Saturday, June 22, 2013

የግብፅ አቋም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕይታ

(Jun 22, 2013, (አዲስ አበባ))--የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት «የአባይን ወንዝ በፍትሐዊነት እንጠቀም» የሚለውን ሃሳብ ለመቀበል ተቸግረው መላው ጠፍቷቸዋል፡፡ አገራቸውን ትዝብት ላይ የሚጥል አቋም እያንፀባረቁ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆምም እየሞገቱ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ካልሆነም የበኩላቸውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ካላቆመች በግብፅ በኩል ሊወሰዱ ከታሰቡት አማራጭ ስልቶች «በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መደገፍ »የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ በእዚህም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ግንባታውን ለማስቆም እንደሚሞክሩ ነው ባለሥልጣናቱ ያስታወቁት፡፡

በእዚህ ጉዳይ ዙሪያ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አነጋግረናል፡፡ «የግብፅ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደ ባንዳ ለመጠቀም ማሰባቸውንም እናወግዛለን» በማለት አስተያየታቸውን የሚጀምሩት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው፡፡ በግብፅ ባለሥልጣናት በኩል እየተገለጸ ያለው ነገር በምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌለውና የተሳሳተ ጎዳና ነው፡፡ ፓርቲው ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ይታገላል፡፡ በመሆኑም በአገር ሉዓላዊነትና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚመጣን ማንኛውንም አካሄድ ይቃወማሉ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማንነት መገለጫና የአገር አለኝታ ነው፡፡ ፓርቲው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ በእዚህም እስከ አሁን ድረስ የበኩሉን አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል፤ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ «የግብፅ መንግሥት በአንድ ሉዓላዊ አገር ላይ የራሱን ፍላጎት መጫን አይችልም፡፡ የዓለም አቀፍ ሕጎችም የእዚህ ዓይነቱን አካሄድ አይፈቅዱም፡፡በቅኝ አገዛዝ ዘመን በተፈፀመው ፍርደ ገምድል ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በታደለችው ሀብት ላይ ግብፅ ‹እኔ ነኝ ወሳኟ ›ብላ መነሳቷ ተገቢ አይደለም» ብለዋል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብም አይደለም፡፡

አቶ አየለ እንደሚናገሩት፤ የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ ሀብት ነው፡፡ የግብፅ ሕዝቦችም ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ችግራቸው ችግራችን ነው፡፡ ስለሆነም አባይን በፍትሐዊነት በጋራ መጠቀም ይገባል፡፡ ይህን መንገድ በመከተል መጓዝና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እየተከተለው ያለው አቅጣጫ ትክክለኛ መሆኑን ፓርቲው ያረጋግጣል፡፡ ግብፅ አቋሟን መፈተሽ አለባት፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በአገር ሉዓላዊነትና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚሰነዘረውን ማንኛውንም ሁኔታ አይቀበልም፡፡

የኢትዮጵያን ልማት ለማጥፋት፣ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ፣ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበትን የህዳሴ ግድብ ለማስቆም የሚንቀሳቀሰውን አካል ፓርቲው አውግዟል፡፡ ይህንንም በፅናት ይታገላል፡፡ በአገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፈታ ጉዳይ እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ የሚያስረዱት፡፡ በአገር ጉዳይም ግንባር ይፈጥራሉ ባይ ናቸው፡፡ ትውልዱም ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን ኢትዮጵያውያን በአንድነት «ሆ»ብለው ተነስተው ልማቱን እያፋጠኑት ነው፡፡ በግብፅ በኩል ይህን ለማስቆም የሚደረገው እንቅስቃሴ ቦታ የለውም፡፡

«በአገር ጉዳይ ከሕዝብ ጎን ተሰልፈን፤ ግንባር ቀደም ሆነን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘግጅተናል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት ያረጀና ያፈጀ ታሪክ በማንሳት የሚያደርጉትን ሩጫ ትተው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር በመመካከርና በመተባበር በጋራ ለመጠቀም ቢሠሩ ይሻላል፡፡ የግብፅ መንግሥትም ቆም ብሎ ማየት አለበት፡፡ ግብፅ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጉዳዩን በደንብ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡ ለውስጥ ችግራቸው መፍትሔ ቢያፈላልጉ ይሻላል»ሲሉም ያስገንዝባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ የሚናፈሱት ወቅታዊ ትኩሳትና ዜናዎች የሚጠበቁ እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ተቃውሞው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በቀጣይም ከእዚህ የበለጠ ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የግድቡ ግንባታ ተጠናክሮ ግድቡ ውሃ መቋጠር ሲጀምር ተቃውሞው ሊበረታ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በመሆኑም ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ማድረግና መጠናከር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለበት፡፡

ግብፅ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ማሰቧ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለግብፆች መሣሪያ ይሆናሉ የሚል እምነት የላቸውም፡፡ «ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በተያያዘ ከገዢው ፓርቲ ባልተናነሰ ምናልባትም በተሻለ ደረጃ የምንጥር ነን፡፡ የቤታችንን ችግር በቤታችን ከመወቃቀስና ከመተቻቸት ውጪ በአገር ህልውናና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ከመከላከል ወደ ኋላ አንልም፡፡ ይህ ደግሞ ከአያት አባቶቻችን የወረስነው ነው »ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡

የግብፅ የሕዝብ ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ቡድኑ ከሚገባው በላይ መረጃዎችን እንዲያገኝ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ተሻለ ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ለአሁኑ የግብፅ ተቃውሞ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ «…ለልዑካን ቡድኑ ካኒቴራችንን ከፍተን ነው ያሳየነው፡፡ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የማይፈቀዱ ቦታዎች ሁሉ ለእነርሱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ብዙ መረጃዎችን እንዲመለከቱና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ከሚፈቀደው በላይ (ለክቶ ከመስጠት ውጪ)መሰጠት አልነበረበትም፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም ለግብፆች እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ እነዚህ መረጃዎችና ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ በአገር ደህንነትና በሕዝብ ጥቅም ላይ አይዘምቱም አይባልም» በማለትም በመንግሥት በኩል ክፍተት መፈጠሩን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ግብፅ ቢሄድ ግብፆች ለክተው እንጂ ጓዳቸውን ከፍተው እንደማያሳዩም ነው ያመለከቱት፡፡

ይህ አጋጣሚ እንደምክንያት ተይዞ ወደ ብሔራዊ መግባባት ቢመጣ የተሻለ ነው፡፡ በእዚህም በአንድ ዓላማ የአንድ ቤት ጣሪያን ለመሥራት መረባረብ ይገባል፡፡ ለእዚህም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አቶ ተሻለ ያሳስባሉ፡፡

«በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ያነሰ የሀገር ፍቅር ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ፓርቲዎቹ ዓይነታቸው ብዙ ነው፡፡ አገሪቷም ብዙ ቀዳዳ አለባት»የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን እነዚህን ቀዳዳዎች የሚጠቀሙ የውጭ ኃይሎች ፤እንዲሁም ለራሳቸው ጥቅም እዚህ ውስጥ የሚገቡ አካላት አይኖሩም ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ነው ያስገነዘቡት፡፡

ፓርቲያቸው የውጭ ኃይል ለመጠቀም ሃሳቡም ፍላጎቱም እንደሌለው በአፅንዖት ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ አባይን ጨምሮ ሌሎች የውሃ ሀብቶቿን የመጠቀም መብት እንዳላትም ያምናል፡፡ ይህንንም ከኢህአዴግ በፊት በፕሮግራም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ዶክተር መረራ ያስታውሳሉ፡፡ ፓርቲያቸው «ግድቡ በዜሮ በጀት መጀመር አልነበረበትም፤ ሱዳን አፍንጫ ሥር ሄዶ መገንባቱም ለጥቃት ያጋልጣል፤ አንድ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ከመገንባት ይልቅ ሌሎች ብዙ ወንዞችን በመጠቀም 10 የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ይሻላል »የሚል አቋም ያንሸራሽር ነበር፡፡

«ኢህአዴግ የውጭ ኃይሎችን ተጠቅሞ አገር እንደሚገዛ ሁሉ በውጭ ሆነው በተለይም የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ተቃዋሚዎች በእዚህ አጋጣሚ አይጠቀሙም ብሎ መከራከር ያስቸግራል፡፡ በትጥቅ ትግልና በሌላ መንገድ የተሰማሩ (በሶማሊያ፣ በሱዳንና በሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ) ኃይሎች ይህን አጋጣሚ አይጠቀሙም ብሎ መከራከር አስቸጋሪ ነው፡፡ወደ ውጭ የሚያይ አካል የለም ብሎ መከራከርም የፖለቲካ የዋህነት ነው የሚሆነው»ያሉት ሊቀመንበሩ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የአረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ገብሩ አስራት በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ውስጥ ከተቀመ ጡት ሁለት ነገሮች አንዱ የአባይ ወንዝ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አባይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ወንዝ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ወንዙን የመጠቀም ሙሉ መብት አላት፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለመስኖ ልማትም ወንዙን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት አላት፡፡ የግብፅ ባለሥልጣኖች አስተሳሰብ ከአገር ጥቅም አንፃር ሲታይ ጎጂ ነው፡፡ በጦር መሣሪያ የሚፈታ ነገርም አይኖርም፤ አይችሉምም፡፡ እነርሱ ይፎክራሉ፤ ይደነፋሉ፡፡ በአገር ሉዓላዊ ጥቅም ላይ እንዲህ ማለታቸውም ትክክል አይደለም፡፡

«ልማትን ለማደናቀፍ የሚመጣን አካል ፓርቲያችን ከኢህአዴግም በላይ ነው የሚቃወመው፡፡ በአገር ሉዓላዊነት ላይ በፍፁም አንደራደርም፡፡ ፓርቲያችን በሕጋዊነት የሚንቀሳቀስ፤ በሠላማዊ መንገድ የሚሠራ፤ ከዚያም በላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ የቆምን ነን፡፡ አንድ አገር በገንዘብና በሌላ ነገር የሚገዛን አይደለንም፤ሊሆንም አይችልም፡፡ በገንዘብ ኃይል የሚገዛንም የለም፡፡ ማንኛውም ለእዚህች አገር አስባለሁ የሚል ፓርቲ የአገርን ጥቅምና ሉዓላዊነት ለሌላ አሳልፎ ከሰጠ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አይደለም»የሚል አቋም አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) የግድቡ የሕዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ ለግድቡ ግንባታ ዕውን መሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ግድቡ የሚገነባበት ቦታ ድረስ በመሄድም ጎብኝቷል፡፡ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሙሼ ሰሙ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተራራቀ አመለካከት የላቸውም ይላሉ፡፡ አብዛኛው ፓርቲ ለግድቡ ግንባታ ስኬት ድጋፍ ያደርጋል፡፡

አቶ ሙሼ እንደሚሉት የግብፅ ባለሥልጣናት የሰነዘሩት ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሚና አሳስቧቸው፤ የሕዝቡ የዴሞክራሲ ጥያቄ ለእነርሱ ጆሮ የሚደመጥ ሆኖ ችግሩን ለመፍታት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ሳይሆን እነርሱ በአባይ ግድብ ላይ የሚኖራቸውን ጥቅም ለማስከበር ያለመ ነው፡፡

የግብፆች ሃሳብ በኢዴፓ በኩል ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህን መሰሉ የግብፆችን ተራና እዚህ ግባ የማይባል ሃሳብን የሚቀበል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ይኖራል ብለውም አያምኑም፡፡ ተራ አሉባልታና አጉራ ዘለል አመለካከት ነው፡፡ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በሕዝብና በመንግሥት መካከል ክፍተት ለመፍጠር የሚደረግ ሴራ ከመሆን ያለፈ ፋይዳም የለውም፡፡ በእዚህም የራሳቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ ነው የሚጥሩት፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናትና ተቃዋሚዎችን የፖለቲካ ግንዛቤ ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ጦርነት እናነሳለን የሚለው አሉባልታም ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ነው፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment