Friday, July 12, 2013

የመብራት ኃይል የመሃል ሜዳ ተጫዋች የሆነው አስራት መገርሳ ወደ እስራኤል ክለብ መዛወሩ እውን ሆነ

(July 12, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የመብራት ኃይል የመሃል ሜዳ ተጫዋች የሆነው አስራት መገርሳ ወደ እስራኤል ክለብ ማቅናቱን አረጋግጧል፡፡ ቀደም ሲል በርካታ የዋልያዎቹ አባላት ወደ ተለያዩ የውጭ አገር ክለቦች መዘዋወራቸውን ተከትሎ አስራት ወደ ሱዳን ክለቦች እንደሚያመራ ቢነገርም ተጫዋቹ ወደ እስራኤል ማቅናትን መርጧል፡፡

አስራት የተዛወረበት የእስራኤል ክለብ ሃፖኢል ኢሮኒ ኒር ራማት ሻሮን የተባለ እግር ኳስ ክለብ ነው፡፡ ይህ ክለብ በእስራኤል ያለፈው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ አስራ አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ አስራትን የሦስት ዓመት ኮንትራት ያስፈረመው ሲሆን፣ ከስምንት ሺ የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ወርሀዊ ደመወዝ ሊከፍለውም ተስማምቷል፡፡

በመብራት ኃይል እግር ኳስ ክለብና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በአማካይ ስፍራ ላይ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው አስራት በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከማናያቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

አስራት ወደ እስራኤል ክለብ ሊያመራ የቻለው በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ በተለይም ከአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ እስከ ብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወሳኝ ሚና በመጫወት ከቋሚ ተሰላፊዎች አንዱ መሆን በመቻሉና በሚጫወትበት ቦታ ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

አስራት ባለፈው ወር ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በሜዳቸው አስተናግደው ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ለቡድኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በዚህ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከደቡብ አፍሪካው ያለፈው ወር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወዲህ በርካታ የዋልያዎቹ አባላት ወደ ተለያዩ ውጭ ክለቦች እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ ሊቢያው አልሂታድ ክለብ ያቀናው የቅዱስ ጊዮርጊሱ የጨዋታ አቀጣጣይ ሽመልስ በቀለ አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ግብ አግቢው የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ፣ ምንያህል ተሾመ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ዳዊት ፍቃዱና በኃይሉ አሰፋን የመሳሰሉ የዋልያዎቹ አባላት ባለፈው ሳምንት ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ሊቢያ፣ ሱዳንና እስራኤል ክለቦች የተዛወሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment