Friday, April 17, 2015

«በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት አፍሪካውያን በጋራ ሊቆሙ ይገባል» - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

(ሚያዚያ 9/2007, (አዲስ አበባ))--በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት አፍሪካውያን በጋራ መቆም እንደሚገባ ቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከሩዋንዳው ፕሬዚ ዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በአዲስ አበባ ከመከሩ በኋላ እንደተናገሩት፤ በደቡብ አፍሪካ ለተከሰተው ድንገተኛ ችግር መላው አፍሪካውያን በጋራ በመቆም ሊፈቱት ይገባል።ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ አፍሪካ ባለው ችግር ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ዜጎች ላይ ሰሞኑን የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ሁሉም አፍሪካውያን ለደቡብ አፍሪካ ነፃ መውጣት አስተዋፅኦ አበርክተዋል። የተፈጠረውን ድንገተኛ ክስተት ለመግታትም ሁሉም አፍሪካውያን መተባበር አለባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በደቡብ አፍሪካ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በኢትዮጵያውያንና በሌሎች አገራት ዜጎች ላይ የተፈጠረውን ችግር የአገሩ መንግሥት በፍጥነት እንደሚገታው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በደቡብ አፍሪካ ደርባን አካባቢ በሚገኙ በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ ጥላቻን በሚያራምዱ ጥቂት የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ዜጎች ላይ እያደረሱ ካለው ኢሰብአዊ ጥቃት ኢትዮጵያ ውያንን ለመከላከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል እና የኤምባሲው ሰራተኞች ሁኔታውን በቅርበት ለመረዳት እንዲሁም ከአካባቢው አስተዳደር እንዲሁም በስፍራው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር ለመነጋገር ከሚያዚያ 1ቀን2007 ዓ.ም ጀምሮ ጥቃቱ ወደ ተፈፀመበት ደርባን ተጉዘዋል።

አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል የጥቃቱ ኢላማ ከሆኑት ሀገራት የሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ኮንጎ፣ዚምባቡዌ፣ሌሴቶ፣ባንግላዲሽ እና ፓኪስታን አምባሳደሮች ጋር በመሆን የስደተኞችን ጉዳይ ከሚከታተለው የደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጋር በመገናኘት ምክክር ማድረጋቸውንም ጠቅሷል ።

በውይይቱም የደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ጥቃት ይፈጸምባቸዋል በተባሉ ቦታዎች የጸጥታ ኃይሉን ከማጠናከር ጀምሮ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አረጋግጠዋል። በጥቃቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን መታሰራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ በቀጣይም ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረቡ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲው ዲፕሎማቶች በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ የኮሚኒቲ አባላት ጋር በመሆን ዜጎችን ከጥቃት ለመታደግ ደርባን የሚገኙ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በደርባን አካባቢ የዙሉ ጎሳ ንጉስ ከሆኑት ንጉስ ጉድዊል ዚዌልቲኒ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አመልክቷል። ውይይቱን ተከትሎም ንጉሱ በዙሉ ቋንቋ በሚተላለፍ የሬድዮ ፕሮግራም ድርጊቱን በማውገዝ የኮነኑ ሲሆን ደቡበ አፍሪካውያን ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በመከባበር እና በመቻቻል እንዲኖሩ ጥሪ ማቅረባቸው ገልጿል።

ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም ሁኔታዎች እየተረጋጉ መምጣታቸውን እና መሻሻሎች መኖራቸውን ገልፀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመታደግ ጥረቱ የሚቀጥል መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመልክቷል። የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት፤ በደርባንና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመደራጀትና በመሰባሰብ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል።

ደቡብ አፍሪካውያን በችግራቸው ጊዜ በሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት ሲጠለሉ እንደነበር በማስታወስ የሀገሬው መንግሥትና ህዝቡ ይህንን የማስገንዘብ ሥራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነው ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ለደቡብ አፍሪካውያን ነፃነት አፍሪካውያን እጃቸው እንዳለበት በማስገንዘብ በኩል ባህላዊ አመራሩና መንግሥት በስፋት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በየዓመቱ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን በህገወጥ ደላሎች ግፊት በኬኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ሲሆን፤ደቡብ አፍሪካ የሚደርሱት ከብዙ እንግልት እና ስቃይ በኋላ ነው።ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረጉ አደገኛ እና ህገወጥ ጉዞዎች ወቅት በደርዘን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኮንቴነር ታፍነው መሞታቸውም ይታወሳል።በሚያቋርጧቸው አገራት በፀጥታ ሀይሎች በመያዝም ለእስራት የተዳረጉት እንዲሁ በመቶ የሚቆጠሩ ናቸው።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment