Sunday, February 16, 2014

«መንግስት መሬት ቆርሶ የሚሰጥበት ምንም ምክንያት የለውም» - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

(Feb 16, (አዲስ አበባ))--«ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ልትሰጥ ነው» የሚል አስተያየት በብዛት ሲነገር ይደመጣል። በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያም ሰሞኑን ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ጥያቄ፦ ከኢትዮ- ሱዳን ድንበር ጋር በተያ ያዘ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል። ከዚ ህም አንዱ የኢትዮጵያና የሱዳን መሪዎች በቅርቡ በካርቱም ተገናኝተው የድንበር ውል ስምምነት ተፈራርመዋል የሚል ነው። በዕርግጥ ይህ መረጃ ትክክል ነው ወይ? ከሆነስ ለህዝቡ ለምን አልተገ ለፀም? ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ልትሰጥ እንደሆነ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ሲናገሩ ይደመጣል። በዚህ ላይ የመንግስት ምላሽ ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፦ የኢትዮጵ ያና የሱዳን መንግስታት በየሁለት ዓመቱ የምናደርገው የጋራ የኮሚሽን ስብሰባ አለን፡፡ ስብሰባው በሁለቱ መሪዎች አማካኝነት የሚሰበሰብ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ መደበኛ የሆነ የኮሚሽን ስብሰባ ነው ፡፡ ነገር ግን ይኼ ስብሰባ በቀጥታ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበርን ከማካለል ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ መደበኛ ስብሰባው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በአለም ዓቀፋዊና አህጉራዊ የሆኑ ጉዳዮችን አንስተን የምንወያይበት ነው፡፡ የጋራ ጉዳያችንን በምናይበት ጊዜ የድንበር ጉዳይ የኢህዴግ መንግስት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን ጋር በተወሰነ ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት የተፈጠረ ካልሆነ በስተቀር ሁሌም የሚካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ስብሰባ ስለድንበር ተነስቶ ተወያይተን የወሰድነው ነገር የለም ፡፡

የሆነ ሆኖ የዚህ ጉዳይ መነሻ ምንድነው? የሚለውን በአግባቡ መረዳት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እንደሚታ ወሰው በ2001ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበርን አስመልክቶ በወቅቱ ተነስቶ የነበረውን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት የድንበር ማካለሉ እንዳልተካሄደና ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ በዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ይህ ወቅት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት መሆኑ ልብ ይባል ፡፡ በ1996ዓ.ም ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቷል። ያኔም በወቅቱ መልስ ተሰጥቶበታል። አሁንም ቢሆን ምላሹ ተመሳሳይና አንድ ነው፡፡

ከታሪካዊ አመጣጡ ስንነሳ የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ያለው የኢህአዴግ መንግስት አዲስ ስምምነት የሚፈራረምበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ይህ ስምምነት በአጼ ምኒሊክ ዘመን የተፈረመ ስምምነት ነው ፡፡ ከዛ በመቀጠልም የዐፄ ኃይለስላሴ መንግስት በተመሳሳይ መንገድ አጥንቶ የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ የወሰነው ስራ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የደርግ መንግስትም የተፈረመውን ስምምነት ለማጣራት ሙከራ አድርጎ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰ ሮችንና በጉዳዩ ጥያቄ ያቀርቡ የነበሩትን ጨምሮ አሰማርቶ ስምምነቱ እንዲቀጥል የወሰነ መሆኑ ይታወሳል፡፡

አሁን የኢህአዴግ መንግስት ስምምነቱን የሚለው ጥበት ሂደት የለም ፡፡ ነገር ግን ከአምስት ዓመት በኋላ ይህ ጉዳይ ለምን ተነሳ? የሚለው ጥያቄ ነው ወሳኙ፡፡ ያው እንደተለመደው በየአምስት ዓመቱ ጉዳዩ ይነሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ስለሚካሄድ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንደሚታወሰው በ1996 ዓ.ም፣ በ2001ዓ.ም እንዲሁም አሁን በ2006 ዓ.ም ተነስቷል። ሆኖም ግን መልሱ አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ስምምነት የሚፈራረምበትና መሬት ቆርሶ የሚሰጥበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር በ1996ዓ.ም የግብጹ መሪ ላይ በሱዳን በኩል አልፈው በመጡ አሸባሪዎች ምክንያት የመግደል ሙከራ በመደረጉ ሱዳኖች አስተላልፈው ልከዋል በሚል ምክንያት በኢትዮጵያና በሱዳን መንግስት መካከል ግጭቶች ነበሩ፡፡ በዚህ ግጭት ወቅት በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ የነበሩ የሱዳን ኢንቨስተሮችና አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፡፡ በመፈናቀላቸው ምክንያትም ተጨማሪ መሬት ክፍት ሆኗል ይህ ተጨማሪ መሬት ክፍት በሚሆንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ኢንቨስተሮች፣ የውጭዎችን ጨምሮ አርሶ አደሮች ማረስ ጀምረዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ከዚህ በፊት ከነበሩ ስምምነቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገው ነገር ቢኖር አሁንም ቢሆን እዛ ቦታ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ባይነኩ አጠቃላይ የድንበር ማካለሉ እስኪያልቅ ድረስ በተስማማነው መሰረት ማንኛውም አርሶ አደር ከቦታው እንዳይፈናቀል የሚል ስምምነት አለን ፡፡ ይህንን ስምምነት የሱዳን መንግስትን ጠይቀን መግባባት ላይ ተደርሷል። የተደረገውም ለእኛ ተጨማሪ ነገር ነው እንጂ እኛ የምናጣው ወይም ያስረከብነው መሬት የለም፡፡

ስለዚህ ይሄ ጉዳይ ትክክለኛ መነሻ አለው ብለን አንወስድም፡፡ አሁን የተካለለ መሬት የለም፡፡ የተካለለ መሬት በሌለበት «ወደ እዛ ተሰጥቷል፤ ወደዚህ መጥቷል» የሚባልበት ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን እንዴት እንደሚካለል ከዓጼ ምኒሊክ ጀምሮ የተደረጉት ስምምነቶች መሬት ላይ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፡፡ ለዚህ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ስራቸውን አጠናቅቀው ያስረከቡበት ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም የድንበር ማካለሉ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ ከህዝቡ ጋር ተወያይቶ እንዴት መሬት ማስለካት ይቻላል? የሚለው ስራ ወደፊት ይጠብቀናል፡፡ ከዛ ውጪ አዲስ የተፈጠረ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩ በተደጋጋሚ የሚነሳበት የራሱ ምክንያት ያለው መሆኑ መታየት አለበት፡፡

የኢትዮጵያና የሱዳን ከፍተኛ ኮሚሽን ስብሰባ በሚካሄድባቸው ሁሉም ስብሰባዎች የድንበር ማካለልና የህዝብ ማስፈር ጉዳዮችን እንዴት እናድርግ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ኮሚቴው ስራውን ጨርሶ አቅርቧል? ወይስ አላቀረበም? የሚለው ጉዳይ ተነስቶም ይገመገ ማል፡፡ የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን አልጨ ረሰም፤ አጓትቷል። ስለዚህ ሥራውን እንዲሰራ ማድረግ ይገባል፤ ከሚል ስምምነት ውጪ ወደ ማካለል ደረጃ የተደረሰበት ሁኔታ የለም ፡፡

ጥያቄ፦ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የመልካም አስተዳደርና የውሃ ችግር ህብረተሰቡን እያማረረ ነው። ከምርጫ 97 በፊት ያለው ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል ብላችሁ አልሰጋችሁም? ነዋሪዎች ወደ ስራ ሲሄዱ ቢጫ ጄሪካን ይዘው ነው የሚወጡት። በመብራትም በኩል ሰው ሰራሽ የሆኑትን ችግሮች የሚፈጥሩት ተጠያቂ ሲሆኑና ሲቀጡ አይታዩም፤ በእርግጥ ተጠያቂነት አለ? የምትታለብ ላም የተባለው ቴሌም የሮሮ ላም እንዳትሆን የሚያሰጋበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ሰው ቢታመም አምቡላንስ እንኳ ለመጥራት አይቻልም። የጥገናና ሌሎች የአገልግሎት ስራዎች የሚሰሩት ህዝቡ በስፋት በሚጠቀምበት ወቅት ነው። ከህዝብ ጋር በመነጋገር የሚሰራበት አግባብ አይታይም። ይቅርታ እንኳ እየተጠየቀ አይደለም። የመብራቱ፣ ውሃና ቴሌው የተደራረበ ችግር ትልቅ መማረር ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ እንደ ምርጫ 97 በሚቀጥለው ምርጫ ህዝቡ ሊቀጣኝ ይችላል ብሎ አይሰጋም?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፦ ይሄንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ለህዝቡ እየገለፅን ነው የመጣነው። እኛ ጉዳዩ ከምርጫ ጋር መገናኘት አለበት ብለን አናምንም። ለምርጫ ብለንም አይደለም ይሄንን ነገር ማስተካከል ያለብን፤ ኃላፊነታችንና ስራችን ስለሆነ ነው የምንሰራው። ህዝቡ በሰጠን ድምፅ መሰረት አሁን ተመድበን የምንሰራው እኛ ነን። በተመደብንበት በዚሁ ወቅት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለንም ነው የምንወስደው። የነገ ምርጫ ምን ይሆናል በሚል ታሳቢ አይደለም የምንሰራው።

ለምርጫም ከሆነ አዲስ አበባ ላይ ሃያ አራት ሰዓት ውሃ የሚያገኘው የከተማው ክፍል 75 በመቶ ነው። አጠቃላይ ስዕሉን ካላየን በስተቀር የተሳሳተ ስዕል እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ነው። የሆነ አንድ ሰፈር ውሃ ስለታጣ አዲስ አበባ በሙሉ ውሃ ታጣ ማለት አይደለም። ሃያ አራት ሰዓት ውሃ ከሚያገኘው 75 በመቶ የከተማው ክፍል ውጪ 25 በመቶ የሚሆነው የከተማው ክፍል በተለያየ ደረጃ ውሃ እያገኘ ነው፤ እስከአስራ አምስት ቀን ውሃ የማያገኝ አንዳንድ ሰፈርም አለ። የት አካባቢ ውሃ እንዳለ፣ የት አካባቢ ውሃ እንደማያገኝ፣ የትኛው አካባቢ ደግሞ ምን ያህል ቀን ውሃ እንደሚያገኝ በካዳስተር ካርታ የተደገፈ መረጃ አለን። ይሄን መረጃ አስፈላጊ ከሆነ ከውሃና ፍሳሽ መስሪያ ቤት ማግኘት ይቻላል።

ሀያ አምስት በመቶ የሚሆነው የከተማው ህብረተሰብም ሃያ አራት ሰዓት ውሃ ማግኘት አለበት። ለዚህ ደግሞ የረጅም ጊዜ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን እየሰራን ነው። በቅርቡም ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡ አሉ። ይሄንን ማየት ይቻላል። ሰፋፊ የከርሰ ምድር ቁፋሮ ስራዎች ተጠናቀው ወደ ማገናኘቱ ስራ እየገባን ነው። ይሄንንም አድርገን የማናሟላቸው ክፍሎች አሉ። ለእነዚህ አካባቢዎችም የያዝነው አቅጣጫ አለ። የተለያዩ ማጠራቀሚያዎችን ገንብተን በቦቴ እየሞላን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ እየሰራን ነው።

ችግሩ አለ፤ ችግሩን ለመፍታት የጀመርነው መንገድም አለ። እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ ነው መሄድ ያለባቸው። ያኔ ነው ተስፋ የሚሰጥ ነገር የምናገኘው። አለበለዚያ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሆኖ ይመጣል። በእኔ እምነት ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። የያዝነውን አቅጣጫ ተከትለን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአግባቡ ከሰራን ይሄ አቅጣጫ ውጤት ያመ ጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ስለዚህ አቅጣጫ ውንም በአግባቡ መያዝ ይጠይቃል። ምን እየሆነ ነው የሚለውን ማየቱ ጥሩ ነው የሚመስለኝ።

ከመብራትም አንፃር ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ሮሮ እያሰማ ነው። በተደጋ ጋሚ እኔም ራሴ ይቅርታ እየጠየቅን የመጣንበት ሁኔታ አለ። ውሃና ፍሳሽ በሚያጋጥሙ ችግሮች ሁሉ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል። ህብረተሰቡ ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርግም መረጃ ሲሰጥ ነበር። ይሄንን በማድረግ የህዝብ ግንኙነት ስራ እየሰራ የሄደበት ሁኔታ አለ። ይሄ በቂ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ማየት እንችላለን። ከዚያ ባሻገር ግን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሚሰ ራቸው ስራዎች በሂደት ሮሮውን ሊቀንሱ ይችላሉ የሚል እምነት ነው ያለን።

ከመብራት ጋር ያለ ውን በተመለከተ የመብራት ችግር ሁለት አይነት ነው። የመነጨውን ሀብት በአግ ባቡ ለማሰራጨት የሚያስ ችል መሰረተ ልማቱ ካልተ ገነባ በስተቀር ልንቀይረው የማንችለው ነው። ይሄ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ትልልቅ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ነው። እነዚሁ ትልልቅ ፋብሪካዎች በሚገነቡበት ጊዜ መሰረተ ልማቱና የኃይል ማሰራጫው መሰረተ ልማት ይሄንን መሸከም የሚችል ሆኖ አልተገነባም። ስለዚህ ያንን የኃይል ማሰራጫ ሳይቀየር ምንም ማድረግ አይቻልም። ይሄንን ማሰራጫ መቀየር አለብን ብለን አንድ በአንድ ለቅመን አስቀምጠን ከሚመለከታቸው ኩባንያዎች ጋር እየሰራን ነው።

ሁለተኛው በተቋሙ በራሱ ውስጥ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች በተመሳሳይ አመለካከትና ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎቻችን ይፈቱታል ብለን አላመንም። ስለዚህ ሪፎርሙን ለውጪ ኩባንያ እንስጥና ከውስጥ ያለውን ችግር አይቶና ለይቶ ይፍታው የሚል አቅጣጫ ይዘናል። በዚህ መሰረት በቅርቡ እንደሚታወቀው የህንድ ኩባንያ አስገብተን ስራ ከጀመረ ሁለት ወር ሆኖታል። በዚሁ መሰረት አዲስ መዋቅር ተዘርግቶ የህንዱ ኩባንያ የአገልግሎቱን መስክ፤ ከተቋሙ የተገነጠለው ሌላው አካል ደግሞ የማመንጨቱንና የማሰራጨት ስራውን እንዲይዝ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በአንድ መዋቅር ይሄንን ትልቅ አገር ማገልገል አይችልም በሚል ነው ይሄ የሆነው። ስለዚህ ሪፎርሙ በሁለት እንዲከፈል በማድረግ ዋናው ችግር ያለበትን አገልግሎት የሚሰጠውን የህንድ ኩባንያ እንዲይዘው ተደርጓል። በዚህ ምክንያት እነዚህ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች ወደ ዘመናዊነት ስለሚሸጋገሩ ሊስተካከል ይችላል። ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት። ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የተያዙ መንገዶችም ስላሉ ችግሩ ይቃለላል። ከህዝብ ጋርም የምክክር መድረኮች ስላሉ ችግሮቹን እየፈታን እንሄዳለን።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ 

Related topics:
ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት መልስ    

No comments:

Post a Comment