Wednesday, April 17, 2013

በሃይማኖት ስም የማታለል ወንጀል የፈጸመችው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣች

(Apr 17, 2013, (አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሃይማኖት ስም በማታለል ወንጀል የተከሰሰችውን ትዕግስት ብርሃኑን በሁለት ዓመት ከአራት ወር ጽኑ እስራትና በአንድ ሺ ብር እንድትቀጣ ወሰነባት።

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግለሰቧ ላይ የተከፈተባት ክስ እንደሚያመለክተው፤ ጥር 24 ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ተክለሐይማኖት ቤተክርስቲያን፣ ግለሰቧ ምእመናን በተሰበሰቡበት «ማርያም ነኝ፣ ማርያም አመል ኩሳኛለች፣ እንደ እየሱስ ክርስቶስ ተገርፌ ተሰቅዬ ከሞት እነሳለሁ» በማለት የማርያምን የፎቶ ዲዛይን ከራሷ ፎቶ ጋር በሚያምታታ መልኩ በማዘጋጀት «የዓለም ፍጻሜ ደርሷል፤ ንብረት አያስፈልግምና ስጡኝ» በማለት ስትሰብክ ነበር።

ግለሰቧ ሞገስ መኮንን ከተባለ የግል ተበዳይ 6 ሺ ብር እና 32 ሺ 500 ብር የሚያወጣ 65 ግራም የወርቅ የአንገት ሀብል፣ እንዲሁም አብረኸት አባዲ ከምትባል የግል ተበዳይ ደግሞ 2 ሺ 400 ብር የሚያወጣ አራት ግራም ወርቅ መቀበሏን ክሱ ያብራራል። ይህንንም በማድረጓ በማታለል ወንጀል ተከሳለች ይላል ።

ግለሰቧ በተክለሐይማኖት ቤተክርስቲያን ባደረገችው ንግግር ሳቢያም በሃምሳ ተከታዮቿ እና «ያደረገችው ንግግር ትክክል አይደለም» በማለት በተቃወሙ ምእመናን መካከል ሁከት በመፈጠሩም የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በማሳሳት ወንጀልም ተከሳለች ።

ዐቃቤ ህግም ክሱን ለማስረዳት አስራ ሦስት የሰው ምስክሮችን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፤ ተከሳሿ ስታስተምር የሚያሳይ የተቀረጸ የቪሲዲ ምስል በማስረጃነት ቀርቦባታል።

ለማሳሳቻነት የተጠቀመችበትን ፎቶግራፍ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግለሰቧ የሰጠችው ትምህርት ሀሰተኛ መሆኑን የሚያሳይ ደብዳቤም ዐቃቢ ህግ አቅርቧል ።

ተከሳሽ ትዕግሰት ብርሃኑም እነዚህን የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች መከላከል ባለመቻሏ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስድስተኛ የወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ተብላ፤ በሁለት ዓመት ከአራት ወር ጽኑ እስራትና በአንድ ሺ ብር እንድትቀጣ ተወስኖባታል።

በግለሰቧ ላይ መጀመሪያ የቀረቡባት አራት ክሶች ቢሆኑም፤ የሰው ልጅን ህይወት ለአደጋ በማጋለጥና ለአደጋ የተጋለጡትን ባለመርዳት እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦችም እንዳይረዱ በማድረግ ከቀረቡባት ሁለት ክሶች ነጻ እንደትሆን ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔ ማሳለፉን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በድረ ገፁ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment