Monday, May 27, 2013

ጊዜው የአፍሪካ ነው

(May 27, 2013, (አዲስ አበባ))--ታላቁ የሚሌኒየም አዳራሽ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበትን፣ ሕዝቦቿ የነፃነትን አየር በጋራ የተነፈሱበትንና አንድነታቸውን የመሠረቱበትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ የአፍሪካ ኅብረት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ከመላው ዓለም በመጡ በርካታ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ የበርካታ ሀገራት መሪዎች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን ይህን ታላቅ በዓል ለመዘገብ የመጡ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ቦታቸውን ይዘዋል፡፡

እንግዶቹ በከበሮ ታጅቦ እየቀረበ ባለው ህብረ ዝማሬ ተማርከዋል፡፡ አህጉሪቱ ከባሪያ ንግድ እስከ ቅኝ ግዛት፣ ከእዚያም ነፃ እስከወጣችበት ጊዜ ድረስ ያሳለፈቻቸውን ውጣውረዶች የሚተርኩበት ሙዚቃዊ ድራማ እንዲሁም በጥበባዊ ለዛ መርሐ ግብሩን የሚያስተዋውቁት የመድረክ መሪዎችም ለሥነሥርዓቱ መድመቅ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርገዋል። መድረኩ ከ50 ዓመታት በኋላ ኅብረቱ አንድ መቶኛ የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር አህጉሪቱን የበለጸገችና ሙሉ ሰላም የሰፈነባት ለማድረግም ቃል ኪዳን የታደሰበት ነው።

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ «ዛሬ ለአፍሪካውያን ልዩ ቀን ነው» በማለት ነው የበዓሉን መጀመር ያበሰሩት፡፡ ይህንም ታላቅ የደስታ ቀን ሁሉም የአፍሪካ ወዳጆች እንደሚጋሩትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

«እዚህ የደረስነው በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈን ነው» ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ኅብረቱ በተመሠረተባቸው ጊዜያት የነበሩት የአህጉሪቱ ብርቅዬ ልጆች በርካታ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠውና አልፈው ለአሁኑ ትውልድ ማስረከባቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ኅብረቱ እንደአሁኑ ባልተጠናከረበት ዘመን የነበሩ በርካታ ዜጎችም በቅኝ ገዥዎች ጫና በከፋ ድህነት እና በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ማለፋቸውን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው እያደገና እየተለወጠ ቢመጣም አፍሪካውያን ዛሬም ድረስ ያልፈቷቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው። በተለይም የዜጎችን ሕይወት የሚቀይር ልማትን በማምጣት ረገድ አገራት ሊሠሯቸው የሚገባቸው በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉባቸው ነው ያረጋገጡት።

«ይህን ታሪክ የምንቀይርበት ጊዜ አሁን ነው» የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኅብረቱ ስብሰባ ዋና ዓላማ የአህገሩቱን ህዳሴ ዕውን ለማድረግ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንደሆነም ነው የሚያስረዱት። አህጉሪቱን እ.ኤ.አ በ2020 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት የኅብረቱ አባል ሀገራት ከምን ጊዜም በላይ ትብብራቸውን ማጠናከር አለባቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የአህጉሪቱን ህዳሴ ዕውን ለማድረግ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ግጭቶችን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ትግል እስከ ፓን አፍሪካኒዝም፣ ቀጥሎም ከ50ዓመታት በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት እስከአደረጉት ትግል ያለውን ሂደት ቃኝተዋል።

አፍሪካውያን በፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ላይ ያደረጉትን ትብብር ያደነቁት ሊቀመንበሯ፤ ለነፃነት በተደረገ ትግል በሌሎች ክፍለ አህጉራት የሚገኙ ሕዝቦች ያደረጉት ድጋፍ ቀላል እንዳልነበርም ነው የሚያስ ገነዝቡት። «እናም ከሁሉም ወዳጆቻችን ጋር ሆነን 50ኛውን የምሥረታ በዓላችንን ስናከብር ደስታ ይሰማናል» ሲሉም ነው የሚናገሩት ።

እንደ ዶክተር ዙማ ገለጻ፤ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ግጭቶችን በመፍታት የአፍሪካን ክብር ማስጠበቅ ይገባል። ይህንን ዕውን ለማድረግ በሁሉም የሥራ ዘርፎች በጥናትና ምርምር የታገዙ ሥራዎች ማከናወን እንዲሁም የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማስፋፋት የአህጉሪቱን ሕዝቦች ማስተሳሰርም ያስፈልጋል።

አፍሪካ ለግብርና ዕድገት ትኩረት መስጠትና የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም መሥራት ይገባታል። ለሣይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሥራዎች ናቸው። «በአፍሪካዊነታችን መኩራት አለብን፤ ጊዜውም የአፍሪካ ነው» በማለትም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት የልማት ትብብር (ኢጋድ) በመወከል ንግግር ያደረጉት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው ኢጋድ በአካባቢው ሰላም፤ መረጋጋትና ልማትን በማምጣት የኅብረቱን ራዕይ ለመተግበር እየሠራ ነው። በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀችው ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ትልቅ ድጋፍ ማድረጓንም ሳይገልጹ አላለፉም።

እንደ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጻ፤ በአካባቢው ከእዚህ በፊት ይታዩ የነበሩትን ያለመረጋጋት ችግሮች በመፈታት ረገድ ኢጋድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው። በሶማሊያና በሁለቱም ሱዳኖች የነበሩት ችግሮች በመፈታት ላይ ናቸው።

የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች የነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር ሚስተር ጆን ጋራንግ የሱዳን ችግር በሰላም እንዲፈታ የተጫወቱትን ሚና አድንቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድመው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአካባቢው ሰላም በማስፈን ረገድ ለተመዘገበው ስኬት ሚናቸው ትልቅ እንደነበርም ነው የተናገሩት።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment