Sunday, March 10, 2013

ምእምናን ነገ የሚጀመረውን የዓብይ ጾም ሲጾሙ ለአገርና ለወገን የሚበጅ መልካም ስራን በመስራት ሊሆን ይገባል

(መጋቢት 1/2005, (አዲሰ አበባ))--የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች ነገ የሚጀመረውን የዓብይ ጾም ሲጾሙ ለአገርና ለወገን የሚበጅ መልካም ሥራን በመስራት ሊሆን እንደሚገባው ቤተ-ክርስትያኗ ገለፀች፡፡ 
 

ስድስተኛው የቤተ-ክርስትያኗ ሊቃነ ጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ነገ የሚጀመረውን የዓብይ ጾም አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላይ እንዳሉት ሁሉም ምእምናን ወርሃ ጾሙን በምግባር፣ በኃይማኖትና መልካም ሥራን በማብዛት ሊያሳልፉት ይገባል፡፡ 

የእምነቱ ተከታዮች ተግባራት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱና ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ርህራሄ፣ ቸርነትን፣ ምጽዋትን፣ ትእግስትን፣ ፍቅርን፣ ስምምነትን፣ ትህትናን፣ መረዳዳትንና መተዛዘን ይበልጥ ገንዘብ ማድረግ ሲችሉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

ቤተ-ክርስትያኗ በመላው አገሪቱ እየተካሄዱ ያሉት የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ሰፊ ጥረት በታላቅ አድናቆት እንደምትመለከተው ገልጸው ቤተ-ክርስትያኗ የጥረቱ አካል በመሆንም የሚጠበቅባትን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች ብለዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ የተጀመሩት የልማት ሥራዎችም ውጤታማነታቸው እስኪረጋገጥ ቤተ-ክርስትያኗ የዘወትር ድጋፏና ትብብሯ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡ ምዕመናንም በወርሃ ጾሙ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ኃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት መልካም የሆኑትን የልማት ሥራዎች ሁሉ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ 
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment