Saturday, August 23, 2014

«የፅንፈኛው ዳያስፖራ ተቃውሞ ተስፋ የቆረጡ የጥቂት ግለሰቦች አቋም ነው» - አቶ ሬድዋን ሁሴን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር

(Aug, 23, 2014,(አዲስ አበባ))--በቅርቡ በአሜሪካ ሁለት መድረኮች ተካሂደዋል። እነዚህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ጎልተው ያሳዩ ነበር፡፡ በአገሪቷ እየተካሄደ ያለው ልማት ብዙሃኑን ተጠቃሚ ያደረገና አነስተኛ ገቢ የነበራቸውን ዜጎች ኑሮ እየለወጠ ያለ ነው። ይህም መድረኩ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በበለጠ ለኢትዮጵያ እውቅና እንዲሰጣት አድርጓል፡፡ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያለው ሚናም ትላልቅ መድረኮችን በኃላፊነት እንድትመራ አሳጭቷት ነበር፡፡

በእነዚህ መድረኮች ተሳታፊ የነበሩ በዓለም ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ኩባንያዎችም በሀገሪቷ ያለው ፋጣን ልማትና ለኢንቨስትመንት በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ በመማረካቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችም ከአሜሪካውያን ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበትንና ምርቶቻቸውንም በስፋት ለመሸጥ የሚችሉበትንም ዕድል ከፍቷል። ዳያስፖራው ለሀገሩ ልማት ይበልጥ አስተዋፅኦ ለማበርከት መነሳሳት ማሳየቱም መድረኮቹ ካበረከቷቸው ትሩፋቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ነው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን የተናገሩት። ሚኒስትሩ ሰሞኑን በመድረኮቹና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ 

አሁን ያለነው የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማገባደጃ ወቅት ላይ ነው ፡፡ እቅዱን በማሳካት ረገድ መንግስት ምን ያህል ውጤታማ ነበር? በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ቀሪ ዕቅዶችን ወይም አሁን «ተንጠባጥበዋል» ተብለው የሚታሰቡ ስራዎችን ማሳካት ይቻላል ብለው ያስባሉ ?

አቶ ሬድዋን፦ የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተመለከተ እንደተባለው የመጨረሻው ዓመት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ እስካሁን ድረስ በተደረጉት ግምገማዎች የተለጠጠውን እቅድ ተንጠራርተን መድረስ ባንችል እንኳ መነሻ ግቡን ማሳካት የምንችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ በተለይም በግብርና ዘርፍ አበረታች የሚባል ውጤት እያስመዘገብን ነው፡፡ ይህም ቀድመንም ማሳካት የምንችልበት እድል መኖሩን ያሳያል፡፡ ይሁንና እንደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሳሰሉት መስኮች የታሰበውን ያህል በፍጥነት አልተጓዝንም፡፡ ከዚሁ ጋር የተንጠባጠቡትን አካክሶ መሄድ የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን ለይቶ መሄድ ይጠይቃል፡፡ በዚህኛው ዓመት በተለይም ቀሪ ስራዎችን በማከናወን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርብናል፡፡ 

አጠቃላይ እድገቱን ስናይ ግን በማንኛውም መመዘኛ ፈጣንም ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድም በተያዘው በጀት ዓመት ቀሪ ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ በምንችልበት ሁኔታዎች ላይ አቅደን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ በመሆኑም ከ80 እስከ90 በመቶ እቅዶችን ለማሳካት ከተቻለ ትልቅ እመርታ ነው ብለን መውሰድ ይገባናል፡፡

ጥያቄ፦ በሀገሪቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ግን በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዜጎችን እያስመረሩ ነው የሚገኙት፡፡ በተለይም መብራት፣ ቴሌኮምና የውሃ አገልግሎቶችን በሚመለከት ህዝቡ በተደጋጋሚ አቤቱታውን ሲገልፅ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት በመሰረታዊነት ችግሮቹን ለመፍታት እየሰራ ያለው ስራ ምንድን ነው?
አቶ ሬድዋን፦ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በተያያዘ በሁሉም ረገድ መሻሻሎች እንዳሉ ከሰሞኑ በተደረገው አገር አቀፍ የመልካም አስተዳደር ጉባኤ ላይ ከህዝቡ ተገልጿል፡፡ በመድረኩ በተለይም በቴሌኮም አገልግሎት ይበል የሚባል ለውጥ መታየቱን ገልጿል፡፡ በወቅቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከህዝቡ ክንፍ ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግና በመስራት ሊፈቱ እንደሚችሉ መግባባት ላይ ላይ ተደርሷል፡፡

በተለይም የመብራት ሃይልን በተመለከተ የተወሰኑ ከግብዓት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዋናነት የሃይል መቆራረጥ ችግር የሃይል እጥረት ምክንያት እንዳልሆነ፤ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት የመቆራረጥ ችግሮች በትራንስፎርሜሽን መስመሩ ላይ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ከሰራተኞች የሚደርሱት አሻጥሮችም ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት መሆኑን ተማምነናል፡፡ ይህንንም ህዝቡና መንግስት በጀመሩት የትብብር መድረክ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ መፍታት የሚቻልበት እድል እንዳለ፤ አሁንም መሻሻል እንዳለበት ተስማምተናል፡፡

ጥያቄ፦ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡በተለይም የተደረገው ጭማሪ «ከተጠበቀው በታች ነው፣ጭማሪው በአነስተኛና ኑሮ ላይ የሚገኘውን የማይደጉም ነው» የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ ፡፡ ይህን በተመለከተ የመንግስት ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ሬድዋን ፦ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የደመወዝ ጭማሪው አንድ የአገሪቱን የማደግ ፍላጎትና የመክፈል አቅምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የዋጋ ንረትን በማያባብስ ሁኔታ መሰረት ተደርጎ ነው የተጨመረው፡፡ ጭማሪው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው። ከዚህ በላይ ቢጨመር ደግሞ የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሀገሪቱን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ነው፡፡ ተጨማሪ ለመክፈል አቅማችንን ከዕደገታችን ጋር የተመጣጠነ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ 

በሌላ በኩል ሰራተኛውን ይበዘብዝ የነበረው የትራንስፖትና የቤት ኪራይ ጉዳይ እንደመሆኑ ትራንስፖርት ማቅረቡ እንደ ጭማሬ ሊወሰድ ይገባል፡፡ አሁን መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ይህንን እንዴት ነው የሚያሳካው የሚለው ነው፡፡ የቤት ክራይም በተመሳሳይ የሰውን ወገብ የሚበጥስ ጉዳይ ነው፡፡እያንዳንዱን በጎ እርምጃ አወድሰን የጎደለውን ደግሞ በሚዛን አንስተን እንዴት እንሙላ የሚለውን በጋራ አቅጣጫ አስቀምጠን መንቀሳቀስ ነው የሚጠበቀው፡፡

ጥያቄ ፡- በአሜሪካ በተካሄደው ፎረም የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ልኡክ ከዳያስፖራው ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው ይነገራል፡፡ ከዳያስፖራው ጋር ለመነጋገር ያደረጋችሁት ሂደት ነበር ወይ? በዋናነት እንደተግዳሮት አድርገው ያነሱት ችግር ምንድን ነው?

በሌላ በኩል ደግሞ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በልዑካኑ ቡድኑ ላይ ያሰሙት ከፍተኛ ተቋውሞ በሀገር ውስጥ ያለውን ህዝብ በሁለት ጎራ የከፈለ ጉዳይ ነው ሆኖ የሰነበተው፡፡ አንደኛው ወገን « ፈፅሞ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት አፈንግጦ የሄደና ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው» በማለት ይከራከራል፡፡ ሌላኛው ወገን በአንፃሩ «አሜሪካ የዴሞክራሲ አገር እንደመሆንዋ ማንም ሰው የፈለገውን መናገር ይችላል» ሲል ተደምጧል፡፡ በዚህ ረገድ በህግ አግባብ ይህ ተግባር እንዴት ነው ሊታይ የሚችለው፡፡ መንግስትስ በጉዳዩ ላይ ዝም ማለት ነበረበት ወይ?

አቶ ሬድዋን ፦ ቴክሳስ በነበረው መድረክ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ሆነው ነበር፡፡ ሂውሰተን ቆንፅላ ፅህፈት ቤት ስለሌለን እዛ የነበረውን መድረክ ያዘጋጁት የዳያስፖራ አባላት ናቸው ፡፡ ከተከፋይ የኤምባሲ ሰራተኞች በላይ ገንዘባቸውን አውጥተው ለመድረኩ ስኬት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚሰሩና ለአገራቸው ለውጥ የሚተጉ ዳያስፖራዎች አሉ፡፡

በሌላ በኩል ግን በሂውስተን 18፣ በካሊፎርኒያ ሎስአንጀለስ ደግሞ 30 የሚሆኑ ሰዎች መድረኩን ሲቃወሙ ተስተዋልዋል፡፡ ዲሲ ላይም በተመሳሳይ ከ200 የማይበልጡ ሰዎች ነበሩ ሰልፍ ወጥተው ሲሳደቡ የነበሩት፡፡ በወቅቱ ይሳደቡ የነበሩትም አመራሩን አልነበረም፤ ሀገራቸው ላይ መጥተው ኢንቨስት ያደረጉትን ባለሀብቶች ነበር «ባንዳ» እያሉ ሲሳደቡ የነበሩት ፡፡ 

የገዛ ወገኖቻቸውን « እንደኛ ራሳችሁን ጠቅማችሁ አገራችሁን አልሙ» ማለት «ባንዳ» የሚያሰኝ አቋም የሚያንፀባርቅ ምን አይነት ሰው ነው? የሚፈልጋት ኢትዮጵያ የትኛዋን ኢትዮጵያ ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ አጠቃላይ ዳያስፖራውን ማየት ከተቻለ ግን ስለሀገሩ መረጃም አለው፤ ይከታተላል፤ እየሆነ ባለው ነገርም ደስተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል ጥቂት የሆነ ሃይል ፅንፈኛ የሆነ አቋም አለው፡፡ ይህ ደግሞ አይኖርም ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እንዳይኖር ማድረግም ከንቱ ልፋት ነው የሚሆነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ምን ያህል ይዘው ይንቀሳቀሳሉ የሚለው ጉዳይ ነው ያለው፡፡ በወቅቱ የተንፀባረቀው ሃሳብ የአብዛኛው ዳያስፖራ አቋም አይደለም፤ አብዛኛውንም አይወክልም፡፡ በመነጠል ላይ ያሉና አጀንዳቸው ተስፋ መቁረጥ ላይ የተመሰረተ ግለሰቦች አቋም ነው፡፡ ከህግ አንፃር ያለው በሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው ፡፡

ጥያቄ ፦ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዋጋው እንዲቀንስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተነጋገረ ነው የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ምንድን ነው?

አቶ ሬድዋን ፦ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ በጣም በርካታ አስተያየቶች ይቀርባሉ ፤ የሚቀርቡ አስተያየቶች ሁሉ ግን ይተገበራሉ ማለት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ፣ ትርፍና ኪሳራውን አይቶ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ይበጃል ያለውን እርምጃ ነው የሚወስደው፡፡ በአጠቃላይ በከፍተኛ ደረጃ የብር የመግዛት አቅምን እንዲቀንስ ማድረግ ዋና መፍትሄ ነው ብሎ አይወስድም ፡፡

ይሁንና በእኛ በኩል መንግስት ቀደም ሲል እንደሚታወቀው 2002 .ም ላይ 10 በመቶ ፣2003.ም ላይ ደግሞ 20 በመቶ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ በተለይም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ የዋጋ ግሽበቱን ወደ አንድ አሃዝ እንዲወርድ ሰፊ ስራ አከናውኗል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረቱ ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ደርሷል፡፡ ዋጋ ግሽበቱን በቀጣይነት ለመቆጣጠር፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፥ የውጭ ምንዛሬ አቅማችንን ማጎልበት እንዲቻል ደግሞ የወጭ ንግዱን ማስፋት ወሳኝ ስራ ነው፡፡
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ, አዲስ አበባ  
 Home

No comments:

Post a Comment