Tuesday, May 14, 2013

ሚኒስትሩ ከኃላፊነት መነሳታቸውን መንግሥት ይፋ አደረገ

(May 14, 2014, (አዲስ አበባ))--የፍትህ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ብርሃን ኃይሉ ከኃላፊነት መነሳታቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ይፋ አድርገዋል።

አቶ ሽመልስ ለጋዜጣው ሪፖርተር ትናንት እንደገለጹት፤ አቶ ብርሃን ከግንቦት 1ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተጻፈ ደብዳቤ ነው። ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ በደብዳቤው ላይ አልተገለጸም።

መንግሥት አቶ ብርሃንን እስከ አሁን ላደረጉት አስተዋጽኦ በማመስገን ከኃላፊነታቸው እንዳነሳቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። በምትካቸው እስከ አሁን የተመደበ ሰው እንደሌለም አመልክተዋል።

በፍትህ ሥርዓቱ ላይ በርካታ የአሠራር ችግሮች እንደሚስተዋሉ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፤ በቅርቡ የፍትህ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸምን የገመገመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አፈጻጸሙ ደካማ መሆኑን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል። አቶ ብርሃን ኃይሉ ቀደም ሲል በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ ኃላፊነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment