Thursday, October 02, 2014

"በኤምባሲው ሁከት የፈጠሩት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው" - አምባሳደር ግርማ

(መስከረም 21/2007, (አዲስ አበባ))--በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተፈጠረው ሁከት የኢትዮጵያን ዕድገትና መልካም ስም የማይፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች የፈፀሙት ድርጊት መሆኑን ኤምባሲው ገለፀ።



በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንደተናገሩት ከትላንት በስቲያ በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ቀን አካባቢ ቁጥራቸው ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ግለሰቦች ወደ ኤምባሲው በመግባት ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል። ግለሰቦቹ በኤምባሲው የቆንስላ አገልግሎት ስራ ክፍል ውስጥ በመግባትና በመሳደብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለማውረድም ሞክረዋል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም የአገሪቱ የጥበቃ ኃይል በስፍራው በመድረስ ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦችን ለአንድ ሰዓት ያህል በቁጥጥር ስር ማዋሉንና በኋላም ማንነታቸውን በመለየትና አድራሻቸውን በመያዝ መለቀቃቸውን አምባሳደር ግርማ ተናግረዋል።

በዕለቱ ምንም ዓይነት በህጋዊ መንገድ የተጠራ ሰልፍ እንዳልነበር የተናገሩት አምባሳደሩ "የድርጊቱ ፈፃሚዎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለስራ ወደ አገሪቱ ሲመጡ እየተከታተሉ የሚሳደቡ፤ በተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶችና በሻእቢያ ጀሌዎች የሚነዱ ናቸው" ብለዋል።

በህገወጥ ድርጊቶቻቸው በአገሪቱ ፖሊሶች ሳይቀር የሚታወቁት እነዚህ ህገወጥ ግለሰቦች በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያና አሜሪካ መሪዎች ደረጃ የተደረገው ውይይት በጣም ውጤታማ መሆኑና ይህም ከመሪዎቹ አንደበት መነገሩ ያናደዳቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላም በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤምባሲው ስልክ በመደወል “ሰንደቅአላማችንን ለማውረድና ለማዋረድ በተሞከረው ድርጊት እጅግ አዝነናል”  ሲሉ ገልፀውልናል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኃብትና ንብረት በሆነው ኤምባሲ ከህግና ከቪዬና ስምምነት ውጪ በመሆን አስነዋሪ ድርጊት መፈፀማቸውም ኮንነዋል።
ምንጭ:  ኢዜአ

1 comment:

Anonymous said...

Dge adrgu wraaa awrbte smntne mulu dmo

Post a Comment