Monday, October 06, 2014

የጽንፈኛ ዲያስፖራ ፖለቲካ

(መስከረም 26/2007, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ አዛውንት የፖለቲካ ሰዎች የአንድ ዘመን ሰዎች ስለሆኑ ወይም ከግራ አስተሳሰብ ስለተቀዱ ላለመስማማት የተስማሙ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ይስተዋላል። በእርግጥ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከትምህርት ቤት ጀምሮ የመተዋወቅ ዕድል ገጥሟቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የፅንፈኞች የፖለቲካ ቅኝት ግን ከዚሁ ታሪክ ጋር ግንኙነት የለውም።

ፅንፈኞች ባለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ የትግል ሜዳዎች ቆስለውና ተላልጠው ተሸንፈው ቂምና ቁርሾ ቋጥረው የተሰደዱ ወገኖች ናቸው። በደርግ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በአገር ቤት የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው ቢሆንም ድርጅቶቹ ተሸንፈው ሲፈርሱ አባላቱ በወቅቱ ሲያራምዱት የነበረውን አስተሳሰብ ትተው ነገሮችን ከቂምና ከታሪክ አንፃር ብቻ ማየት ጀምረዋል፡፡

በደርግ ዘመን ካድሬዎች ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ወገኖች በእርግጥ ተሸንፈዋል፡፡ ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ የደርግ የጦር መኮንኖች ቂም ይዘው ተሰደዋል፡፡ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የደርግ የኪነት ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ በአጠቃላይ የሥርዓቱ የርዕዮተ ዓለም ጠበቆች የቂም በቀል ፖለቲካ አርግዘው ተሰደዋል።

የፅንፈኞች ፖለቲካ በቂምና በጥላቻ የታጀበ በመሆኑ ለሠላማዊ ፖለቲካና ለሰጥቶ መቀበል የተዘጋጀ አይደለም። መንግሥት ለተቃዋሚ ሁሉ ግማሽ መንገድ ተጉዞ ለማስተናገድ ጥሪ ሲያቀርብ ፅንፈኞች ግማሽ መንገድ ርቀው ይሸሻሉ። የእነዚህ ወገኖች ፍላጎት አሁንም ማሸነፍ እንጂ በዴ ሞክራሲያዊ መርህ መሸናነፍን አይደለም። «ጅብ በማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ»እንዲሉ ፅንፈኞች ዴሞክራት ነን እስከማለት የሄዱበት ሁኔታ እያየን ነው።

ዛሬ ፅንፈኞች በሚቆጣጠሩት መገናኛ ብዙኃን በኩል ተሰምቶ የማያውቅ ዘረኝነትና ጥላቻ እየተሰበከ ነው፡፡እነዚህ ወገኖች ይህን የሚያደርጉት «ለኢትዮጵያ አንድነት» ብለን ነው ይሉናል። የኢትዮጵያ አንድነት ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ የሆነ አስተምህሮን ይጠይቃል። ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገል ወገን ሥነ ምግባር ያስፈልገዋል፡፡ በአንድ ብሔር ላይ ጥላቻ የሚሰብክ ቡድን የአንድነት ኃይል ሊሆን አይችልም። አንድን ሃይማኖት ከሌላው እንዲጋጭ የሰበከ ቡድን በምን ዓይነት ሁኔታ የአንድነት ኃይል ተብሎ ሊገመት ይችላል? የአንድነት ኃይል ማለት ከዴሞክራሲዊ አንድነት ውጪ ማሰብ ይቻል ይሆን? ይህ ሊሆን አይችልም።

ፅንፈኛው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ግትር አቋም የሚያራምደው «የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው»እንደሚባለው በየትኛውም መንገድ ሥልጣን ላይ ልውጣ ከሚል አስተሳሰብ ብቻ በመነሳትም አይደለም። በአገር ቤት ዴሞክራሲ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር የተስፋ መቁረጥ ጨለምተኝነት ስለተጫነው ብቻም አይደለም።

ፅንፈኛው በሁሉም ዓይነት በሽታዎች የተተበተበ መድኃኒት የለሽ፣ ሠላም ዴሞክራሲና ልማት የሚባሉ ሥነ-ሐሳቦችን ለማድመጥ አቅም የጎደለው፣ ለሠላማዊ ፖለቲካ ያልተዘጋጀ፣ በነውጥ ወይም በትጥቅ ትግል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የተዘጋጀ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካም በሁለት ጫፎች የተወጠረ (polarized) እንዲሆን በሁለቱም ጫፎች መካከል ያለውን ሰፊ ሥፍራ ለመርገጥ ፈቃደኝነት የጎደለው ወገን በመሆኑ ነው።

በፅንፈኛው ዲያስፖራ የፖለቲካ ሰዎች የተመራ የፖለቲካ ቡድን በአገር ቤት በተካሄዱት ለውጦች እዚህ ግባ የሚባል አዎንታዊ አስተዋፅኦ አልነበረውም፡፡ የፅንፈኛው ዲያስፖራ ጫና ያለበት አገር በቀል የፖለቲካ ቡድንም ውሎ አድሮ በፅንፈኛው ዲያስፖራው የፖለቲካ ፍላጎት መነዳቱ አይቀርም። የፖለቲካ ስብስቦቹ ከሕዝብ የተነጠሉ ስለሆኑ የጥቂት ልሂቃን ጊዜ ማሳለፊያ ከመሆን አያልፉም።

ፅንፈኛው ዲያስፖራም ቢሆን እንደ ሌላው ዲያስፖራ በአገር ቤት ፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ህይወት አወንታዊና ንቁ ተሳትፎ ቢያደርግ ተገቢ ቢሆንም፤በአንፃሩ ግን ከአቅሙ በላይ የሆነውን ፖለቲካ ለመምራት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ይጥራል።ነገር ግን በኢኮኖሚውና በልማት ቢሳተፍ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ይህንን ግን ሲያደርግ አይታይም፤ለማደናቀፍ ግን ላይ ታች ሲል ይስተዋላል።

በፖለቲካ ሂደት ያለው ተሳትፎ በአገራዊ አጀንዳዎች ለሠላምና ለዴሞክራሲ ለዘላቂ ልማት ድጋፉን ቢሰጥ የተሻለ መግባባት ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ ውጪ በፖለቲካው ዘርፍ ለመሳተፍ የሚፈልግ ወገን ግን ኑሮውን በውጭ እስከቀጠለ ድረስ የፖለቲካ አመራር ለመስጠት ባይቃጣው ይመከራል።

ዲያስፖራ ከአገሩ ጋር ያለውን ጤነኛ ግንኙነት ከፅንፈኞች ጠብቆ የራሱን ማህበራዊ ካፒታል ለማስፋትና ለማጠናከር የተወሰኑ መሠረታዊ የህይወት መርሆዎች ያስፈልጉታል። ከሌሎች የዲያስፖራ ወገኖች ታሪክና ልምድ ለመማር ፈቃደኛ መሆን ይጠይቃል፡፡ ከአገር ቤት ጋር ያለውን ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ግንኙነትም ይጠናከር ዘንድ የኢትዮጵያዊነት እሴት እየተጠናከረ መሄድ መቻል አለበት።

ይህ ይሳካ ዘንድ የተወሰኑ የጋራ የሥነ ምግባር እሴቶች መከተል የግድ ይለናል። ኢትዮጵያዊነት በየወቅቱ እየታደሰ የሚሄድ ነው። በአንድ ወቅት የነበረ ገዥ እሴት እየተሸረሸረ በአዲስ መተካቱም አይቀሬ ነው። አዲሲቷን እና የነገዋን ኢትዮጵያን ግን ከዴሞክራሲያዊ እኩልነት ውጭ ማሰብ አይቻልም። ዘመኑ ተቀይሯል።

ፅንፈኛው ዲያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለው ግንኙነት በፖለቲካዊ ፓርቲዎች አማካይነት መግለፅ አይገባውም። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ቢሆንም ኑሯቸው በውጭ እስከቀጠለ ድረስ ንቁ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊ ሊሆኑ ስለማይችሉ የሚሰጡት ድጋፍ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በተለይ በልማት ዙሪያ ያነጣጠረ ቢሆን ይመረጣል።

በአገራችን ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በመቻቻልና በእኩልነት መርሆዎች ላይ እንዲሆን ብዙ ገድሎች ተካሂደዋል። በዲያስፖራው ውስጥ የሚገኙ ፅንፈኛው ወገኖችም ቢሆኑ እነዚህ እሴቶች የአገራችን የፖለቲካ ባህል እንዲሆኑ ድጋፍ መስጠት አለባቸው። ከዴሞክራሲያዊ እኩልነትና ከመቻቻል ውጪ ኢትዮጵያን ማሰብ እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል።

አገራችን ላለፉት ጥቂት ዓመታት ፋታ በማግኘቷ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ስለአገራችን አዎንታዊ ነገሮችን መዘገብ ጀምረዋል። በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ እና የሠላም መሠረት ሥር እየሰደደ ይሄድ ዘንድ የዲያስፖራ ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዲያስፖራ አካባቢ የሚገኙ ፅንፈኞችም በአገራችን የቀሰሩትን ጦረኛ ጣት ማጠፍ አለባቸው። ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኞች መሣሪያ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ወገኖችን በውይይት መመለስ ካልተቻሉም መነጠል አለባቸው። ሠላም ሁሉም ዜጎች በጋራ የሚታገሉለት የጋራ አጀንዳ ነው።

በዲያስፖራው አካባቢ የፅንፈኛው መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጨውን ነገር ለማወቅ በቅድሚያ መመርመር ያስፈልጋል። አንድን ነገር ተባለ ብለን ከመናገር በፊት ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን ይችላል ወይ? እንዴትስ ተናጋሪዎች መረጃውን ሊያገኙት ቻሉ? ይህን ነገር የሚያስወሩ ሰዎች ዓላማቸው ምንድነው? ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል። ከአገራችን እና ከወገናችን ጋር ያለንን ሠላማዊ ግንኙነት ለመጠበቅ የሚቻለው ነገሮችን በመመርመር ስንረዳ ነው።

የአገሬ ሰው ሌባው ሌባ! ሌባ! እያለ ይሮጣል የሚል አባባል አለው። የዛሬው ዘረኛም ቀድሞ ሌሎችን ዘረኛ! ዘረኛ! እያለ ከውይይት መድረክ የሚሸሽ ነው፡፡ ዘረኛ ማለት በቀላሉ ሌላውን በእምነቱ፣ በቋንቋው፣ በቆዳው ቀለም የሚያገል ማለት ነው።

በዲያስፖራው አካባቢ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የእምነት ተቋማት እና ስብስቦች ዘረኝነትን መወጋት ከቻሉ ዕድሜያቸውም ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ውጭ በዘረኝነት የተሰነቁ አደረጃጀቶች ከጊዜያዊ እይታ ያለፈ ትርጉም የላቸውም። የዲያስፖራ ተቋማት ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የሚያስተናግዱ ሆነው እንዲቀረፁ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመረባረብ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡

ቂምና ቁርሾ የአሁኑ ትውልድ አይገልጸውም፡፡ ቂምና ቁርሾ የፅንፈኛ ፖለቲከኞች ባህርይ ነው፡፡ የዛሬው ትውልድ ከትናንቱ ዘመን ካለፈበት የፖለቲካ ሽኩቻ ራሱን መከላከል አለበት፡፡ አዛውንቶች ግን ሊተውት ይከብዳቸዋል፡፡ ሌላ ታሪክ የላቸውምና፡፡

አንዳንድ ወገኖች በምዕራቡ ዓለም የዴሞክራሲን ባህል በመርሳት ነፃ አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖችን ለመነጠል ጥረት ያደርጋሉ።እንደ እውነቱ ከሆነ መነጠል የነበረባቸው የግለሰብ ነፃነትን የሚጋፉ ወገኖች ነበሩ፡

እነዚህ ወገኖች ደርሰው ስለ ዴሞክራሲ የሚያወሩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ወገኖች «ጅብ በማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ» የሚለውን ተረት እስኪያጣጥሙት ድረስ ደጋግሞ በመንገር የግል ነፃነትን መጠበቅ ያስፈልጋል።

በዲያስፖራው መካከል ቀጣይ ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ማህበራዊ ካፒታል ሊዳብር የሚችለው ግልፅ ውይይት ማካሄድ ሲቻል ነው። የሚካሄደው ወይይትም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል። የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብም ተገቢ ነው። በዝህነትን የሚቀበልና ለልማቷ የሚታትር ትውልድን ትሻለች እንጂ የጥፋት መልዕክተኛ የሆነውን የፅንፈኝነት አካሄድና አመለካከት በምንም መልኩ አትቀበልም።ጽንፈኛ ዲያስፖራውም ከዚህ የውድቀት መንገድ ራሱን ማዳንና መታረም አለበት።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

1 comment:

Anonymous said...

betam asgerami new

Post a Comment