Monday, May 27, 2013

የግብፅ ፕሬዚዳንት «አገራቸው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብላ አታምንም» አሉ

(May 27, 2013, (አዲስ አበባ))--የግብፅ መንግሥት «ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እያስገነባች ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት የለውም» ሲሉ የግብፅ ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

የግብፅ ፕሬዚዳንት ሚስተር መሐመድ ሙርሲዳ ከትናንት በስቲያ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳመለከቱት፤ መንግሥታቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በግብፅ ሕዝብ ላይ ጫና ያሳድራል የሚል እምነት የለውም። ከእዚህ ባሻገር የግድቡ ግንባታ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል።

መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ለማግኘት ፍላጎት እንዳለው ፕሬዚዳንቱ አመል ክተው፤ ለግድቡ እውን መሆን የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩልም ሀገራችን ከኢትዮጵያ ጋር የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር የምትፈልግ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የሥጋ ምርትና ቡና ከእዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መውሰድ የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምትገነባቸው በየትኞቹም ግድቦች ግብፅንም ሆነ ሌሎች ሀገራት የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት ገልጸው፤ ከእዚያ ይልቅ ሁሉም ሀገራት ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ በጋራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከየትኞቹም የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በግልጽነትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል። ለእዚህም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያላትን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የምትሠራ መሆኑን መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አስታውቀዋል። 
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ
Home 

No comments:

Post a Comment