Wednesday, August 20, 2014

ግልፅ ደብዳቤ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር

(Aug 20, 2014, (አዲስ አበባ))--ክብርት አምባሳደር፣ ለጤናዎት እንዴት ነዎት?...... ይህንን ግልፅ ደብዳቤ ጋዜጣ ላይ እንዳወጣ ያስገደደኝ ፤ ከወር በፊት ደብዳቤዬን ቢሮዎ ድረስ በመምጣት ሠጥቼ ብሄድም እስካሁን መልስ ባለማግኘቴ እና፤ ምናልባትም እርስዎ አላገኙት ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡

ክብርት አምሳደር፤ ተስፋዬ እሸቱ ሀብቱ እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት መምህር እና የትምህርት ቤቱ ኃላፊም ነኝ፡፡ በተጨማሪም በሀገሬ ባለ የጥበባት እንቅስቃሴ ውስጥ በጸሐፌ-ተውኔትነት፣ በአዘጋጅነትና በተዋናይነት ጉልህ ሚና እየተጫወትኩ እገኛለሁ፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ ለእርስዎ ቅሬታየን እንድጽፍ ያስገደደኝ ምክንያት እንደሚከተለው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት «ሰን ዳንስ ኢንስቲትዩት» የተባለ ታዋቂ የሀገርዎ ድርጅት ለሦስት ሳምንት የሚቆይ የትያትር ዳይሬክተሮች ሥልጠና ሙሉ ወጭውን ሸፍኖልኝ እንድሳተፍ ቢጋብዘኝም፤ «ወጣት ነህ? አላገባህም? ባንክህ ውስጥ ገንዘብ የለም? ከዚህ በፊት የትም ሀገር ሂደህ አታውቅም፡፡» ተብዬ ቪዛ በመከልከሌ ከተጋበዙ 8 ወጣት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተሮች እኔ ብቻ መካፈል አልቻልኩም፡፡ በድጋሜ አመለከትኩ፤ እንደገና ተከለከልኩ፡፡ የጋበዘኝም ድርጅት እኔን ወክሎ ለኮንግረሱ ቢያመለክት አልሆነም፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ የቆንፅላዎ ቪዛ የመከልከል ምክንያት አሳማኝ ብቻ ሳይሆን ነጥብ ያለው ሆኖ አላገኘሁትም ነበር፡፡ እንደሚገባኝ እርስዎ ሀገር ያለውን እምቅ እውቀት መማር ያለብኝ በወጣት ዘመኔ ይመስለኛል፡፡ እኔ እርስዎ ሀገር ለመሄድ እርጅናየን መጠበቅ ይኖርብኝ ይሆን? ትዳርስ መመስረት ያለብኝ አሜሪካ ለመሄድ ብቻ መሆን ነበረበት? ትዳር ላለመያዝ የራሴ የግሌ ምክንያቶች መታየት አልነበረባቸውም? ሀገርዎ ተምሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ባለትዳር መሆን መስፈርት መሆን ነበረበት?

ክብርት አምባሳደር፤ እኔ የዩኒቨርሲቲ መምህር እንጂ ነጋዴ አይደለሁም፡፡ እርስዎ በግልፅ እንደሚያውቁት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የህይወት ግባቸው፤ በዘመናቸው ጥናትና ምርምር በማካሄድ ሀገራቸውን በእውቀት ማነፅ ነው፡፡ እንደሚገባኝ ገንዘብን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲ ትክክለኛ ምርጫ አይመስለኝም፡፡ ወይስ ኮንሳላሩ ፊት ከመቅረቤ በፊት ከወዳጅ ጓደኞች ገንዘብ ሰብስቤ ማሳየት ነበረብኝ ይሆን? ከዚያስ በኋላ በራሴ ውሸት ከራሴ ጋር በቀላሉ የምታረቅ ይመስልዎታል? ታዲያ አንድን የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የባንክ ደብተር መጠየቅ ክብረነክ አይሆንም? ከዚህ ቀደም ሌላ ሀገር አለመሄዴ ቪዛ ከመከልከያ መስፈርቶች መካከል አንዱ መሆንስ ነበረበት. . .? የእኔ ምርጫ እርስዎ ሀገር ካሉ አርቲስቶች እውቀት መካፈል ቢሆንና፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳመለክት የእርስዎ ሀገር ድርጅቶች ቢቀበሉኝ፤ ቪዛ ለማግኘት ከኔ ፍላጐት ውጭ አውሮፓ ወይም ላቲን አሜሪካ መሄዴ ግዴታ መሆን አለበት. . .? የምርጫ ጉዳይ ስፍራ ሊኖረው አይገባም! በምርጫ ማመን የእርስዎ ሀገር የዘመናዊነት አስተሳሰብ መገለጫ ይመስለኝም ነበር፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች፣ የባለፈው ዓመት ሥልጠናዬ ሳይሆን ቀረ፡፡ ምክንያቶቹ ባያሳምኑኙም ምናልባትም እኔ ያላየሁት፣ ያልገባኝ ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል በሚል እምነት ቪዛ መከልከሌን በፀጋ ተቀበልኩት፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ በዓመቱ በሊንከን የትያትር መዕከል አማካኝነት ከሀምሌ 6-27፣ እ.ኤ.አ የሚቆይ ወጣት የትያትር ዳይሬክተሮች ሥልጠና ከነሙሉ ወጭው ጋር ብጋበዝም፤ የእርስዎ ቆንፅላ ለሦስተኛ ጊዜ ቪዛ ከለከለኝ፡፡ ይቅርታ ያደርጉልኝ እና ይሄ ለእኔ ስድብ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮንስላሩ ጥያቄ ከጠየቀኝ በኋላ ቪዛ ለመስጠት ፍቃደኛ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እኔም አመሠገንኩት፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ግን ቪዛ እንደማይሰጠኝ አረጋገጠልኝ፡፡ የተከለከልኩበትን ምክንያት ስጠይቅ እንደ ሥራ ፈት ሰው «ወረቀቶችህን ጠቅልለህ ውጣ!» ነበር መልሱ፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ በሀገረ አሜሪካ በእኔ እድሜ አካባቢ ለሚገኝ የዮኒቨርሲቲ መምህር እና የአንድ ታዋቂ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ስለሚደረግለት እገዛና ድጋፍ፣ ስለሚያገኘው ሙገሳ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ታዲያ በጣም ሠለጠኑ ከሚባሉ ቀዳሚ ሀገሮች መካከል የእርስዎ ሀገር ለወጣት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የሚሰጠው ምላሽ አግባብ ነው ይላሉ? በምክንያት ማሰብ እና መኖር የእርስዎ ሀገር መገለጫስ አይደለምን? ወይስ የቆንፅላው የቪዛ ፍቃድ እንዲፀድቅልኝ «ቪዛው ተፈቅዶልሀል» ስባል እንደ ህፃን ልጅ መቦረቅ ነበረብኝ? ይህ ዓይነቱ ኢምክንያታዊነት እኔን ብቻ ሳይሆን በኃላፊነት የማስተዳድረውን ትምህርት ቤት፤ ሲቀጥልም በሀገሬ የኩራት መገለጫ ከሆኑ ዩኒቨርስቲዎች ቀዳሚ ስፍራ ያለውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን መሳደብ እና ቦታ አለመስጠት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የዘለለ ትርጉም ማግኝት አልቻልኩም፡፡ ቅሬታዬንም ለርስዎ የገለፁኩልዎ፤ የምኮራበት፣ ቀን በቀን እራሴን በእውቀት የማንፅበት ተማሪዎች ከዛም በላይ ሀገሬ ብዙ የምትጠብቅበት ዩኒቨርሲቲዬ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገባውን ክብር በማጣቱ ነው፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ ካልተሳሳትኩ የእርስዎ ሀገር ሥልጣኔና የታወቁ ዩኒቨርሲቲዎቻችሁ የጥንካሬ ምንጭ እና የጀርባ አጥንት ከሚገለፅባቸው ባህሪያት አንዱ፣ ሀገርዎ ለዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች የምትሠጠው ክብር ነው፡፡ በተለይም እኛ የታዳጊ ሀገር ወጣቶች ይህ ከእናንተ መማር የምንፈልገው ነው፡፡ ታዲያ ገና ለገና የድሀዋ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህር መሆኔ፣ አሜሪካ ሄዶ አይመለስም ተብሎ ታስቦ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ስድብም ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ሀገርዎ ሂደው የቀሩ ካሉ ስህተት ብቻ ሳይሆን ሀገርን መክዳት ነውና ሀገሩን ለከዳ ደግሞ እችን ታህል ቦታ የለኝም፡፡ ሁሉም ያደርጉታል ማለት ግን አይደለም፡፡ በመሆኑም የእኔም፣ የዩኒቨርሲቲዬም ክብር ሲጓደል፣ በምክንያት ለሚያምኑት ለእርስዎ ቅሬታዬን ማቅረብ አግባብ ነው እላለሁ፡፡

ክብርት አምባሳደር ጉዳዬ፤ የመጻፌ ዓላማም ከእርስዎ ሀገር መጻሕፍት በቀሰምኩት እውቀት መሠረት ተግባራዊ መፍትሄ ለሚሻ ጉዳይ አመክንዮን መሠረት ያደረገ ግብረ - ምላሽ የመስጠት ሥርዓትን መተግበሬ፤ ቅሬታዬንም በዚሁ አግባብ መግለፅ እና መግለፅ ብቻ መሆኑን እንዲያጤኑልኝ እሻለሁ፡፡ ምናልባት የአንድ ሀገር አምባሳደር በቆንፅላ የውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን የለውም ብለው የሚያስቡም ከሆነ፤ ቆንፅላዎ ሰው ነውና ህፀፅ እንደማያጣው ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ በተለይም ከላይ ከጠቀስኩልዎ ማሳያ አንፃር ‹‹አጥፍቷል›› ብዬ ብናገር የምሳሳት አይመስለኝም፡፡

ክብርት አምባሳደር፤ በመጨረሻም ቅሬታዬን አንብበው ሐሳቤን በውል እንደሚያጤኑልኝና የቅሬታዬንም አግባብነት ተረድተው በኤምባሲዎ ቀጣይ የተግባር አፈፃፀም ሥርዓት ውስጥ በግብአትነት እንደሚጠቀሙበት ያለኝን ፅኑ እምነት ስገልፅልዎት በአክብሮት ነው፡፡

ከተስፋዬ እሸቱ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የትያትር ጥበባት ት/ቤት ኃላፊ እና መምህር
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ, አዲስ አበባ

1 comment:

Anonymous said...

I don't trust this article. You are trying US embassy to defame. You might be terrorist for US. Is that special for you? Others might be denied....send the letter to HM Desalegn and he will beg for you.....in the first place, you send to Addis Zemen news paper which is the basket of lies........for the sake of kiray sebsabinet in your language......

Post a Comment