Saturday, December 27, 2014

ኢትዮጵያ የሱዳን ወደብን አማራጭ አድርጋ መጠቀም ልትጀምር ነው

(ታህሳስ, 18/2007, (አዲስ አበባ))--አትዮጵያ ለውጭ ንግድ ብቻ ስትጠቀምበት የነበረውን የሱዳን ወደብ ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ ምርቶችን ለማስገባት አማራጭ አድርጋ መጠቀም እንደምትጀምር የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታው ተናገሩ።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በተቋሙ የአምስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸምና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር ምክከር አካሂዷል። በመድረኩም ላይ እቃዎችን ወደ አገር ወሰጥ ለማስገባት እና ከአገር ወጭ ለማስወጣት የሚፈጀው ጊዜ መራዘም፣ እቃ ይዘው የሚመጡ ኮንቴነሮች ባዶቸውን ወደ ወደብ መመለሳቸው፣ የመጋዘን ችግሮች እና የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደ ችግር ተነስተዋል።

በጉዳዩ ላይ መልስ የሰጡት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታቸው መንግስቴ የተነሱት ችግሮች በአፈፃፀም አቅም ውስንነት፣ በመረጃ አያያዝ ቸግሮች የሚከሰቱ ናቸው ብለዋል። በተለይ ወደ ውጭ ከሚላከው በላይ በቁጥር ሆነ በመጠን ከፍተኛ የሆነ ምርት ወደ አገር ወሰጥ መግባታቸው ለአገልግሎቱ በሚፈለገው ልክ መስጠት እንዳይቻል በማድረግ ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

"ይህንንም በመገንዘብ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ግዴታ በመሆኑ አሁን ያሉት አማራጮችን በማገናዘብ ወደ ውጭ እቃዎቸን ለመላክ ብቻ ስንጠቀምበት የነበረውን የሱዳን ወደብ እቃዎችንም ለማስገባት መጠቀም እንድንጀምር አስገድዶናል" ብለዋል። በመጪው ጥር ወር 50 ሺህ ቶን የሚጠጋ ማዳበሪያ በሱዳን ወደብ በኩል ለሙከራ እንደሚገባ ስራውንም ለማስጀመር ከሱዳን መንግሰት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ሚኒስትር ዲኤታው ገልፀዋል።

የሱዳንን ወደብ ከዚህ በፊት እቃዎችን ለመላክ ብቻ ስንጠቀምበት ነበር ያለት ሚኒስትሩ አሁን ምርቶችን ለማስገባት አማራጭ አድርግን መጠቀማችን በማደግ ላይ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ያመጣው ፍላጎት ለማስተናገድ መሆኑን ተናግረዋል። አማራጭ ወደብ የመጠቀም እንቅስቃሴው በሱዳን ወደብ በተጨማሪ እንደ ዘይላ፣ ባርበራ እና የመሳሰሉ ወደቦችንም በአማራጭነት መጠቀም እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የመጋዘን ችግሮችን ለመቅረፍ በሞጆ አከባቢ ከ5 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የሚሆን መጋዘን ከአንድ ሳምንት በፊት አገልግሎት መስጠጥ መጀመሩን አስታውሰው በሌሎች አካባቢዎችም ተጨማሪ መጋዘኖችን በመገንባት ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሞከር ተናግረዋል።
ምንጭ:  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment