Wednesday, March 27, 2013

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና አስከፊ ገጽታው

(Mar 27, 2013, (አዲሰ አበባ))--በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለብዙ ሰዎች መንገላታትና ሞት ምክንያት እየሆነ ነው። ድርጊቱ የሚያስከትለው ማኅበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ ከሀገራት አልፎ ዓለም አቀፋዊ ስጋት እየሆነ ይገኛል። ድርጊቱ የመንግሥትን ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ በሚፃረር ሁኔታ እየተፈጸመ ከመሆኑም በላይ ወንጀሉ እየተራቀቀና እየተባባሰ መጥቷል።

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጓዦች በደላሎች እየተታለሉ ሀብትና ንብረታቸውን ሸጠው ቀያቸውን ለቀው ይሄዳሉ። ያለምግብና ውሃ ሕይወታቸውን ለአስከፊ አደጋ በማጋለጥ በአውሬዎች እየተበሉ፣ ከጀልባ ላይ ወደ ባህር እየተወረወሩ ፣በመንገድ ላይ እየሞቱ ነው። ከሀገራቸው ወጥተው ያሰቡበት ቦታም ሳይደርሱና ያሉበት ሳይታወቅ የቀሩ በርካቶች ሲሆኑ ሀብትና ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን አካላቸውን ያጡም አሉ። በአንፃሩ ደላሎች ከፍተኛ ገንዘብ እየበዘበዙ የግል ጥቅማቸውን እያካበቱ የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ተጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አድማሱን አስፍቶ ረቂቅነቱን አሳድጐ ወጣቱን ኃይል እንዲሰደድ በማድረግ በሀገሪቱ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩም በላይ ገጽታዋን እያበላሸም ይገኛል።

የሕገወጥ ዝውውሩን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም ችግሩን ለማስቀረት አልተቻለም። በአሁኑ ወቅት ችግሩ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በተለይ ደግሞ በሀድያ ዞን በምትገኝ ጊምቢቹ ከተማ ሶሮ ወረዳ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የሶሮ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የዞኑ መስተዳድር ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት ስለችግሩ አስከፊነት ተነጋግረዋል።

ወጣት ደመቀ ዘለቀ ይባላል የ7ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ደላሎች 'ደቡብ አፍሪካ ብትሄድ ገንዘብ ታገኛለህ' ስላሉት ወደዚያው ሄዶ ያሰበውን ሳያገኝ ተመልሷል። ደላላው «በአፈር ምርመራ ሥራ አለ። የትምህርት ማስረጃችሁን ያዙና እልካችኋለሁ። እዚያ በዚህ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ታገኛላችሁ። ብዙዎች ሀብታም የሆኑት ይሄን እየሠሩ ነው» በማለት እንዲሁም የጥቂት ሰዎችን መለወጥ በመጥቀስና በማሳየት እንዳታለለው ይናገራል።

7ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነና የትምህርት ማስረጃ እንደሌለው ቢነግረውም የትምህርት ማስረጃውን እርሱ እንደሚያሰራለት ስለነገረው የቤተሰቦቹን ንብረት ሸጦ ፣ከወንድሙም ፣ከጓደኞቹም ተበድሮ 15ሺ ብር ቀብድ ከፍሎ ቀሪውን ጉዳዩ ሲፈጸም ለመክፈል ተስማምቶ አብሮት ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። አዲስ አበባ ከመጣም በኋላ ለ3 ወራት ጉዳዩ ሳይፈጽምለት ሲንከራተት ከመቆየቱም ባሻገር የውሃ ሽታ ሆነበት። ከብዙ መከራ በኋላ በሰዎች አማካኝነት ደላላውን አግኝቶ ሌሎቹን እየላከ እርሱን ለምን እንደማይልከው ሲጠይቀው «አንተን የማስገባህ ጥሩ ቦታ ስለሆነ ጉዳይህን እየጨረስኩልህ ነው፡፡ 

አሁን ቶሎ 5ሺ ብር ብትጨምር አልቆልህ ትሄዳለህ» ስላለው አምስት ሺ ብር ጨምሮ ይሰጠዋል፡፡ ያቺን ብር ያገኘው ደላላ በድጋሚ ይጠፋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ደግሞ ከዚህ በፊት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት የሰማ ሌላ ደላላ በተራው «እኔ ጉዳዩን በቀላሉ አስጨርስልሃለሁ» አለው። ደቡብ አፍሪካ የሚገኝ የዚህ ታዳጊ ወንድም እንዲመጣ ለደላላው ስለጨ ቀጨቀው፤ የመሄድ ፍላጐቱ ዳግም ስለተነሳሳ። 

የእናቱን መሬት በኪራይ አሲይዞ ከፈለ። 'ይሄ ደላላም ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ' እያለ ካንገላታው በኋላ ገንዘቡን ተቀብሎ ኬንያ ላይ ወስዶ ይጥለዋል። እዚያ ደግሞ ሌላ ፈተና ገጠመው፡፡ ኬንያ ላይ ዘራፊዎች ገንዘብ ሲጠይቁት ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ክፉኛ ደበደቡት። በዚህ ሳቢያም አንድ ኩላሊቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ እስካሁን ድረስ ደም እየሸና እየማቀቀ ለመኖር ተገዷል። 

በጓደኞቹና በሌሎች ሰዎች ዕርዳታ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄደው ደመቀ ወንድሙና ጓደኞቹ ሲረዱት ቆይተው ሕመሙ ስለፀናበትና መሥራት ስላልቻለ ከ3 ወር በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። በሀገሩ ላይ መሥራት እየቻለ በደላሎችና በተባባሪዎቻቸው ተታሎ በሕገወጥ መንገድ በመሄዱ ለችግር እንዳጋለጠው የተናገረው ደመቀ የተበደረውን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻሉ ካበደሩት ሰዎች ጋር ተጋጭቷል። የቤተሰቡን ንብረት ሸጦ ገንዘቡን የከፈለ ቢሆንም ካሰበው ቦታ ሳይደርስ፣ ሃሳቡን ሳያሳካ ከጤናውም ከገንዘቡም ሳይሆን በመቅረቱ እጅግ ማዘኑን ይገልጻል።

«ጥቂት ኑሯቸውን የለወጡ ሰዎችን እያየን በጓደኞቻችንም እየተገፋፋን፣ ደላሎችም በሃሰተኛ ስብከት እያነሳሱን የእነርሱ መጠቀሚያ ሆነናል። ለዚህ ችግር የተዳረግሁት በተሳሳተ አመለካከት ስለሆነ ወጣቱ በደላላ ከሚደረግ እንዲህ ዓይነት ጉዞ ራሱን ይጠብቅ» ብሎ መክሯል።

ደላሎች እርስ በእርስ ስለሚተዋወቁና በተቀናጀ መልኩ በቅብብሎሽ እየሠሩ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል የሚለው ደመቀ ማንነታቸው ስለሚታወቅ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ይላል። ኅብረተሰቡም ያገኘውን መረጃ በማሰባሰብ ጥቆማ በማድረግ ከመንግሥት ጐን መቆም አለበት። ወጣቱን እያነሳሱ የሚልኩ ደላሎች ከመካከላችን ስላሉ እርምጃ ሊወሰድባቸውና ከዚህ ሥራቸው ሊቆጠቡ ይገባል የሚል ሃሳብ አለው።

በሀድያ ዞን ጊምቢቹ ከተማ ሶሮ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አቤቦ ላሴሶ በአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በአካባቢ ልማድና ወግ መሠረት የሚዳኙ የአካባቢው ዳኛ ናቸው። በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት ወጣቶች ከአባባቢው እየተወሰዱ ለሞትና እንግልት እየተዳረጉ በመሆኑና ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ ሊገታ ይገባል በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

«በእኛ አካባቢ ያሉ ሴቶችም ሆኑ ወንዶቹ ወደ ውጭ ሀገር እየሄዱ ነው። የሚሄዱት ግን በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት ሕጋዊነትን ባልተከተለ ሁኔታ በመሆኑ ብዙዎቹ ወጣቶች ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለችግርና ለመከራ እየተዳረጉ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ጥቂት የተሳካላቸው ሰዎች በማሳየት ደላሎች በሚጫወቱት አሉታዊ ሚና ነው» ይላሉ።

በአሁኑ ሰዓት ወጣቶቹ ላይ የሚታየው አዝማሚያ አገር ውስጥ ከመሥራት ይልቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ ነው የሚሉት ዳኛ አቤቦ ወጣቶቹ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው አንስተዋል። እዚህ ተሠርቶ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ እዚያ የሚገኘው እንደሚሻል አድርገው በማሰብ ከብቶቹን እየሸጠ በእጃቸው ላይ ከ50ሺ ብር በላይ በመያዝ በሕገወጥ መንገድ እየወጡ ራሳቸውን ለሞት እና ለተለያዩ አደጋዎች እያጋለጡ ነው ባይ ናቸው። አንዳንድ ቤተሰብም ልጆቹ እንዲሄዱ በመገፋፋት ከብቶቻቸውን እየሸጡ ገንዘብ በመስጠት ድርጊቱ እንዲስፋፋ እያደረገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሊያስብበት እንደሚገባ ነው የጠየቁት።

ደላሎች ሕገወጥ ሴት ተጓዦችን እየደፈሩ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ። ሴቶቹም በእርግዝና ምክንያት ከመንገድ ይመለሳሉ የጤና ችግር ይደርስባቸዋል። ገንዘባቸውም ይከስራል። የጥቃቱ ሰለባ በመሆን በችግር ላይ ይገኛሉ ሲሉ በምሬት ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት ብዙዎቹ ወጣቶች ያሉበት አይታወቅም። መሞታቸውን ብቻ ተሰምቶ ሬሳ ሳይገኝ የሚቀርበትና እርማቸውን ሳያወጡ የሚቀሩበት ጊዜ በርካታ ነው። 

ወላጆች ልጆቻቸውን ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ብዙ ወጣቶች ከቤት እየወጡ ቤተሰብ ያለ ልጅ እየቀረ እንደሆነ በመግለጽ በአካባቢው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እያስከተለ ስላለው ችግር ያስረዳሉ። ከዞኑ ብዙ ወጣቶች ወደተለያዩ ሀገሮች እየተሰደዱ በጅብ ተበልተዋል፣ በባህር ውስጥ ተጥለዋል፣ በኮንቴይነር ታፍነው ሞተዋል፣ እሥር ቤት ገብተው ሕይወታቸው አልፏል። ሌሎቹም በእሥር ቤት እየተሰቃዩ ነው ብለዋል ዳኛ አቤቦ። 

ወጣቶቹ በአገራቸው መሥራት እየቻሉ በርካታ ገንዘብ ይዘው በመሄድ ለሞት እየተዳረጉ በመሆናቸው የማስተማርና የመምከር ሥራ እየተሠራ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ወደ ውጭ መሄድ ከፈለጉ ራሳቸውን ለአደጋ ሳያጋልጡ በሕጋዊ መንገድ መሄድ የሚችሉ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉም አስተያ የታቸውን ሰጥተዋል።
 
በሕገወጥ መንገድ ወጣቶቹን እየሰበሰቡ በሚያጓጉዙ ደላሎችም ሆነ በተባባሪዎቻቸው ምክንያት እየደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ሰብዓዊ ጥሰት ቀላል ባለመሆኑ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ችግሩን ለማስቀረትም የችግሩ ተጠቂ የሆነው ኅብረተሰብ በግንባር ቀደምትነት ሊተባበር ይገባል ይላሉ።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በአሁኑ ወቅት በዞኑም ሆነ በክልሉ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀድያ ዞን አስተባባሪ አቶ ማትያስ እንየው በተለይም በዞኑ የሕገወጥ ደላሎች ተግባር ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየተባባሰ መጥቷል ነው ያሉት። በመሆኑም ችግሩ በተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት ጥረት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን በማለት ነው የችግሩን አሳሳቢነት የገለጹት፡፡

ሕገወጥ ደላሎችና አጓጓዦች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በወጣቶቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ይፈጽሙባቸዋል፣ ልዩ ልዩ የአካል ጉዳቶችን ያደርሱባቸዋል፣ ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ ፣በመዳረሻ አገራት ለሴተኛ አዳሪነት ይዳርጓቸዋል፣ ከትላልቅ ፎቆች ላይ ይወረውሯቸዋል፣ ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ በጉዞ ላይና በመዳረሻ አካባቢዎች ስለሚደርስባቸው ለከፍተኛ ጭንቀትና ለሥነልቦና ችግሮች እየተዳረጉ ነው። የሥነልቦና ጭንቀቱም በአጠቃላይ ለሕዝብና ለመንግሥት በተለይም ለቤተሰቦቻቸው እየተረፈ ከመምጣቱም በላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ቀውስም እያስከተለ መሆኑን ያብራራሉ።

ለተፈጠረው ችግር ዋናው መንስኤ የአመራሩ፣ የባለሙያው፣ የወጣቶች፣ ሴቶችና የመላው ኅብረተሰብ የአመለካከት ችግር ነው ያሉት አቶ ማትያስ ሕገወጥነትን ለመከላከል ጥረቶች እየተካሄዱ ቢሆንም በቂ ውጤት አላስመዘገቡም። ይልቁንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወንዶች ደቡብ አፍሪካን ፣ሴቶች ደግሞ ዓረብ አገሮችን ብቸኛ የሀብት ማግኛ አድርገው ወደ ማምለክ የደረሱበት አስደንጋጭ የአመለካከት ችግር ውስጥ ገብተዋል። ይህ አስተሳሰባቸው ሊሰበር ይገባል። በሀገራቸው ውስጥ ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

መንግሥት የችግሩ ሰለባ የሆኑትንና ሌሎችንም ወጣቶች ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲደራጁ በማድረግ በገጠርም ሆነ በከተማ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡ ወጣቶችም በዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከዚህም ጐን ለጐን በታንዛኒያ፣ በኬንያና በተለያዩ ሀገራት በእሥር ቤት ያሉትን ለመመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ጋር እየሠራ ነው።

የሀድያ ዞን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ዩኒት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ኤርገንዶ እንደገለጹት በዞኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኘውን የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ለመግታት እና የዜጐችን ሕይወት ለመታደግ እየተሠራ ነው። በዓመቱ መጀመሪያ ከሁሉም ወረዳዎች ከሁሉም ቀበሌ መረጃ ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት የሰዎች ዝውውር እየተባባሰ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል።

ይህንኑ በመገንዘብ በዞኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ዞናዊ የቴክኒክ አስፈጻሚ ኮሚቴ በማቋቋም የሕዝብ ንቅናቄ የኮንፍረንሶች መድረኮችን በማዘጋጀት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰብ ተወካዮች ፣ከነጋዴዎች፣ ከማኅበራት ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከትምህርት ተቋማት ከሕዝብ እንደራሴዎች፣ ከፍትህ አካላትና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ ነው። እርሳቸው እንደጠቀሱት ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ጥናታዊ ጽሑፍ ለወሳኝ የመንግሥት አካል ለማቅረብ መረጃ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናቋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃርም ሕገወጦችን ወደ ሕግ አቅርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ የዞኑ የፍትህ አካላት ባደረጉት ጥረት በ2005 .ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ብቻ በ219 ፋይሎች 125 ተጠርጣሪዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የተደረገ ቢሆንም በተገቢው ሁኔታ ማስረጃዎች ሊቀርቡ ባለመቻላቸው፣ ለወንጀለኞች ሽፋን የሚሰጡ ሰዎች በመበራከታቸው እንዲሁም አብዛኞቹ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች አካባቢውን ለቀው በመሰወራቸው የተፈለገውን ያህል መጓዝ አልተቻለም ነው ያሉት።

በሕገወጥ ደላላዎች ተታለው በሄዱ የዞኑ ወጣቶች ላይ የሞት፣ የአካል መጉደልና ሌሎች ከፍተኛ ጉዳቶች ከመድረሱም በላይ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስከተሏል። አካባቢው አምራች ዜጐችን አጥቷል ፤በመማር ማስተማሩ ፕሮግራም ላይም ከፍተኛ እንቅፋት ተፈጥሯል። በበርካታ ወጣቶች ላይም ለልማት ፀር የሆነ ሥነልቦናዊ ችግር አስከትሎባቸዋል የሚሉት አቶ ምትኩ ይህን ድርጊት በጋራ መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መስፋፋት ኅብረተሰቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው መሆኑን ለመከላከል በሚደረገው ሥራ መረጃዎችን በመስጠትና በመጠቆም ዋነኛ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በምክክሩ ላይ የነበሩት የኅብረተሰቡ ክፍሎችም ከመንግሥት ጐን ሆነው ድርጊቱን ለመከላከል እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ያለዕድሜያቸው የቀበሌ መታወቂያና ፓስፖርት የሚሰጠው አካልም ለድርጊቱ እየተባበረ መሆኑንና ወንጀል እየሠራ መሆኑን ተገንዝቦ ከድርጊቱ ሊቆጠብ ይገባዋል። መንግሥትም አሠራሩ ሊፈተሽ ግድ ይለዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment