Friday, February 08, 2013

በናይጄሪያ ስኬት የዋልያዎቹ ጥንካሬ ተመዝኗል

(Feb 08, 2013, ቦጋለ አበበ)--በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሦስት ተደልድለው የነበሩት ናይጄሪያና ቡርኪናፋሶ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋገጠዋል። ናይጄሪያና ቡርኪናፋሶ በአፍሪካ ዋንጫው ግምት ያልተሰጣቸው ሀገሮች ቢሆኑም ባልታሰበ ሁኔታ ጫፍ መድረስ ችለዋል።


ናይጄሪያና ቡርኪናፋሶ በምድብ ጨዋታቸው ከኢትዮጵያና ከአምናዋ ሻምፒዮን ዛምቢያ ጋር ተደልድለው ወደ ሩብ ፍፃሜ ቢያልፉም ግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገሮች ከግማሽ ፍፃሜም አልፈው የዋንጫ ተፋላሚ መሆን ችለዋል።

ናይጄሪያ በተለይም በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የአፍሪካ እግር ኳስ ቁንጮ የሆኑትን ኮትዲቯሮችን ጥላ ግማሽ ፍፃሜ ትደርሳለች ብሎ ማሰብ አዳጋች ነበር።ናይጄሪያ ዝሆኖቹ በመባል የሚታወቁትን የኮትዲቯር እግር ኳስ ወርቃማው ትውልድን እንደማያሸንፉ የተገመተው በመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸው ከዋልያዎቹ በገጠማቸው ትልቅ ፈተና ነው።

አረንጓዴ ንስር በመባል የሚታወቀው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከዋልያዎቹ በነበራቸው ጨዋታ ከምድባቸው ለማለፍ ጠንካራ ፉክክር ገጥሟ ቸዋል። ከዋልያዎቹ ከባድ ፈተና የገጠማቸው አረንጓዴ ንስሮቹ በጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ባለቀ ሰዓት እድል ቀንቷቸው አሸናፊ መሆን ችለው ነበር።ናይጄሪያዎች ዋልያዎቹን አሳማኝ ባልሆነ ጨዋታ አሸንፈው ኮትዲቯርን በሩብ ፍፃሜ ሲገጥሙ ይከብዳቸዋል ቢባልም ኮትዲቯርን እንደማይፈሯትና ከባዱ ጨዋታቸው ከዋልያዎቹ ጋር ያደረጉት እንደነበር በአንደበታቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በእርግጥም አረንጓዴ ንስሮቹ የኮትዲቯርን ጠንካራ ስብስብ አሳማኝ በሆነ ጨዋታ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ካሸነፉ በኋላ ነው ከባድ ፉክክር የገጠማቸው። ይህም ፉክክር ከዋልያዎቹ ጋር ያደረጉት ጨዋታ እንደሆነ ነው የተነገረው። ናይጄሪያ ዋልያዎቹን መግጠማቸው እራሳቸውን እንዲፈትሹ አድርጓቸዋል ማለት ይቻላል።ለእዚህም ቡድናቸው ውስጥ የነበሩ ክፍተቶች ከዋልያዎቹ ጋር ካደረጉት ጨዋታ በኋላ አስተካክለው የማይበገሩ እየሆኑ መምጣታቸውን መካድ አይቻልም።
 
ናይጄሪያ ከዋልያዎቹ ጨዋታ በኋላ የነበረባትን ድክመቶች አርማ እዚህ መድረሷ ዋልያዎቹ ምንያህል ጠንካራ እንደሆኑ ያሳያል።ይህ ማለት ግን ዋልያዎቹ ድክመት የለባቸውም ማለት ሳይሆን ዋልያዎቹ ቀጥ አርገው ያቆሙት ቡድን ኮትዲቯርን የመሰለ ብሔራዊ ቡድን አሳማኝ በሆነ መልኩ ማሸነፉ ሲታይ ዋልያዎቹን ማድነቅ ተገቢነት ይኖረዋል።

ሰኢዶ ኬታን የመሳሰሉ በአውሮፓ ሊጎች ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው የማሊ ብሔራዊ ቡድን በናይጄሪያ አራት ግብ ሲገባበት ማየትም ዋልያዎቹን የሚያስመሰግን ነው።ዋልያዎቹ በናይጄሪያ የተሸነፉት አሳማኝ በሆነ ጨዋታ እንዳልነበረ ታይቷል። ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ናይጄሪያ በማሊ ላይ ፍፁም የበላይነት አሳይታለች ማለት ይቻላል።ማሊ ከኢትዮጵያ አንፃር በእግር ኳስ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሰች ሀገር ብትሆንም ዋልያዎቹ ያቆሙት ቡድን አራት ለአንድ በሆነ ውጤት አሳምኖ ሲያሸንፋት ማየት ዋልያዎቹን ለማድነቅ ያስችላል።
 
ናይጄሪያ ከአስራ ስምንት ዓመት በፊት የነበራትን የሻምፒዮናነት ክብር ለማግኘት የሚቀራት እሁድ ቡርኪናፋሶን መርታት ነው።አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺም ናይጄሪያ የመጨረሻ የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ በአምበልነት የሰሩትን ታሪክ አሁን በአሰ ልጣኝነት የመድገም እድል አጋጥሟቸዋል።

አሰልጣኝ ኬሺ ዋንጫውን ለማንሳት ግምት ማግኘት የጀመሩት ኮትዲቯርን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነው።ከማሊ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ በፍፁም የበላይነት ማሸነፋቸው ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡ ከጨዋታው በፊት ዋንጫ ይገባቸዋል የሚል አስተያየት እንዲጎርፍላቸው አድርጓል።
አሰልጣኝ ኬሺ ማሊን በአሳማኝ ጨዋታ ካሸነፉ በኋላ «ማሊ ጥሩ ቡድን ነው፤ሰኢዶ ኬታን የመሳሰሉ ታላላቅ ተጫዋቾችን አካትቷል፤በተከላካይ ክፍላቸው ላይ የነበረውን ክፍተት ተጠቅመን ማሸነፍ ችለናል »በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

የማሊው አሰልጣኝ ፓትሪስ ካትሮን በበኩላቸው አሁንም በተጫዋቾቻቸው እንደማያፍሩ ገልጸዋል። «በተጫዋቾቼ አላፍርም፤ ለዋንጫ ለማለፍ ጥረት አድርገናል፤ ከእዚህ በኋላም ጥረታችን ለደረጃ ጨዋታው ይቀጥላል » በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። ከምድብ ሦስት ወደ ፍፃሜ ያለፈችው ቡርኪናፋሶም በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ያልተጠበቀች ክስተት ሆናለች።ቡርኪናፋሶ በአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ ስትደርስ ይህ የመጀመሪያዋ ነው።ከእዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችላለች።
 
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሞት ምድብ የተባለው በምድብ አራት ኮትዲቯር፤ ቶጎና የሰሜን አፍሪካዎቹ ሀገሮች ቱኒዚያና አልጄሪያ የተደለደሉበት ነበር።ይሁን እንጂ ከእዚሀ ምድብ እንኳን ለፍፃሜ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰ አንድም ሀገር የለም።

በተቃራኒው በምድብ ሦስት ከዋልያዎቹ ጋር ተደልድለው የነበሩት ቡርኪናፋሶዎችና ናይጄሪያዎች ማንም ሳያስባቸው ከአንድ ምድብ ለፍፃሜ ቀርበዋል።ይህም የሁለቱን ቡድኖች ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ማራኪ ጨዋታ በማሳየት ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩትን ዋልያዎቹን ሌላ ምድብ ውስጥ ተደልድለው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ያስመሰከረ ነው።

ቡርኪናፋሶ ከኮትዲቯር ቀጥሎ ትልቅ ግምት የተሰጣትን ጋናን አሸንፋ ነው ወደ ፍፃሜ ያለፈችው።ጋና በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ስም ቢኖራትም ለፍፃሜ አልፋ በማታውቀው ቡርኪናፋሶ ከፍፃሜ መቅረቷ አስገራሚ ሆኗል። 

ቡርኪናፋሶ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኗን ጋናን ባሸነፈችበት ጨዋታ በዳኛ በደል ደርሶባታል ማለት ይቻላል።ጋና የተሰጣት ፍፁም ቅጣት ምትና ፒትሮፓ በቀይ ካርድ የወጣበት አጋጣሚ ለበርካታ ተመልካቾች አሳማኝ ሆኖ አልተገኘም። ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን አለን ትራዮሬን በጉዳት፤ፒትሮፓን በቅጣት በፍፃሜው ጨዋታ የማያሰልፉት አሰልጣኝ ፖል ፑት በበኩላቸው ወሳኞቹ ተጫዋቾቻቸውን ማጣታቸው እንደማያሳስባቸውና ናይጄሪያን አሸንፈው ሻምፒዮን እንደሚሆኑ እርግጠኛ ሆነዋል::

No comments:

Post a Comment