Wednesday, July 10, 2013

40 ሚሊዮን ብር ያጭበረበረ ግለሰብ ተያዘ

(July 10, 2013, (አዲስ አበባ))--ከሰባት አመት በፊት ከባንክ ገንዘብ አጭበርብሮ ከሀገር የተሰወረው ግለሰብ በአለም አቀፉ የፖሊስ ድረጀት /ኢንተር ፖል/ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትብብር በየመን ሰንአ ተይዞ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ አቶ አስመላሸ ሀድሽ የተባለው ግለሰብ ከንብ እና ከወጋገን ባንክ አስከ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመበደርያነት ያስያዘውን ንብረት ሽጦ ከአገር ተሰውሯል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የብሔራዊ ኢንተርፖል  ኃላፊ ኮማንደር ግርማይ ካህሳይ ግለሰቡ በተጠረጠረበት ወንጀል ከሰባት አመት በላይ ሲፈለግ ቆይቷል፡፡ ግለሰቡ በየመን መንግስት ትብብር ሰንአ መደበቁ ከተገለፀ በኋላም በአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትብብር በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ሀገር እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተደራጁ ወንጀሎች ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ሞኒ መንገሻ በበኩላቸው የተጠርጣሪው የምርመራ ሂደት በቀጣይ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኮማንደር ሞኒ የምርመራ ክፍሉ ከዚህ በፊት ባካሄደው የምርመራ ሂደትም የወንጀሉ ተባባሪ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ የሚያካሂዱት ወንጀልን የመከላከል ተግባር ወንጀልን ፈፅሞ ከሀገር ለመጥፋት ለሚሞክሩ ግለሰቦች ማምለጥ እንደማይቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የፌዴራል ፖሊስ እና የአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ በጥምረት ባካሄዱት ወንጀልን የመከላከል ስራ ወንጀል ፈፅመው በጀርመንና በደቡበ ሱዳን ተሸሽገው የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment