Monday, March 18, 2013

የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ይፋዊ ጉብኝት ጀመሩ

(Mar 18, 2013, (አዲሰ አበባ))--የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጁሐኪም ጋውክ ትናንት ከቀኑ 1030 ላይ አዲስ አበባ ሲገቡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መኮንን ማንያዘዋል ተቀብለዋቸዋል፤

(March 16, 2013 - Source: Sean Gallup/Getty Images Europe)
የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጁሐኪም ጋውክ በኢትዮጵያ የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገቡ። ፕሬዚዳንቱ በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መኮንን ማንያዘዋልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። 
 
ፕሬዚዳንት ጁሐኪም ጋውክ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ፕሬዚዳንቱ ከሲቪል ማህበራት፣ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች ጋር ይወያያሉ። ላሊበላና የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤትን ይጎበኛሉ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ግሩም አባይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያና በጀርመን መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ጠንካራ ነው። የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ግንኙነቱን ይበልጥ ያዳብረዋል። ከጀርመን መንግሥት ጋር በየሦስት ዓመቱ የሚከለስ የልማት እቅድ መኖሩን ጠቁመው፤ ጀርመን በሰው ኃይልና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ ትልቅ ድጋፍ እያደረገች መሆኗም ተናግረዋል። 

እንደ አምባሳደሩ ገላጻ፤ ጀርመን ጠንካራ የኢትዮጵያ የንግድ አጋር ነች። በወጪ ንግድ በአውሮፓ ቀዳሚ የኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ ነች። በአገር ውስጥ ጀርመናውያን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ተሰማርተው ይገኛሉ። ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በጸጥታና በሌሎች ጉዳዮች በትብብር እየሰራች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment