Thursday, January 22, 2015

የባቡር ትራንስፖርት ዳግም ትንሳኤ

(ጥር 14/2007, (አዲስ አበባ))-- የባቡር ትራንስፖርት የሰው ልጆች የመጓጓዣ አማራጭ መሆን የጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ (እ.ኤ.አ 1820) በእንግሊዘ አገር ነበር። ይህ የትራንስፖርት አማራጭ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ደግሞ በርካታ የዘመናዊነት መገለጫዎች መኪና፣ ስልክ፣ ቴሌግራፍና ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ማለትም በ20ኛው ከፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነበር።

በወቅቱ በፈረንሳዮች አጋዥነት የባቡር ሀዲዱ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ከዛም ጅቡቲ ወደብ የሚያደርስ ነበር። ይህም 780 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው 680 ኪሎ ሜትሩ የኢትዮጵያን ግዛት ያካለለ ሲሆን ቀሪው 100 ኪሎ ሜትር የጅቡቲን ግዛት ይይዝ ነበር።

ኢትዮጵያም ከዚህ የባቡር ሀዲድ ውጪ ምንም አይነት የባቡር መስመር አልነበራትም። በዚህም የባቡር ትራንስፖርት በምስራቅ የአገሪቷ ክፍል ብቻ ተወስኖ ቆይቶ ነበር። ድሬዳዋ ወይም ጅቡቲ የማይሄድ ሰውና ዕቃ ባቡርን አማራጩ አያደርግም ነበር። ይህም የባቡር ሀዲድ በቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴና በደርግ ዘመነ መንግስት ምንም መሻሻል ወይም እድሳት ሳይደረግለት ከጂቡቲ ድሬዳዋ ልብሶችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ብቻ ሲያጓጉዝ ከቆየ በኋላ ጭራሽ ቆሞ ነበር።

አሁን ታዲያ ያ ሁሉ ቁጭት የወለደው እንቅስ ቃሴና ኢትዮጵያ ያለችበት አካሄድ በአየርና በመኪና ብቻ ተጓጉዞ የሚደረስ አለመሆኑ ታምኖበት ባቡርን ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ በየፊናው እየገነባች ትገኛለች። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ባቡርን እንደ አንድ የትራንስፖርት አማራጯ ብቻ ሳይሆን እንደዋነኛ የመጓጓዣ ስልት ልታደርግ እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች፤ ወደ ተግባርም ገብታለች።

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻለችና አየር መንገዷም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የወሰደ አስተማማኝ የመጓጓዣ ስልት ሆኗል። ወደ ግብጽ ካይሮ ዓለምአቀፍ በረራ የጀመረው የያኔው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ በርካታ የዓለም ክፍልን እያካለለ እየተወደደም ነው።

በዚህም የዓለም ህዝብ ሁሉ ምርጫውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርማ ያለውን የኢትዮጵያን አየር መንገድ እየመረጠ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ከአገር ገጽታ ግንባታዋ ባለፈም የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ዘርፍ ሆኗል። ይህ ታዲያ በምድር ትራንስፖርትም ሊደገም ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በቅዲሚያ ግን የወጪና ገቢን ንግድ በር የሆነውን የምስራቁ ክፍል ቅድሚያውን አግኝቷል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ከምታራምደው አረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር የሚጣጣምና የአየር ብክለትን የማያስከትል፣ለሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር በቴክኖሎጂና በዕውቀት ሽግግር ረገድ ጠቀሜታ እንዲኖረው ብሎም ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ምዕራብ አፍሪካ የተዘረጋው የምድር ባቡር መረብ አካል በመሆን ከሌሎች አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የ756 ኪሎ ሜትር የባቡር ፕሮጀክት ተነድፏል። የዚህ ፕሮጀክት 4ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን 70 በመቶ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር ፣ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈናል። ስራውም በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን የመንግስት አካላትና የባቡር መሀንዲሶች እየተናገሩ ናቸው።

የባቡር ፕሮጀክቶቹ እንቅስቃሴ በከፊል
ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የ756 ኪሎ ሜትር የባቡር ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ሰበታ መኢሶ እስከ ደወሌ ድረስ ብሎም እስከ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ /ሰበታ- አዳማ- መኢሶ-ድሬዳዋ- ደወሌ ድረስ 656 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ከደወሌ እስከ ጂቡቲ ወደብ ደግሞ 100 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሆናል። ደወሌ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ድንበር መሆኑን ልብ ይሏል።

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ስር ካሉት የባቡር ፕሮጀክቶች አንዱ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ነው። ከኒውዮርክና /አሜሪካ /ብራሰልስ /ቤልጄም/ ቀጥሎ ሦስተኛዋ የዲፕሎማቶች መዳረሻ የሆነችው የአፍሪካና የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ እንደ ጓደኞቿ ሁሉ የባቡር መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልጋት አያጠያያቂ አለመሆኑን ተከትሎ የከተማ ውስጥ ቀላል ባቡር ስራው ተጀምሮ አገልግሎት ሊሰጥ በማጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ናቸው።

ወደ 4 ሚሊዮን የሚሆን ነዋሪ ያላት የአፍሪካና የመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት አገር ከተማዋ አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ በትራንስፖርት ምክንያት እጅግ ሲማረሩ ማስተዋል የተለመደ ነው። ነዋሪዎቹ ከምሬታቸውም አልፎ በስራቸውም ላይ ተጽዕኖው ከባድ ነበር፤ አሁንም አለ። ግን በቅርቡ ዘመናዊው የከተማ ውስጥ ባቡር የነዋሪዎችን ችግር ለመፍታት በር እያንኳኳ ነው።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ የባቡር ስራ ሊጠናቀቅ ብዙ አልቀረውም። ከዚህ ባለፈም 41 ባቡሮች ለከተማው ህዝብ እንኳን ደህና መጣችሁ በሉኝ እያሉ ሲሆን 9 ባቡሮች የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያዋ አዲስ አበባን ተቀላቅለዋል፤አገር ውስጥ የገቡት ባቡሮች በአሁኑ ወቅት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ይገኛሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ ከጂቡቲ በመምጣት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

አዲስ አበባን በባቡር ማስተሳሰር ያስፈለገበት ምክንያት
አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋች መምጣቷ ግልጽ ነው። በዚህም ነዋሪዎች በታክሲ፣ በከተማ አውቶቡስ፣ በሃይገርና በሌሎች የትራንስፖርት ዘዴዎች ብቻ ከቤታቸው ወደ ሌላ የከተማዋ አካል መዘዋወር አቅቷቸዋል። አንደኛ ቀጥታ ትራንስፖርት አይገኝም፣ ሌላው መኪኖች የሚወስድባቸው ጊዜ ረጅምና አሰልቺ በመሆኑ ጊዜው ትራንስፖርት ላይ ብቻ ያልቃል። ከዚህ በላይ ደግሞ አዲስ አበባ ከዕድገቷ አንጻር ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ግድ ይላታል። ምክንያቱም ሌሎቹን ዓለም አቀፍ ተቋማት እንኳን ትተን የአፍሪካ ህብረት ብናነሳ ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ በመሆኗ ብዙ ጊዜ ጉባዔዎችና ሴሚናሮች ስለሚኖሩ ከሚኖረው የትራንስፖርት መጨናነቅ ለማዳን ባቡር አማራጭ ብቻ ሳይሆን ተመራጭም ነው። ዲፕሎማቶቹ በባቡር ባይሄዱ እንኳን የአዲስ አበባ ነዋሪ በመኪና መሄዱን ወደ ባቡር ሲቀይር መጨናነቁ ረገብ ይላል ብሎ መገመት ቀላል ይሆናል። ዋናው ጉዳይ ግን የከተማዋ የትራንስፖርት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚለው ይሆናል። ስለዚህ ባቡር የግድ እንደሚል ብዙ ማሳያዎች ቢኖሩም እነዚህ ግን በቂ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ፕሮጀክቱስ የት ደርሷል? ባቡሮቹስ?
የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ለሚሰሩ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ባዘጋጀው ጉብኝት ላይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር በሃይሉ ስንታየሁና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ተናግረዋል።

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊው አቶ ደረጀ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጥር መጨረሻ የሙከራ ስራ እንደሚጀምር ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ለሚሰሩ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገልፀዋል። ዘጠኝ ባቡሮች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት መንገድ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ቃሊቲ ያሉትንና ለአገልግሎት የተዘጋጁትን ለጋዜጠኞችና ለኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችና ሃላፊዎች አስጎብኝተዋል።

ስለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አንዳንድ ነገሮች
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ስራው የተጀመረው በአራዳ ክፍለ ከተማ ምንሊክ አደባባይ ወይም ጊዮርጊስ አካባቢ ሲሆን በቅድሚያ የተሰራውም የዋሻ ውስጥ ስራ ነው። በወቅቱ አካባቢው ለባቡር ተብሎ ሲቆፈር የትራንስፖርት ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ የነበሩ ቢሆንም ዛሬ ለተመለከተው ግን እንኳንም ያሰኛል።

በምንሊክ አደባባይ ወደ መርካቶ የሚወስደው የባቡር ስራ ሂደትም እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን መረዳት አያዳግትም። ምክንያቱም በአካባቢው የሚሰራው ስራ የውስጥ ለውስጥ ስራ ስለነበር። ታዲያ አሁን ይህ ስራ ተጠናቋል። በምንሊክ አደባባይ የተሰራው የዋሻ ውስጥ ስራ ከ650 ኪሎ ሜትር እንደሚበልጥ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር በሃይሉ ስንታየሁ ይገልፃሉ። በአዲስ አበባ የ34 ኪሎ ሜትር ቀላል ባቡር ግንባታ ውስጥ በአጠቃላይ በቂ ፌርማታዎች የሚኖሩ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር በሃይሉ፤ የአካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ ያስገባ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሊፍቶች እንደሚገጠሙ ተናግረዋል።

አንድ ባቡር በአማካኝ እስከ 317 ሰዎች ይይዛል። ጉዞውም ፈጣን ነው። ከአያት በመገናኛ መስቀል አደባባይ፣ ከመርካቶ በጦር ሃይሎችና በልደታ መስቀል አደባባይ ከዚያም ወደ ቃሊቲ የባቡር አገልግሎቱ የሚደርስባቸው ቦታዎች መሆናቸውን እንዲሁም አንዳንድ ቦታዎች ሁለት ሁለት መስመሮች ያላቸው መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ስራ ሲጀምር በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሲሆን ለዚህም ባቡሮቹ ሃይል የሚሰበስቡባቸው የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች ተገጥመዋል። ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የሚሰጡት ባቡሮች ለከተማዋ የአየር ንብረት ተብለው የተዘጋጁና ለሌሎች ቦታዎች የማያገለግሉ መሆኑን መሃንደሱ ኢንጅነር በሃይሉ ነግረውናል።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ከመቅረፉም በላይ ከተማዋ የዲፕሎማቶች መናኸሪያ በመሆኗ ሌላ ተጨማሪ መስፈርት እንድታሟላ ያደርጋታል። ከዛም በላይ በአዲስ አበባ የሚኖረው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የነዋሪዎች ብዛት ከዚህ ስለሚበልጥ ባቡሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ ይሆናል። በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋም በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን ነዋሪዎቹ በቀላሉ ካለ ትራንስፖርት መጨናነቅ ወደ ሚፈልጉበት ቦታ ለመሄድም የሚያስችላቸው ይሆናል ማለት ነው። ከሰበታ መኢሶ ያለውን እንቅስቃሴ ደግሞ በነገው እትማችን ይዘን እንቀርባለን።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment