለምዶ ሸራ ተራ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ዛሬ ከሰዓት የእሳት ቃጠሎ ደረሰ። የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ሦስት ሰዓት የፈጀ የመከላከል ሥራ በመሥራት ቃጠሎውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ገልጿል።



የባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት የተፈጠረው የእሳት አደጋ ሰፊ በመሆኑ የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። አደጋው የደረሰበት ቦታ ፈጣን ተቀጣጣይ የሚባሉት እንደ ፕላስቲክ ውጤቶች፣ ብርድ ልብስ፣ ዘይትና ሌሎች ሸቀጦች በመኖራቸው አደጋውን ለመቆጣጠር ረጅም ሰዓት መውሰዱን ነው የተናገሩት።

በአካባቢው የሚገኙት ቤቶች ተቀራርበው መሰራታቸውና ለአደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎች አመቺ ባለመሆናቸው አደጋውን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገውን ጥረት ፈታኝ እንዳደረገው ገልጸዋል።

እሳቱን ለማጥፋት የሁሉም ክፍለ ከተሞች የእሳት አደጋ ቅርንጫፍ የእሳት መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችና አራት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉት ከፍተኛ ውኃ የመርጨት አቅም ያላቸው ቦታዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። የአደጋው መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስም የአደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment