Wednesday, August 28, 2013

የኃይማኖት ተቋማት የሠላም የጋራ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

(ነሐሴ 21/2005, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት የሠላም የጋራ ጉባዔ ዛሬ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መካሄድ ጀመረ። ጉባዔው "የኃይማኖቶች አብሮነት እሴት በማጎልበት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጉባዔውን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት የአገሪቷ መገለጫና ኩራት ናቸው ብለዋል። ኢትዮጵያ ድንቅ የመቻቻል ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ኃይማኖቶች በአገሪቱ አንድነትና መቻቻል እንዲጎለብት፣ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲዳብር የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት መንፈስ ለመግታት የኃይማኖት ተቋማት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። አክራሪነትና ሽብርተኝነት በአገር ገጽታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም ባሻገር የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ትግል የሚያደናቅፍና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን የሚሸረሽር በመሆኑ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል ብለዋል።

በአገሪቱ ለዘመናት የቆየውን የሠላምና የመቻቻል ባህል የሚያደፈርሱ፣ ሕገ-መንግሥቱን በሚፃረር መልኩ በፀረ-ሠላም እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን መንግሥት ሕግን መሠረት ያደረገ እርምጃ ለመወሰድ የሚገደድ መሆኑንም አስታውቀዋል። የፀረ-ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ የሚደግፉ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም አሳስበዋል። የፀረ-ሠላም ኃይሎችን ድርጊት ለማከሸፍ ሕዝብና መንግሥት እጅ ለእጅ ተያይዘው የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ጉባዔው በአገሪቱ ለዘመናት የቆየውን የኃይማኖቶች ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴት ወደ ዘላቂ ልማት፣ ሠላምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማሸጋገር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ ሼህ ኪያር መሐመድ አማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኃይማኖት ተቋማት የሠላም አምባሳደር በመሆን በጋራ ለሠላም ይሰራሉ።

ኢትዮጵያ ሁሉም ኃይማኖቶች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር እንደመሆኗ መጠን ይህን የመቻቻል ባህል ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ በበኩላቸው አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር የማይጣጣሙና ብዝሃነትን፣ የእምነት ነፃነትን እንዲሁም እኩልነትን የማይቀበሉና ከኃይማኖታዊ አስተምህሮት ጋራ አብሮ የማይሄዱ በመሆናቸው ሊወገዙ ይገባል ብለዋል። ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከሁሉም ኃይማኖቶች የተውጣጡ 2 ሺህ 500 ተሳታፊዎች ተካፋይ ሆነዋል።
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment