Sunday, March 02, 2014

ሰሞነኛው «የድንበር ተካለለ» መላምታዊ ፖለቲካ

(Mar 02, 2014, (አዲስ አበባ))--በአንዳንድ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝተው በሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የሰከነ ሰላማዊ የተቃወሞ ፖለቲካ አካሄድን መመልከት ብርቅ እየሆነ ከመጣ ከራርሟል፡፡ የአገራችን ተቃዋሚዎች በተለይ በጣም ጯሂ የሆኑት ወደ ሕዝብ ልብ ሊያደርሳቸው የሚችል አንድም ፖሊሲና ፕሮግራም የላቸውም፤ በመሆኑም ስሜት ይቀሰቅሳል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ጉዳይ አንጠልጥለው የመሮጥ አባዜ ተጠናወቷቸዋል፡፡

የተወሰኑ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶችም ይሄንኑ «አብዶ የማሳበድ» አባዜ ሲያቀነቅኑ ይታያል። እነዚህ ተቃዋሚዎችና የአመለ ካከታቸው አራማጅ ጋዜጠኞች ሰሞኑን እንድተለመደው አብደው ሊያሳብዱን አንደ ሳይፈትሹ ቃርመው የሰለቀጡትን አጀንዳ ይዘው ብቅ ብለዋል። ይህ አጀንዳ «የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር መሬት ቆርሶ ለመስጠት ስምምነት ተፈራረመ» የሚል ነው፡፡ በነፃ ፕሬስ ሽፋን አመለካከታቸውን የሚያራምዱ ልሳኖቻቸው ደግሞ ለሱዳን ተሰጡ ያሉዋቸውን ስፍራዎች ዝርዝር አውጥተዋል፡፡

ታዲያ ሰሞኑን ተቃዋሚዎቻችን ከየትም ቃርመው በነዙት ውዥንብር እየተናጥን እያለ ከወደ መንግስት አካባቢ እውነተኛውን ምላሽ መስማት ጀመርን፡፡ ከሳምንት በፊት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማካሄድን የመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ባቋቋሙት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አንስተውት ክምክር ቤቱ አባላት አንዱ የሆነው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የካቲት 3/2006 ዓ.ም ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ይህንኑ ጉዳይ የሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥቂት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነዙትን ውዥንብር በተመለከተ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላይ ጉዳዩ ተነስቶ የተሰጠውን ምላሽ ከመመልከቴ በፊት ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሰጡትን ማብራሪያ ልጥቀስ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦ የነበረው ጥያቄ «የኢትዮጵያና ሱዳን መሪዎች በሱዳን ካርቱም ተገናኝተው የድንበር ወሰን ስምምነት ተፈራርመዋል የሚል መረጃ ወጥቷል። እርግጥ ይህ መረጃ ትክክል ነው?» የሚል ነበር፡፡ ከእዚሁ ጋር ተያይዞ «ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ልትሰጥ ነው የሚል ወሬ በአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ሲወራ ይሰማል፤ በዚህ ላይ የመንግስት አቋም ምንድን ነው?» የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት በቅርቡ በቋሚነት በየሁለት ዓመቱ በመሪዎች ደረጃ የሚያደርጉትን የሁለቱ አገራት (የኢትዮጵያና ሱዳን) ከፍተኛ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡

ይህ ስብሰባ ድንገተኛ ወይም ልዩ ሳይሆን ቋሚ መሆኑን፣ ዓላማውም የሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ያተኮረ ሳይሆን፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የሚደረግበት እንደሆነም ተናግረዋል። የሁለቱ አገራት ጉዳይ ሲነሳ የድንበር ጉዳይ መነሳቱ አይቀሬ መሆኑንና ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ያለፉት አመታት በሙሉ ይህ ጉዳይ ሲነሳ መቆየቱን አሰታውሰው አሁን መነሳቱንም የተለየ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ጉዳዩን «ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ቆርሳ ሰጠች» በሚል አኳኋን ማንሳታቸው የራሱ መነሻ ምክንያት እንዳለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁ ሲሆን ባለፉት ምርጫ በተደረገባቸው ወቅቶች፣ ምርጫ አንድ አመት ሲቀረው፤ በ1996 ዓ.ም እና በ2001 ዓ.ም ጉዳዩ ተነስቶ በወቅቱ በቂ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል ብለዋል፡፡ አሁንም ምርጫ አንድ ዓመት ሲቀረው መነሳቱንም አስታውሰዋል፡፡

ከእዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ መረዳት የሚቻለው በምርጫ ፉክክር ወደ ሕዝብ ልብ ዘልቆ በውክልና ስልጣን ሊያሰጣቸው የሚያስችል አጀንዳ የሌላቸው ፓርቲዎች የድንበር ጉዳይ በጣም ስሜት ኮርኳሪና ሕዝብን ቅር የሚያሰኝ በመሆኑ ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል የሚያነሱት መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ስሜት ኮርኳሪ ጉዳይ አደናግረው ከሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድ ውጪ በሁከት ስልጣን ለመመንተፍ የሚያስችል ዕድል ይገኝ ይሆናል ብለው ተስፋ ስለሚያደርጉ ነው ይህን የማደናገር አካሄድ የመረጡት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተጨባጭ ያለውን እውነት አስመልክተው ሲያብራሩ፤ የኢትዮ ሱዳን ድንበር ስምምነት እ ኤ አ በ1902 በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት መፈረሙን፣ በአፄ ኃይለሥላሴ እና በወታደራዊ ደርግም የስልጣን ዘመን የድንበር ውሉ ተጠንቶ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲቀጥል፣ በእንጥልጥል የቀረው የድንበር ስምምነቱን በመሬት ላይ የማካለል ሥራ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑንም አስታውሰዋል። ኢህአዴግም የመንግስትን ስልጣን ከተረከበ በኋላ ይሄው የ1902ቱ የድንበር ውል ይቀጥል የሚል አቋም መያዙንም አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ ማብራሪያ መሰጠቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ የድንበር ስምምነት የሚፈርምበት፣ መሬት ቆርሶ ለሱዳን የሚሰጥበት ምንም ምክንያት እንደሌለም በማረጋገጥ የወሬው አናፋሾቹን መሰረተቢስነት አጋልጠዋል፡፡ ትክክለኛውና ተጨባጭ እውነታው ይህ መሆኑን ከተረዳን አሁን ወደነ ሰማያዊ ፓርቲ እንመለስና የበሬ ወለደ ታሪክ ነገራቸውን እንመልከት”

ሰማያዊ ፓርቲ ድንበርና ወሰንን የአሀዳዊ ሥርዓት ማቀንቀኛ ያደርጋል። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከፍተኛ መስዋዕትነትን በጠየቀ የህዝብ ትግል ሞቶ የተቀበረ አሃዳዊ የመንግስት ስርአት የመመለስ ዓላማ ይዞ የተነሳ ፓርቲ ነው። ፓርቲው ይህ ነው የሚባል አገራዊ ፕሮግራም ባይኖረውም አመራሮቹ ይህን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ያለው ብሄር ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ አወቃቀር ለሰማያዊ ፓርቲ ሊዋጥለት አይችልም፡፡

አቋሙን ከአዲሲቱ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር ጋር ሊያስተካክልም አልፈለገም፡፡ ይህን የማድረግ አቅምም ፍላጎትም የለውም፡፡ ፓርቲው አሃዳዊ መንግስት የመመስረት አቋም በአዲሲቱ ኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን ምንጭና ባለቤት በሆኑት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የስልጣን ውክልና እንደማያስገኝም ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ በማወቁም ሥልጣን ለመመንተፍ የሚያስችሉትን መንገዶች ሁሉ ይፈልጋል። ማንኛውንም ጉዳይ ውሸት ይሁን እውነት፣ ለሕዝብ ይጥቀም አይጥቀም፣ አሉታዊ ውጤት ያስከትል አያስከትል ትንሽ እንኳን ሳያስጨንቀው «ሕዝብን በመንግስት ላይ ማሰነሳት ያስችላል» ብሎ ከገመተ ይዞ ወደ አደባባይ ከመሮጥ አይመለስም፤ ማንም ሳይቀድመው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ (አንዳንዶች «ግራጫ»ይሉታል) ምንም ሳይመረምር ያዋጣኛል ያለውን የመቃወሚያ አጀንዳ ይዞ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት ዋነኛ የትግል ስልቱ ነው። ሌሎች ወደ ሕዝብ መቅረብ የሚያስችሉ የሰላማዊ ተቃውሞ መንገዶችን በፍፁም አይፈልጋቸውም፤ ምናልባትም አይችላቸውም፣ አያውቃቸውም ይሆናል፡፡ ይህን ስልት የመረጠው አደባባይ የወጣ ሕዝብ ሁሉ በግብፅ ታህሪር አደባባይ እንደሆነው የመንግስት ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት ስላለው ነው፡፡ ከግብፁ የታህሪር አደባባይ ሕዝባዊ ንቅናቄ በፊት ለውጥ የግድ ያለ የበሰለ ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ሰማያዊ ፓርቲ አያውቀውም፤ ይህን የማሰብ ፍላጎትም የለውም፡፡ የህዝብ ንቅናቄ፣ ጥቂት ግለሰቦች በግላቸው ባላቸው መሰረተ ቢስ ጥላቻ ተነሳስተው ከኪሳቸው አውጥተው በሚነዙት ስሜት የሚያግለበልቡ አጀንዳዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሚፈጠር ሳይሆን፣ የከፋ ጭቆና ያበሰለው የምሬት ውጤት መሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አያውቁትም፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ፓርቲያቸው የያዘው አቋም - በተለይ የህገመንግስቱ መሰረት የሆነው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብትን በተመለከተ የያዘው አቋም እነርሱን መሰል ጥቂት ወገኖች ብቻ የሚደግፉት መሆኑንም ማሰብ አይፈልጉም። በሕገመንግስቱ የተከበረላቸውን መብት የማይደግፈውንና ከፍተኛ ፅናትን በጠየቀ መራራ ትግል ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው የወረወሩትን ብሄራዊ ጭቆና ዳግም ሊጭንባቸው ለሚራወጠው ሰማያዊ ፓርቲ መቼም የስልጣን ውክልና ሊሰጡ አይችሉም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ሰማያዊ ፓርቲ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሐራሬ . . . ክልሎች ያሉትን ደጋፊዎች መመልከት በቂ ነው፡፡ አንድም ደጋፊ የለውም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ሰማያዊ ፓርቲ በሕዝብ ውክልና ስልጣን መረከብ አለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ መንግስትን ማስወገድ የሚችል ሕዝባዊ ንቅናቄ የመፍጠርም አቅም የሌለው ፓርቲ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ያም ሆነ ይህ ሰማያዊ ፓርቲ ከሳምንት በፊት ጎንደር ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂዷል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን የጠራው «መንግስት ድንበር ቆርሶ ለሱዳን ሰጠ» የሚል ፍፁም ውሸት ይዞ ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብን ለተቃውሞ ለመቀስቀስ የፈጠረው ወሬ መሰረተ ቢስ ውሸት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጉዳዩ የወሰን ጉዳይ በመሆኑ የዘጠኙንም የፌዴራል መንግስቱ ክልሎች ሕዝቦች የሚመለከት መሆኑንም ማስታወስ ነበረበት፡፡ «ድንበር ተቆረሰ» ብሎ የፈጠራ ወሬ የነዛበትን የሰሜን ጎንደር አካባቢ ሕዝብ ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እውነት ቢኖረው ኖሮ ጉዳዩን ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ያቀርበው ነበር፡፡ ነጥሎ ለሰሜን ጎንደር ሕዝብ ያቀረበበት ወይም ማቅረብ የፈለገው በተለያየ ምክንያት ማንኛውንም መንግስት ላይ የሚነሳ ተቃውሞ የሚደግፉ ጥቂት ሰዎች በዚያ አካባቢ አገኛለሁ በሚል ግምት ነው፡፡

ይህ ከመላው የሰሜን ጎንደር አካባቢ «ድንበር ተቆረሰ» በሚል የሰማያዊ ፓርቲ ውሸት ተነግሯቸው ለተቃውሞ ሰልፍ የተጠሩ ሁለት ሺ ያህል ሰዎች ጎንደር ከተማ ላይ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት በሰማያዊ ፓርቲ ውሸት ተደናግረው ሊሆን ቢችልም ሁኔታው ግን አሳፋሪ ነው ፡፡ ሁሉም የጎንደር ከተማ ሕዝብ ይህን እፍረት ይጋራል ማለት እንዳልሆነ ግን ሊታወቅ ይገባል። የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን መሰረተ ቢስ ውሸት ላይ በመመስረት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፉ እጅግ አዝኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲንም ታዘቦታል፡፡ ሕዝብ አነቃንቅበታለሁ ያለው ሰልፍ ህልውናውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን ተአማኒነትንም አሳጥቶታል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ «ድንበር ተቆረሰ» ብሎ በጎንደር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ከመጥራቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ አዲስ አበባ በሚገኘው ፅህፈት ቤቱ ውስጥ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን የሚመለከት የውውይት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ ከጀርባ ሆነው ሰማያዊ ፓርቲን ይመራሉ እየተባለ በውስጥ አዋቂ የሚነገርላቸው ፕ/ር መስፍን ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ በተጨባጭ ያለውን እውነት ከመናገር አልፈው «ድንበር ተቆርሶ ለሱዳን ተሰጥቷል» የሚል ቃል አልወጣቸውም፡፡

ፕ/ር መስፍን ቃል ያልወጣቸው ሕዝብ በመንግስት ላይ ይነሳል ብለው ስለፈሩ ለመጠንቀቅ አይመስለኝም። ከዚህ ቀደም የተከተሉት አካሄድ ሰላማዊነታቸውን የሚያመለክት አይደለም። ፕ/ር መስፍን «ሰማያዊ ፓርቲ ድንበር ተቆርሶ መሰጠቱን የሚያሳይ አንዳችም ማስረጃ አላቀረበም፣ እኔም ይህን የሚያሳይ ማስረጃ የለኝም» ብለው በይፋ የተናገሩት፣ የድንበር ጉዳይ በምስጢር ሊሰራ የማይችል የግንባር ላይ ስጋ በመሆኑ በቀናት ግዜ ውስጥ እውነቱ ይፋ ሆኖ የምሁርነት ካባቸውን የሚያስገፍፋቸው መሆኑን ስለሚያውቁ ሊሆን እንደሚችል ግን ብዙዎች ገምተዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ግን አማካሪው ፕ/ር መስፍን የለገሱትን እውነት እንኳን መቀበል አልፈለገም፡፡ ሁከት በመቀስቀስ ልክፍት ህሊናው ስለታወረ ነው መቀበል የከበደው፡፡ ጉዳዩ እውነት ይሁን ውሸት ለሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ቁም ነገር አይደለም፡፡ የእነርሱ ጉዳይ በውሸትም ቢሆን ሕዝብን መንግስት ላይ ማስነሳት ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብን በመንግስት ላይ ለማነሳሳት የተጠቀመበት ዘዴ በደጋፊዎቹ ዘንድ እንኳን ተቀባይነት አላስገኘለትም፡፡ ይህ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ሕዝብን የራሱን ዓላማ ለማሳካት እንደፈለገ የሚያሾረው መሳሪያ አድርጎ የሚመለከተው መሆኑን ያሳያል፡፡ ፓርቲው ሕዝብ የራሱ ፍላጎትና ጥቅም እንዳለው አካል (entity) የማይመለከት መሆኑንም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የሰማያዊ ፓርቲ አመለካከት ለሕዝብ ካለው ከፍተኛ ንቀት የመነጨ ነው።

የሰማያዊ ፓርቲ የበሬ ወለደ ወሬ የፈጠረው መደናገርና ጥርጣሬ ወደ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም ዘልቆ ገብቷል። ሆኖም ወደ አደባባይ አንጠልጥለው ከመሮጣቸው በፊት ፓርቲዎቹ ለጋራ ምክር ቤት አቀረቡት - ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ የሆነው ገዥው ፓርቲ ማብራሪያ እንዲሰጥበት፤ በዚሁ መሰረትም ገዥው ፓርቲ በጉዳዩ ላይ የተሟላ ማብራሪያ ሰጥቷል። ጉዳዩን ሳያጣሩ ጮሆ ለማስጮህ ከመሞከር ይልቅ ለውይይት በማቅረብ እውነቱን ለማወቅ የመፈለግ አካሄድ፣ ለአገር ከሚቆረቆር ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚጠበቅ በመሆኑ ተቃዋሚዎቹ ጉዳዩን ወደጋራ ምክር ቤት መውሰዳቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ማንኛውንም አገራዊ ጉዳይ ላይ በመመካከርና በመወያየት መግባባት እንደሚቻልም ያሳየ አሰራር ነው፡፡ በውይይቱ በኢህአዴግ ተወካይ በኩል የተሰነዘሩ ምላሾችም ነበሩ። አንድበአንድ እንጥቀሳቸው።

1‚ ከ1902 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮ ሱዳን ድንበር የመካለል ስምምነቶች የተፈፀሙ ቢሆንም፣ በተጨባጭ በመሬት ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ምልክቶች የማስቀመጥ ስራ ያልተተገበረ በመሆኑ ጉዳዩን ፈር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡

2‚ መሬት ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ድንበር የማካለል ስራ አስፈላጊ መሆኑን ኢህአዴግ ያምናል፡፡ ኢህአዴግ በድንበር መካለሉ የሚያምነው በዓለምአቀፍ ሕግ ተቀባይነት ያለው ደረጃውን የጠበቀ ወሰን መኖሩ፣ በአገሮች መካከል ለሚነሳ ግጭትና የሰላም እጦት መፍትሄ የሚያገኝበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ነው፡፡

3‚ አሁን መንግስት ድሮ የነበረን ስምምነት ወደኋላ በመተው አዲስ ስምምነት ውስጥ አልገባም። ይህን ማድረግም አይቻልም፣ ሕገወጥ ስለሆነ። ነገር ግን ተጀምረው ያልተቋጩ ጉዳዮች መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ኃላፊነት ስላለባቸው ይህ ነገር እልባት የሚያገኝበትን ሁኔታ በሁለቱ አገራት የጋራ የድንበር ኮሚሽንና የቴክኒክ ኮሚቴዎች አማካኝነት እየተከናወነ ያለ ስራ አለ፡፡

4‚ እስካሁን ባለበት ሁኔታ ስራው አላለቀም፡፡ ስራው አልቆ የኢትዮጵያ ድንበር ከዚህ በመለስ ነው፣ የሱዳን ድንበር ደግሞ ከዚህ በመለስ ነው የሚል ምንም አይነት ስምምነት አልተደረገም፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ አሉባልታዎቹ የመጡበት ምክንያት አለ፡፡ ይህም አገሪቱ የጀመረችው የሕዳሴ ጉዞ ያላስደሰታቸው አካላት ያደረጉት ነው በማለት ለጥያቄው ዝርዝር መልስ ሰጥተዋል።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment