Saturday, November 16, 2013

ለብራዚል-የ90 ደቂቃ ርቀት

(Nov 16, 2013, (አዲስ አበባ))--መነሻ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ከጠዋቱ 12ሰዓት፤ 62 ደጋፊዎች፣ 30 ተጫዋቾች፣12 ደግሞ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑን አመራር ጨምሮ፣ በድምሩ 102 የልዑካን ቡድን አባላት በአንድ አውሮፕላን፤ መድረሻ ናይጄሪያ ካላባር ቻናል ቪው ሆቴል....።

ሁሉም የልዑካን ቡድኑ አባላት በልባቸው የያዙት የ90 ደቂቃውን ጨዋታ የማሸነፍ ብቃትና ወኔ እንዲሁም ስፖርት ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ስንቃቸው አድርገዋል። ማራኪ ጨዋታና ከሁለት በላይ ግቦች እንደሚያስፈልጋቸውም ያውቁታል።

ይህ ጉዞ ኢትዮጵያን በእግር ኳስ ለዓለም ሊያስተዋውቁ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ያቀኑትን የዋሊያዎቹን መነሻና መድረሻ ይጠቁማል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀ መሪያ ጊዜ ከአቡጃ 700ኪሎ ሜትር ወደምት ርቀዋ የወደብ ከተማ ካላባር በቻርተርድ አውሮፕላን (በአንድ ላይ) 102 ባላደራ አባላትን ይዞ የሄደው ከትናንት በስቲያ ነው። ለ90 ደቂቃው የሰላም ጦርነት የቀሩትም ሰዓታት ብቻ ናቸው።

የሚቀረው ነገር ከሁለቱ አገሮች ማን ወደ 2014ቱ የብራዚል ዓለም ዋንጫ ያመራል? የሚለው ሲሆን፤ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የዛሬውን ምሽት መጠበቅ ግድ ይላል። ዋሊያዎቹም ናይጄሪያ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ ካላባር ከደረሰ በኋላ የመጀመሪያ ልምምዱን በካላባር ዩኒቨርሲቲ ሜዳ እንዲሁም ትናንት ጨዋታው በሚካሄድበት በዩጄ ኢሱይን ስታዲየም ልምምዱን በተሳካ ሁኔታ ሰርቷል።

ከቡድኑ ጋር የተጓዙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንደገለጹልን ፤ ዋሊያዎቹ ያደረጉት የመጀመሪያና የመጨረሻ ልምምድ ለጨዋታው በደንብ መዘጋጀታቸውንና በቋሚ አሰላለፍ የሚገቡትን በመጠኑ ም ቢሆን የጠቆመ ነበር። በእዚህም መሰረት ጌታነህ ከበደ በሙሉ ጤንነት ላይ ስለሚገኝ ከሳላዲን (ሳላ) ጋር ሊጣመር እንደሚችል ተገምቷል።

አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውም ለናይጄሪና ለሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፤ «ጨዋታውን አሸንፈን ወደ ብራዚል የመግባት ዕድል አለን» ብለዋል። በዩጄ ኢሱይን ስታዲየም አዲስ አበባ ላይ የነበረው ማራኪ ጨዋታ ዳግም ከማሳየት በተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የዋሊያዎቹ አባላት በካላባር የተለያዩ ጎዳናዎች በመኪና ሲጓዙ ከደጋፊዎች ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸው በሥፍራው የሚገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከቡድኑ ጋር ወደ ካላባር ከተጓዙት 60 ደጋፊዎች ሌላም በርካታ ኢትዮጵያውያን በዩጄ ኢሱይን ስታዲየም ተገኝተው ማራኪ ጨዋታ ከውጤት ጋር ለዓለም ህዝብ ለማሳየት ከተዘጋጀው ቡድናቸው ጎን ለመቆም መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

መላው ኢትዮጵያዊ ሙሉ ትኩረቱ በዛሬው ጨዋታ ላይ ነው። ከቤተሰብ ፣ከጓደኛ፣ከሥራ ባልደረባና ከማንም ጋር የሚደረግ ውይይት ሁሉ እንደ ድሮው ስለ ማንቸስተር፣አርሰናል ወይም ባርሴሎና አይደለም ፤ ይልቁንም «ስለ አፍሪካ ባርሴሎናዎች» እንጂ።

ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ« የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ዓመታት ትልቅ ክስተት አስመዝግቧል ፤ወደ መሰረቱት የአፍሪካ ዋንጫም መመለስ ችለዋል» በማለት የዋሊያዎቹን ጥንካሬና ውጤታማነት እየገለጸ ነው። ለዋሊያዎቹና ለኢትዮጵያውያን ግን የፊፋ አድናቆት ብቻ በቂያቸው አይመስልም፤ ይልቁንም በማራኪው ጨዋታ ግቦችን ማስቆጠርና ለብራዚል ጉዞ ፓስ ፖርት መቁረጥ። ጨዋታው በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገውም ሁለቱም (ዋሊያዎቹና ንስሮቹ) ማለፍ የሚችሉበትን ዕድል የሚወስኑት እራሳቸው ናቸው።

በርካታ ናይጄሪያውያን በቡድናቸው ዕምነት መጣላቸውን የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያም ተአምር ልትሰራ እንደምትችል የናይጄሪያው ዴይሊ ስታር በዘገባው አስፍሯል። እንዲያውም ዴይሊ ስታር ከናይጄሪያውያን ሰበሰብኩት ባለው ድምጽ በርካቶቹ ዋሊያዎቹ «ሊያልፉ ይችላሉ» በማለት አስነብቧል።

በዩጄ ኢሱይን ስታዲየም የሚካሄደውና በጉጉት የሚጠበቀው የዋሊያዎቹና የንስሮቹ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት የ34 ዓመት ጋምቢያዊው ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ በሚያሰሙት ፊሽካ የምዕራፍ ሁለቱ የሜዳ ላይ ፍልሚያ ይጀመራል።

ከዋና ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ ጋር ኤርትራዊው አንገሶም ኡቅባ ማርያም የመጀመሪያ ረዳት ዳኛ፣ በሩዋንዳዊው ፌሊሰን ካባንዳ የተተኩት ኬንያዊው አደን ማራዋ ራንጄ ሌላው ረዳት ዳኛ ሲሆኑ፤ ማውዶ ጃሎው ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንደሚመሩት ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) አስታውቋል።

ከካላባር የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ጨዋታው ምሽት 12 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን ሱፐር ስፖርት፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ኤፍ ኤም አዲስ 97.1፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎትና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቀጥታ እንደሚያስተላልፉት ተገልጿል።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ዋሊያዎቹ ከብራዚል ጫፍ የቀራቸውን የ90ደቂቃ ርቀት በድል ይወጡ ዘንድ መልካም ድጋፉንና ምኞቱን ይገልጻል። መልካም ዕድል!!!
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment