Wednesday, December 31, 2014

«በኤደን ባህረሰላጤ የሰጠመ ጀልባም፣የሞተ ኢትዮጵያዊም የለም»- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

(ታህሳስ, 22/2007, (አዲስ አበባ))-- ከሁለት ሳምንታት በፊት በኤደን ባህረሰላጤ በሰመጠው ጀልባ 70 ያህል ኢትዮጵያውያን ሞቱ ተብሎ በተለያዩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው ዘገባ ሐሰት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የዑጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካቱጋ ሙሴቬኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኤደን ባህረ ሰላጤ ምንም የሰጠመ ጀልባ እንደሌለና በኢትዮጵያውያን ላይም ምንም ዓይነት የሞት አደጋ እንዳልተከሰተ ተረጋግጧል።


 የመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አደጋውን ለማጣራት በኤደን ባህረሰላጤ ከ250 እስከ 300ኪሎ ሜትር ርቀት በአብኤል መንደር ዱባብና ሙሃ በተባሉ የባህር ጠረፎች ከየመን ጦር 17ኛ ብርጌድ ጋር በመሆን ባደረገው ፍለጋ ምንም ዓይነት ጀልባ አለመስጠሙን እንዳረጋገጠ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

የመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከየመን መከላከያ ኃይሎች የተውጣጡ ሁለት ቡድኖችን ጀልባው ሰጠመ ወደ ተባለበት አካባቢ በመላክ ባካሄዱት ፍለጋ ምንም ዓይነት አደጋ አለመድረሱ መረጋገጡን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ በዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን አስገንዝበዋል። አደጋው በተጨባጭ ያልተከሰተና በአገሪቱ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ያነጣጠረ፣ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተልዕኮ ሊሆን እንደሚችል የሚገመት መሆኑንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካቱጋ ሙሴቬኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር የተናገሩት አምባሳደር ዲና ፕሬዚዳንቱ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንና ሁለቱ አገሮች በኢነርጂ፣በትራንስፖርት፣ በከተሞች ትስስርና በጤና ዘርፍ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ዑጋንዳ በአፍሪካና በቀጣናው አገሮች የሚያጋጥመውን ድርቅ በጋራ ለመቋቋም፣ ሽብርተኝነትን፣ሐገወጥ የገንዘብ ዝውውርንና የባህር ላይ ውንብድናን በጋራ ለመመከት መስማማታቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣አገሮቹ በአፍሪካ ልማትን ለማፋጠንና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ግጭት በኢጋድ ማዕቀፍ እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በግልገል ጊቤ 3 እንዲሁም በመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጉብኝት ማድረጋቸውን አብራርተው፣ሁለቱ አገሮች በምሥራቅ አፍሪካ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ በተለይም በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የነበረው አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ከሌሎች አገሮች ጋር በመሆን ያደረገችው ጥረት መሳካቱንም አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል። የሶማሊያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲዋሊ ሼኪ አህመድ ሥልጣናቸውን በሰላም መልቀቃቸውንና ኦማር አብዲራሺድ ዓሊ ሻርማክ መሾማቸውን አመልክተው፤በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ  

Related topics:

No comments:

Post a Comment