Wednesday, October 08, 2014

ተስፋ መቁረጥ የፈጠረው የዋሽንግተን...!

(መስከረም 27/2007, (አዲስ አበባ))--የአንድን ሀገር ኤምባሲ፣ ኤምባሲውን የወከለው ሀገር ግዛት አድርጎ የመቁጠር ተለምዷዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አለ። በዚህ አግባብ ማንም አካል ያለ ኤምባሲው ፍቃድና ይሁንታ የዲፕሎማ ቲክ መብት ባለው ኤምባሲ ግቢ ውስጥ መግባትም፣ ምንም መፈፀምም አይችልም።

ከዚህ የተለመደ እምነትና አስተሳሰብ በተፃራሪ ኤምባሲዎች የወከሏቸው ሀገራት ሌላ ተቀጥላ ሀገር ወይም ግዛት መሆናቸውን የሚቃወሙ ምሁራን ደግሞ ኤምባሲዎቹም ሆኑ ዲፕሎማቶቹ ባሉበት ሀገር ህግ ሊተዳደሩ ግድ እንደሆነ፣ ህጉንም ጥሰው ከተገኙ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል በማለት ይሞግታሉ።

በ1963 የፀደቀው የቪየና ስምምነት በአንቀፅ 22 ንዑስ ቁጥር 2 ግን አንድ የሌላ ሀገር ኤምባሲ በሀገሩ እንዲኖር የፈቀደ ወይም የተቀበለ ሀገር፣ የዲፕሎማሲ ተግባር የሚከናወንበት ስፍራ ወይም ኤምባሲ በሌሎች እንዳይወረር ወይም ጉዳት እንዳይደርስበት፣ ሰላሙን የሚያውክ ጥፋትም ሆነ ሉዓላዊ ክብሩን የሚጎዳ ተግባር እንዳይ ፈፀምበት የመከላከልና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት አጥብቆ ይገልፃል።

what cause the confusion is, the general rule that diplomatic missions are inviolable. That means the receiving state's police can't enter an embassy with out the sending states consent.

በዚህ የሃሳብ መነሻነት በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተፈፀመው ጉዳይ ምንድን ነው? መንግሥታችን፣ ማለትም የኢትዮጵያ መንግሥትን ዋሽንግተን ላይ የወከለው ኤምባሲያችን ፖሊሶቹ ገብተው ህገወጦቹን ከተከበረው የዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤት (ኤምባሲያችን) እንዲያስወጡልን ጠይቀናል ወይ? ክስተቱ የትኛውን ህግ ይፃረራል? በጉዳዩ የዋሽንግተን ፖሊስና የአሜሪካ መንግሥት ተግባር ምን ያህል ህጋዊ ነው? የኢትዮጵያ መንግሥትስ ምን ማድረግ አለበት? በሚሉት አንኳር ነጥቦች ዙሪያ እየተሽከረክርን በእውነታ መልክ በቀረቡት የሃሳብ መነሻዎች ማንፀሪያነት ውሳኔ አልባ ዳሰሳ እናድርግ።

የዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤት የሆነው በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መስከረም 19/2007 ዓ.ም በጥቂት ህገወጥ ነውጠኞች ህግ የጣሰ ተግባር ወረራ ተፈፅሞበታል። የህገወጦቹ ቀዳሚ ተግባር የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ዓለም አቀፉን የቪየና ስምምነት በጣሰ ያልተገባ አቅጣጫ ማውረድና አሳንሶ ማሳየት ነበር።

በዚያው መጠን ከ15 አይበልጡም የተባሉት እነዚህ ነውጠኞች በኤምባሲው ግቢ ውስጥ ኹከት በመፈፀምና የሃይል ጥቃት እንደሚያደርሱ በመዛት የዲፕሎማቲክ ስራውን ነፃነት ተጋፍተዋል። በዲፕሎማቶቹም ላይ ጫና አሳድረዋል።

ይህንኑ ተከትሎ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲያሳስቡ ከነበሩት የኤምባሲው የዲፕሎማቲክ ሰዎች አንዱ በተለይ ትልቁ ስህተት (በህገወጦቹ ሰንደቅ ዓላማችንን አውርዶ ለመቀየር ሙከራ ሲደረግ) ሲፈፀም በያዙት ሽጉጥ አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ተኩሰዋል። ከውንብድና ተግባር ባልተለየ ያልተለመደ የህገወጥነት ተግባር የፈፀሙትን ግለሰቦች ስርዓት እንዲያሲዙ የዋሽንግተን ፖሊሶች ከስፍራው እንዲደርሱ ተጠርተዋል።

በቪየና ኮንቬንሽን መሰረት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተፈፀመው የጥቂቶች ወረራ ሉዓላዊነታችንን የሚነካ፣ የሀገራችንንም ጥቅም ጉዳት ላይ የሚጥል ነው። በዚህ ምክንያት ፖሊሶቹ ወደ ኤምባሲው የመግባታቸው የሀሳብ መነሻ ህገወጡን ድርጊት ለማስቆምና ኤምባሲው ውስጥ ገብተው ሌላ ድራማ ለመፈፀም የተዘጋጁትን ህገወጦች ማስወጣት ነው። ይህም ቢሆን የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ሰዎች ፍቃድ (consent) ሊኖር ይገባል። የፖሊሶቹ ተግባር በዲፕሎማቲክ ሰዎች ፍቃድ የተፈፀመ በመሆኑ ተገቢ ነው።

ይሁንና ወረራው ወንጀል ነው። የጉዳዩ የወንጀልነት መነሻ የቪየና ኮንቬንሽን መጣሱ ብቻ ሳይሆን ሕጉን የተቀበለችው አሜሪካ የስምምነቱን አንቀፅ የራሷ ህግ አድርጋ በመቀበሏ በህገወጦቹ የአሜሪካ ህግ ተጥሷል ብሎ መደምደምም ይቻላል።

አሁንም የአሜሪካ መንግስት ይህን ህገ ወጥነት እያጣራው መሆኑ እየተገለፀ ነው። በማጣራቱ ሂደት ወደ ኤምባሲው ገብተዋል ተብለው በተጠረጠሩና ማስረጃም በቀረበባቸው ሰዎች ላይ ይህ አይነት ርምጃ ተወሰደ ተብሎ ከመገለፁ በፊት ግን የዲፕሎማቲክ መብት ያለው፣ የኢትዮጵያን ህዝቦች ሰንደቅ ዓላማ ለማሳነስና ኢትዮጵያዊነትን ለማዋረድ የሞከሩትን ሀይሎች ከድርጊታቸው ያለዘበው ሰው በአሜሪካ መንግስት ግፊት (ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ስለ ጉዳዩ ባይገልፅም) ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደርጓል እየተባለ እየተነገረ ነው።

በቪየናው ስምምነት መሰረት የዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን አንድ ዲፕሎማትም ያለመከሰስና ያለመታሰር የማይገሰስ መብት አለው። በዚሁ መሰረት በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሽጉጥ ተኩሷል የተባለው ዲፕሎማት ሊታሰር ወይም በቁጥጥር ስር ሊውል አይችልም። በህጉ መሰረት ይህም አልተፈፀመበትም።

ምናልባትም ከአሜሪካ ህግ አኳያ የመታሰርና ያለመታሰር፣ የመጠየቅና ያለመጠየቁ ጉዳይ ሊነሳ የሚችለው መሳሪያውን በህጋዊ መንገድ ታጥቋል ወይስ አልታጠቀም፣ በሰዎች ደህንነት ላይ አደጋ አድርሷል ወይስ አላደረሰም ከሚለው አንፃር ሊሆን ይችላል። ይህም ቢሆን ግለሰቡ የዲፕሎማቲክ መብት ያለው በመሆኑ ለመከሰስና ለመጠየቅ መብቱ መነሳት ይኖርበታል።

ያም ሆኖ የዲፕሎማቲክ መብት ያለው ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች፣ በሌላ አነጋገርም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ልዩ መታወቂያና መከበሪያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ለመጠበቅ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ ወስኗል፣ ፈፅሟልም። ይህን ጨምሮ በማንም ላይ ጉዳት አላደረሰም።

በአንፃሩ ህገወጦቹ በሀገራችን ሉዓላዊ ጥቅም ላይ ጉዳትን ፈፅመዋል። የዓላማቸው መነሻና መደረሻ ድንገተኛ ስህተት ሳይሆን ጥፋትን ዒላማ ያደረገ የታቀደ ሀገወጥነት ነው። ወንጀለኞቹ ጥፋቱን የፈፀሙት ሆን ብለውና ተዘጋጅተው ለመሆኑ ማረጋገጫው የፀረ ማንነትና የፀረ ኢትዮጵያዊነት አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሀገራችን ህዝቦች ያልሆነ ሌላ ባንዲራ መያዛቸውና በግዳጅ ሊቀይሩ መሞከራቸውም ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ ልናየው የሚገባው ሌላው ጉዳይ የህገወጦቹን ያልተቋረጠ የመበጥበጥ አባዜና የህገወጥነት ዝግጅት ነው። እንደ ግንቦት 7 ያሉ የሽብር ቡድኖች በተለይ የዴሞክራሲ መናኸሪያ ነኝ በምትለው አሜሪካ የኢትዮጵያን ጥቅሞች ባልሰለጠነና በወራዳነት በሚያስቆጥር ረብ የለሽ ፍላጎት ሲተናኮሉ ይስተዋላል። ይህንኑ እንደማያቋርጡም በአደባባይ ሲገልፁ ይደመጣል። ይህን እውነታ የአሜሪካ መንግስትም ጭምር ጠንቅቆ ያውቀዋል።

በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ እድገት ባለፈ በሌሎች ጉዳዮችም ጭምር የአሜሪካ ሁነኛ አጋር መሆኗ እየጠነከረ መምጣቱን በአደባባይ በገለፁበት በዚህ ሰሞን፤ የአሸባሪዎቹ የረጅም ጊዜ ጥረትና ፍላጎት ላይ ይኸው የኦባማ ንግግር ክፉ ጥላ ስላጠላ አሸባሪዎቹ የተስፋ መቁረጣቸውን የመጨረሻ መፍጨርጨር ኤምባሲያችንን በመውረር አሳይተዋል። ድርጊታቸው ይህ ብቻ ነበር ብሎ መውሰድ ግን አይቻልም።

እነዚሁ ቡድኖች በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገርን በልማት መለወጥ ባይችሉም እንደ ሻዕቢያ ባሉ የቡድን አሰማሪዎቻቸው በየሀገሩ ኡኡ ብለው መረበሽ፣ ተሳድበውና አዋርደው ማሸማቀቅ፣ ስም አጥፍተው መታወቅን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገዋል። የኤምባሲ ላይ ወረራቸው አዲስና ለየት ያለ ቢሆንም የጥፋት እንቅስ ቃሴያቸው ባህሪውን ያልለወጠና የነበረ ነው። ከዚህም አንፃር በተለይ የአሜሪካ መንግስት ድርጊታቸውን ጠንቅቆ ያውቃል ብሎ መናገር ይቻላል።

ይህ እየታወቀ በመረጃ አሰሳና ግኝት ብዙም የማይታማው የአሜሪካ መንግስት እንዲህ አይነት ሀገወጥነት በሚበዛባቸው ግዛቶች ያሉ ኤምባሲዎቻችንና የዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤቶችን የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪ ከሚላቸው ወገኖች መጠበቅ ለምን ተሳነው ብለን መጠየቅ እንችላለን።

በቪየና ኮንቬንሽን መሰረት የዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች የአሸባሪዎች ወይም የህገወጦች ሰለባ ይሆናሉ ተብሎ ከተሰጋ ባሉበት ሀገር መንግስት የተለየ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። እንዲህ አይነቶቹ ጥበቃዎች በእኛ ሀገር ያለውን ጨምሮ በየሀገሩ ላሉ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የሚደረግ መሆኑንም ልብ ማለት ይገባል። ከዚህም አንፃር ችግሩ እየታወቀ ቀድሞውኑ የአሜሪካ መንግስት ለምን የተለየ ትኩረት አልሰጠም ብለን መጠየቅ እንችላለን።

ሌላው ጉዳይ በዴሞክራሲ መብት ስም፣ ህግና ዓለም አቀፍ ስምምነት እየጣሱ በየኤምባሲው ወረራ የሚፈፅሙ ህገወጦች ጉዳያቸው በቀላሉ መታየት የሌለበት መሆኑን የመገንዘቡ ጉዳይ ነው። ይህ የወረራ ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ከመዘጋጀት ተለይቶ እንደማይታይ ብዙዎች ሊያምኑ ይችላሉ።

ነገ ይህ አይነቱ ተግባር በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ኤምባሲዎችም ላይ አጉል አስተምህሮ ሆኖ ለአሸባሪዎች ሌላ የጥቃት መላ እንዳይሆን ማሰብን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያስተውለው ይገባል። የሽብር ጉዳይ ሲታሰብ የሽብር ጥቃት በአሜሪካ መንትያ ህንፃዎች ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ኢትዮጵያ የአሸባሪዎች ስጋት እያየለ መምጣቱን በመግለፅና ዓለም ቀድሞ ዝግጅት እንዲያደርግ በማሳሰብ ቀዳሚ እንደነበረች አይዘነጋም፤ የኋላ ኋላ እሷ ያነሳችው ሀሳብ የዓለም የጋራ አጀንዳ መሆኑ እውን ቢሆንም።

አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ የሚመስለው የእነ ግንቦት 7 ግራ የገባው ብዥታ ሌላ የሽብር ማቀነባበሪያ ዘዴ ሆኖ እንዳይወጣ ሳይቃጠል በቅጠል ማለቱ ተገቢ ነው።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment