Wednesday, February 06, 2013

የሃይማኖት ተቋማት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አገራዊ ንቅናቄ እንፈጥራለን አሉ

(Feb 06, 2013, አዲስ አበ ባ)--የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመቃወም፣ ችግሩን ለመግታት አገር አቀፍ ንቅናቄ እንፈጥራለን አሉ፡፡

Ethiopian reporter
ጉባዔው ትናንት በሸራተን አዲስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ሕገወጥ ዝውውሩ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ውስብስብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እንደሚያስከትል በመገንዘብ፣ ሕገወጥ ፍልሰትና ዝውውር የሚያደርሱትን አደጋዎች ሁሉም ዜጎች ጆሮ እንዲደርሱ መጠነ ሰፊ ሥራ በመሥራት ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገንዝበናል፤›› በሚል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙት የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና ፍልሰትን ለመግታት በጋራ እንዲንቀሳቀሱ ጉባዔው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ሃይማኖቶች ስለሰው ልጆች እኩልነትና ስለሥራ ክቡርነት ለምዕመናን በአግባቡ በማስተማር ችግሩ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ለመታደግ ማሰቡን አስታውቋል፡፡

ከማስተማርም በተጓዳኝ የሥራ ዕድል ያላገኙ ወጣቶች በመንግሥትም ሆነ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ባሉ የልማት ድርጅቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በስፋት እንዲሳተፉም እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የተቋማቱ ጉባዔ የሃይማኖት ተቋማት በየአካባቢው ማስረጃ በሚጠየቁበት ጊዜም ትክከለኛና ሀቀኛ መረጃ ብቻ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቋል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አደገኛ ወንጀል ነው ያሉት የሃይማኖት ተቋማቱ፣ ‹‹ከዘመናዊ ባርነትና የሰው አካል ተሸጦ ከሚገኝ ድጎማ ማዳን የሁሉም የሃይማኖት መሪዎች መንፈሳዊና ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው፤›› ብሏል፡፡

“በዚህ አደገኛ የሆነ ወንጀል ስቃይና ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳትና ለዚህም ድርጊት ተባባሪ የሆኑት ሕገወጥ ግለሰቦችን ተባብሮ ወደ ሕግ የማቅረብ የመሥራት ግዴታም አለብን፤” ብሏል፡፡

ችግሩን ለማስቆም የሃይማኖትንና የመንግሥትን ኃላፊነት ለያይቶ ያስቀመጠው የተቋማቱ ጉባዔ፣ ወጣቶችን በእኩል የሚያሳትፍ የመንግሥት ግልጽነት ያለው የአስተዳደር እርከን እንዲፈጠር፣ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር በዚህ ወንጀል ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ቡድኖች በንቃት በመከታተል ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ ወደ ውጭ የሚጓዙ ግለሰቦች አስፈላጊውን መስፈርት እንዲያሟሉና ሥልጠና እንዲያገኙ እንዲደረግ፣ እንዲሁም ይህንን በሚያስፈጽሙ ኤጀንሲዎች ላይ ሕጋዊ ቁጥጥር ማድረግና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም አገልግሎቱን ያለ ውጣ ውረድና እንግልት እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ዋነኛ ሰባት የሃይማኖት ተቋማት ያካተተ ሲሆን፣ መንግሥት ችግሩን ለመግታት ባዋቀረው ብሔራዊ ጉባዔ አንዱ አባል ነው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment