(Mar 02, 2013, (አዲሰ
አበባ))--አካል ጉዳተኛ ሆኖ መፈጠር ሙሉ አካል
ያላቸው ሰዎች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ከመፈፀም የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ አሜሪካዊቷ ጄሲካ ኮክስ ገለጸች።
ኮክስ ስትወለድም ሁለት እጆች የሌላት ሲሆን፤ እግሮቿን በመጠቀም አውሮፕላን በማብረር በዓለም የክብረ ወሰን መዝገብ
ስሟን በማስፈር የመጀመሪያ ናት ።
ጄሲካ የሕይወት ተሞክሮዋን ባቀረበችበት ወቅት ኢትዮጵያዊው አቶ ስንታየሁ ተሻለ ተገኝቶ ልምዱን አካፍሏል፤(ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ) |
ስትወለድ ጀምሮ ሁለት እጆች እንደሌላት
የተረዱት ቤተሰቦቿ እንደማንኛውም ሙሉ አካል እንዳለው ሰው በመቁጠር ምሉእነት እንዲሰማት አድርገው እንዳሳደጓት
ያስታወሰችው ጄሲካ፤ ለአሁኑ ማንነ ቷ የእነርሱ በጎ ተፅእኖ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ትናግራለች። « ቤተሰቦቼ
ተፈጥሮዬን አምኜ እንድቀበል አድርገውኛል። ዘወትር በእራስ መተማመን እንዳለብኝ የሚያስተምሩ ምክሮችን ይለግሱኝ
ነበር። ከምንም ነገር በላይ በዕውቀት እንድታነፅ አስፈላጊውን ትምህርት እንዳገኝ ረድተውኛል። በእዚህም አውሮፕላን
ለማብረር የሚያስችል ፈቃድ እስከማግኘት ደርሻለሁ» ብላለች።
በኢትዮጵያ ቆይታዋ አውሮፕላን እንደምታበር
የገለጸችው ጄሲካ፤ አካል ጉዳተኛ መሆን የፈለጉት ደረጃ ከመድረስ እንደማያግድ የሚያስተምረውን የሕይወት ተሞክሮዋን
በተለያዩ መድረኮች እንደምታስተላልፍ ተናግራለች።
የጄሲካ የሕይወት ተሞክሮ በቀረበበት መድረክ
ላይ ሁለት እጆቹ ባጋጠማቸው እክል ተስፋ ሳይቆርጥ በእግሩ የተለያዩ የእንጨት ቁሳቁስ በመስራት የሚታወቀው አቶ
ስንታየሁ ተሻለ ሁኔታዎች ከተመቻቹ አካል ጉዳተኛ መሆን ሁሉንም ነገር ከማድረግ እንደማያግድ ልምዱን አካፍሏል። «እኔ ማንኛውንም ነገር በእግሬ አከናውናለሁ። የተመቻቸ ሁኔታ ካለም በእግሬ መኪና መንዳት አያቅተኝም» ያለው አቶ ስንታየሁ በሀገራችን ለአካል ጉዳተኞች የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
ያጋጠሙትን ችግሮች ተቋቁሞ እራሱን በራሱ
የተለያዩ የእንጨት ቁሳቁስ መስራት እንዳስተማረ ለታዳሚዎች የገለጸው አቶ ስንታየሁ፤ የሕይወት ተሞክሮውን ለሌሎች
በማካፈል መነቃቃት እንዲፈጠር ሁኔታዎች እንዲመ ቻቹለት ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዲሲኤቢሊቲ ኤንድ ዴቬሎፕመንት ሴንተር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ጄሲካ የፅናት ምሳሌ መሆኗን ጠቅሰው፤ «በእጅ ይሠራል ተብሎ የማይታሰበውን ሥራ እጅ ባይኖርም መሥራት እንደሚቻል አሳይታናለች» ብለዋል።
«በእኛ ሀገር አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች
መሥራት አይችሉም የሚባለው ነገር ይበዛል። እጅ የሌለው ሰው መኪና የመንዳት ችሎታ ቢኖረውም ሕጉ ስለማይፈቅድ ዕድሉ
አይሰጠውም። ጄስካ ፍላጎትና የተመቻቹ ሁኔታዎች ተጣምረው ስላገኘች ለስኬት በቅታለች» ያሉት ወይዘሮ የትነበርሽ፤ ፖሊሲ አውጪዎች የአካል ጉዳተኞችን አቅም የማይገድቡ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የአሜሪካ
ኤምባሲና ሀንዲካፕ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት የጄሲካ ኮክስን የኢትዮጵያ ቆይታ ያመቻቹ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ቀናት
ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደምትገናኝ ተገልጿል። ጄሲካ ኮክስ እስከ አሁን ድረስ በ18 አገራት በመዘዋወር የሕይወት ተሞክሮዋን አካፍላለች።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment