Monday, March 18, 2013

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድረ ገፅ ይፋ ሆነ

(Mar 18, 2013, (አዲሰ አበባ))--የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት በታላቁ የህዳሴ ግድብና በግድቡ ዙሪያ እየተከናወነ ስለሚገኘው ሥራ ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ለማድረስ ያዘጋጀው ድረ ገፅ ትናንት አገልግሎት ጀምሯል። 

ጽህፈት ቤቱ ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር www.hidasse.gov.et በሚል መጠሪያ የተዘጋጀው ይኽው ድረ ገፅ ትናንት በጽህፈት ቤቱ አዳራሽ በይፋ ተመርቋል። ድረ ገፁ ግድቡን የሚመለከቱ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ህዝቡ እያበረከተ ያለውን የገንዘብና የድጋፍ ዓይነት እንዲሁም ግንባታው የደረሰበትን የእድገት ደረጃ የሚያሳዩ መረጃዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

የምክር ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ከተማ እንደሚሉት፤ በሀገር ውስጥ አቅም ብቻ እየተከናወነ እና የሕዝብና የመንግሥት የነቃ ተሣትፎ ጐልቶ የሚታይበትን የእዚህን ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ገፅታ ለማሳየት የድረ ገፁ መከፈት ታላቅ ሚና አለው። የሕዝቡንም ተሣትፎ በማጠናከር ወደ ታላቅ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ድረ ገፁ የታላቁ ሕዳሴ ግድብንና ህዝባዊ ተሳትፎውን በተመለከተ በልዩ ልዩ የመወያያ ርዕሶች ላይ በመመርኮዝ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች የሚወያዩበትን መድረክም ማካተቱን ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት። 

የድረ ገፁ ሥራ መጀመር ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎችን ለህዝቡ በማድረስ ለግድቡ ዕውን መሆን መላው ህብረተሰብ ተሳትፎውን በተሟሟቀና ቀጣይነት ባለው መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጎላ ሚና ይኖረዋል።
ዜጎች ይህንኑ ድረ ገፅ በመጎብኘት በቂ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉ ያመለከቱት አቶ ፍቃዱ፤ ጠቃሚ ግብረ መልሶችንም በመለገስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩንም ነው የጠቆሙት። 

በድረ ገፅ ምረቃ ላይ የተገኙት የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተወካይ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ መስሪያ ቤቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን በተለያየ መልኩ ድጋፎችን እያደረገ ነው። ከእነዚህም መካከል የግድቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ከመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

እንደ ተወካዩ ገለፃ፤ አዲሱን ድረ ገፅም በባለሙያዎቹ ከፍተኛ ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ አድርጓል። ኤጀንሲው በቀጣይም የላቀ አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው።

በተያያዘ ዜና መጋቢት 24 የሚከበረውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ የፅህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ከተማ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ እንዳስታወሱት፤ በዓሉ «መለስ ቃልህ ይከበራል ታላቁ የህዳሴ ግድብም በህዝባችን ተሳትፎ እውን ይሆናል» በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል። 

«በዓሉን የምናከብረው ታላቁን የዓባይን ወንዝ በህዝብና በመንግሥት ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ አቅጣጫውን የምናስቀይርበት ዋዜማ ላይ መደረሱ ለየት ያደርገዋል» ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አቅጣጫ የማስቀየሱ ተግባር ለመጋቢት 24 ያለመድረሱን ነው ያመለከቱት። ሆኖም የማስቀየሱ ተግባር በሚከናወንበት ወቅት ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ አቅም ለዓለም ህዝብ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።

በዓሉ በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ ከመጋቢት 21 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም የስፖርትና የሙዚቃ ዝግጅቶች የሚገኙበት መሆኑን ያመላክታሉ። በብሔራዊ ቴአያትርም የግጥም ምሽት ይካሄዳል። 

ግድቡ በሚገኝበት ጉባ አካባቢም መጋቢት 24 ቀን በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር መሆኑን ተናግረው በዚህ፤አጋጣሚም ህዝቡ ለግድቡ እውን መሆን እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ያሳሰቡት።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home


No comments:

Post a Comment