Wednesday, January 21, 2015

«ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳው የላቀ ውጤት አስመዝግባለች» - የዓለም ባንክ

(ጥር 13/2007, (አዲስ አበባ))-- ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት ገጠርን መሠረት ባደረገ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ባከናወነቻቸው ጠንካራ ሥራዎች ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሏን የዓለም ባንክ የ2014 ሪፖርት አመለከተ፡፡

በኢትዮጵያ ድህነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ከነበረበት 44በመቶ በ2011ወደ 30በመቶ መቀነስ እንደተቻለ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ለድህነት ቅነሳው መሠረታዊ ምክንያቶች ተብለው የተጠቀሱት የግብርናው ዘርፍ እድገት እና አጠቃላይ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት የታየው እምርታ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በዚህም በዜጎች የአኗኗር ዘይቤ፣ በጤናና ትምህርት ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸው ተመልክቷል፡፡
 
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ሀገሪቷ በዓለም በድህነት አረንቋ ውስጥ ከሚገኙ አገሮች አንዷ እንደነበረች ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ከፍተኛ እድገት እና የተቀናጀ የገጠር ሴፍቲ ኔት መርሐ ግብር ለተመዘገበው ውጤት ተጠቃሾቹ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርቷል። ይህም ሀገሪቷ ባለፉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአማካይ ላስመዘገበችው የ10ነጥብ9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ እንዳበረከተም አመልክቷል፡፡ በ2000 አገሪቷ ከነበረችበት የድህነት አረንቋ ለመውጣት ባሳየችው አስገራሚ ግስጋሴ ከኡጋንዳ በስተቀር የሚስተካከላት የአፍሪካ አገር እንደሌለም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
 
በተጠቀሰው ጊዜ የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ ከፍ ማለቱንና የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካቱም በኩል በአገሪቷ ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበ ተገልጿል፡፡ ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ በተለይም ረሃብን በማጥፋት፣ የሕፃናትን ሞትን በመቀነስ፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስንና ወባን በመቆጣጠር በኩል ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
 
2000 በገጠር አካባቢዎች ከ5ሴቶች አንዷ ብቻ በእርግዝና ጊዜ የወሊድ ክትትል ታገኝ የነበረች ሲሆን፣ በ2011 ግን ይህ መሻሻል በማሳየት ከ3ሴቶች አንዷ የእርግዝና ክትትል ማግኘት ችላለች፡፡ በ1995 አንድ ሴት በአማካይ 7 ልጆች ትወልድ የነበረ ሲሆን፤ በ2011 ግን ይህ የወሊድ ምጣኔ 4ነጥብ6 ደርሷል፡፡ የሕፃናትን ሞት በመቀነስ በኩልም ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል፡፡
በተያያዘም በተጠቀሰው ጊዜ የዜጎችን የኑሮ ደረጃም በማሻሻል በኩልም በኤሌክትሪክ አቅርቦት እና በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በተጠቀሰው ጊዜ በእጥፍ መሻሻል እንደታየ ተጠቁሟል፡፡
 
በሀገሪቷ በድህነት ቅነሳ ሂደት ውስጥ ካጋጠሙ ተግዳሮቶችም በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት መስፋት አንዱ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የእህል ዋጋ መጨመር በግብርናው ዘርፍ ለተሰማራው አርሶ አደር የገቢ መሻሻል ቢያመጣም ለሸማቹ የኅብረተሰብ ክፍል ፈተና እንደሆነበት ተጠቅሷል፡፡
 
ኢንዱስትሪዎች በአስርት ዓመቱ ማብቂያ በከተሞች አካባቢ ለድህነት ቅነሳው አስተዋፅኦ እያበረከቱ ስለመሆኑም ጥቂት ማሳያዎች እንዳሉ ጠቅሶ፣ አሁንም አብዛኛው ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር ከመሆኑ አንፃር የድህነት ቅነሳ ፖሊሲው ለከተሞች እድገትና ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment