Wednesday, August 20, 2014

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማይቀዘቅዝ ትኩሳት- በማይደበዝዝ ፅናት የታጀበ የማንነት ዓርማ!

(Aug 20, 2014,  (አዲስ አበባ))--እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ግድቡ የሚነገሩ የትኛውም ዓይነት አሉታዊ አስተሳሰቦች ይቆረቁሩን ጀምረዋል። አትችሉም ሲሉን ችለን፣ አትጀምሩም ሲሉን ጀምረን ከማሳየት አልፈን፣ ግድቡን ጨርሰን ባኖርነው አሻራ በታሪካዊ ግንባታው ውስጥ ህያው ሆነን ለመታየት ከልብ ቋምጠናል። ይህ የዘመን መንፈስ ነው፤ የልማት ትኩሳት ነው፤ ችሎ የማሳየት በሽታ ነው! ከጅምሩ እስከአሁን ባሉት የሦስት ዓመታት ጊዜያት ዕለት በዕለት በሁላችንም መንፈስ ውስጥ ከፍታ እየፈጠረ የመጣው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማንነታችን ወደመሆን መሸጋገር የመቻሉ ምስጢር ማረጋገጫም ነው።

ይህ ልባዊ ፍላጎትና መንፈሳዊ እምነት ወደመሆን የተሸጋገረ የዘመን ትኩሳት በእዚህ ትውልድ ማንነት ውስጥ የፍትሐዊነትና የእኩልነት ነበልባል ፈጥሮ አካባቢውን በብርሃን ሊያደምቅ፣ ጨለማን ሊሰብር፣ ድህነትን ሊንድ፣ ብልጽግናን ሊያውጅ በግስጋሴ ላይ ነው። ጉዞውን ሊያቆም፣ ሊያስቆም የሚችል አንዳች ኃይል የለም።

ይህ እልህ የተቀላቀለበት የፀረ ድህነትና የህዳሴ ጉዞ በበረታ ቁጭትና ተሳትፎ ስለታገዘ የማይጨበጥ መንፈስ እስኪመስል ድረስ የአትችሉም ሰንሰለቶችን በወላፈኑ እያቃጠለ ይበጥሳቸውም ጀምሯል። በእዚህም ካለፈው የበረታ፣ የላቀም ሀገራዊና ሕዝባዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች መታየት ችለዋል። እኛ ስለ እኛ ከምንናገረው በላይ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያውያኖች ስለጀመርነው ሀገራዊና አካባቢያዊ ልማት ይናገሩልን ጀምረዋል። ይህም ዓለም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጎን መቆማቸው አይቀሬ መሆኑን አመላክቷል።

በታላቅ ኢትዮጵያዊ ፅናት፣ በታላቅ የሕዝብ ቁርጠኝነትና ሕዝባዊ ተሳትፎ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲከናወን የቆየው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሌም አብሮን በዘለቀው የይቻላል መንፈስና የተግባር ውጤት ከፍ ብለን እንድንታይ አቅጣጫ ማሳየቱንም ቀጥሏል። ነገን ከምንደርስበት ዘላቂና የተሻለ ጥቅም በተጨማሪ በዛሬ የጋራ ልማት አሻራችንን አኑረን ሌላ አዲስ የዘመን ፈጠራ እንዲወለድ ምክንያትና ብርታትም ይሆነናል። ይህን ትልቅ ግብ እና ራዕይ የያዘ ጉዞ ዳር ለማድረስ አሁንም «እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!» እያልን በቃልም በተጠናከረ ተሳትፎም ልንረባረብ ይገባል።

እኛ ኢትዮጵያውያን (በሀገር ውስጥም በውጭም ያለን) የሀገራችን እውነተኛ ልጆች መሆናችን በተግባር በማስመስከር ቁጭትና ፅናታችን፣ ተሳትፎና ጥረታችን ባስገኘው ውጤት በየዕለቱ በህዳሴው ግድብ ላይ የየራሳችንን አሻራ ማረፉን ማረጋገጥ ያስፈልገናል። እንደጀመርነው ጨርሰን በማሳየት በእኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንደምናምን፣ ለእዚህም ፋና ወጊ ሆነን እንደሠራንና እንደምንሠራ በተጨባጭ ማሳየትም ይኖርብናል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርን 3ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ግንባታው በሚከናወንበት ቤኒሻንጉል ክልል ጉባ ወረዳ በተዘጋጀ ሥነሥርዓት የበዓሉ ክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን አበክረው የተናገሩትም ይህንኑ ነው።

በእንደጀመርነው እንጨርሳለን መርህ የተጀመረውን ሀገራዊ ፕሮጀክት በማሳካት ወደበለጸገች ኢትዮጵያ የሚደረገውን የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ ይቀጥላል። ሕዝቡም በባለቤትነትና በቁጭት የጀመረውን የራሱን ፕሮጀክት ዳር እንደሚያደርሰው ጥርጥር የለም። ለእዚህም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት የግንባታው የሀብት ምንጭ፣ ገንቢና አናፂው ራሱ ሕዝቡ ሆኖ ቃሉን በተግባር እንደሚያረጋግጠው መንግሥት ፅኑ እምነት አለው።

ከ30 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ሲጠነሰስ ብዙ የአይቻልም አስተሳሰቦች ሲንፀባረቁ ነበር፤ ፕሮጀክቱ ህልም እንጂ እውን የሚሆን አይደለም ከማለት ጀምሮ ግድቡን ማሰብ ወቅታዊ አይደለም፣ በግብፅ መንግሥትም አይፈቀድም የሚሉ አሳሳችና አዘናጊ ምክሮችን ሲለግሱ የነበሩም የሚታወሱ ናቸው።

ታላቁ መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግን የግድቡን የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡ ጊዜ በሕዝባቸው ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው በግልጽ አቋማቸውን በማሳወቅ ግንባታው ለአፍታ የማይቆም የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ማብሰሪያ መሆኑን አመልክተው ነበር፤ ያለመቻልና ተስፋ መቁረጥ ማዘናጊያ ማክተሚያ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር። ሕዝቡም በወቅቱ የዘመናት ቁጭቱንና ሀገራዊ ተረቱን ቀልብሶ በግንባታው ተሳትፎ እንደየአቅሙ በመረባረብ ግድቡን አስጀምሯል፤ ቦንድ በመግዛት፣ ቦታው ድረስ ተጉዞ በአስቸጋሪ የተፈጥሮ ፈተና ሳይበገሩ እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎችን በማበረታታት ለሀገራችንና ለራሳችን ልማት አብረን ነን ሲል አብሮነቱን ገልጿል፤ እስከአሁንም በመግለጽ ላይ ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተጨባጭ የታየው ውጤት ይኸው ነው። ግንባታው ተጠናክሯል። የልማት ርብርቡ ቀጥሏል። የህዳሴያችንን ፈለግ እንደጀመርነው ለመዝለቅ፣ የማንነት ዓርማነቱንም ለማሳደግ የተሳትፏችን መጠናከር የግድ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የባንዲራችንን ያህል በአንድነት ያሰለፈን ዓርማችን ነው፤ ኩራታችን ነው፣ ታሪካችንም ነው። የፍትሐዊነትና የእኩልነት ነበልባሉ በማንነታችን ውስጥ ያኖረው ፍም ሳይቀዘቅዝ ኢትዮጵያዊ ተሳትፏችን እስከ ፍፃሜው ይቀጥላል።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ, አዲስ አበባ 

No comments:

Post a Comment