Wednesday, February 27, 2013

ተስፋ ቢሱ ጉዞ !

(Feb 27, 2013,እፀገነት አክሊሉ, አዲስ አበባ)--ከአገርና ከቤተሰብ ተለይቶ በባዕድ አገር ኑሮ መመስረት አንድም ራስንና ቤተሰብን በጣም ሲሳካም አገርን ለመጥቀም ታስቦ የሚወሰን ውሳኔ ነው። የተሳካላትና የቀናው ያሰበበት ሲደርስ በለስ ያልቀናውና ዕድል ፊቷን ያዞረችበት ደግሞ እንዲሁ ባክኖ መቅረቱ እየታየም እየተሰማም ነው።

«ስደትና ፍልሰት የተለያየ ትርጉምና ዓላማ ያላቸው ናቸው» ይላል የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በየዓመቱ የሚከበረውን የስደተኞች ቀን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ « ስደት ማለት አንድ ሰው በፖለቲካ አስተሳሰቡና በአመለካከቱ ወይም በእምነቱ የተነሳ በደል ሲደርስበት ሀገሩን ጥሎ ሲሄድ የሚከሰት ነው። ይህ ዓይነቱ ሰው ደግሞ 'ስደተኛ' ይባላል። 'ፍልሰት' የምንለው ግን ይህንን ጨምሮ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ነው» ሲል ይተነትነዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ታዳጊ አገራት እየተስተዋለ ያለው የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋወር «ፍልሰት» የሚለውን ስያሜ ይይዛል።

የተባበሩት መንግስታት የሥነ ህዝብ ፖሊሲ እ..2010 ባሰራጨው ግምታዊ መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍልሰት ላይ ያሉ ሰዎች ብዛት 214ሚሊዮን መድረሱን ያመለክታል። ከእዚህ ውስጥ ደግሞ 30 ሚሊዮን የሚጠጉት ሕዝቦች ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው። 

ከዚህ አሀዝ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ቁጥርም «ትንሽ ነው» የሚል ግምት የለም። በተለይም ዜጎች በህገወጥ መልኩ ከአገር እንደመውጣታቸው ቁጥራቸውንም «ይህንን ያህል ይደርሳል» ብሎ መገመት እንደሚያስቸግር መረጃው ያትታል።

በእርግጥም ጉዞው በሕገወጥ መንገድም የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን «በእዚህ ጊዜ ይህንን ያህል ሰው ከአገሩ ወጥቶ ወደ ባዕድ ምድር ፈልሷል፤ እዚያም በእዚህ ሥራ ላይ ተሰማርቷል ወይም ችግር ደርሶበታል» ለማለት በጣም አዳጋች ነው።

የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን ተጠቅመው ከአገራቸው የሚወጡ ሰዎች ደግሞ ዋነኛ ጥያቄያቸው ወይም እንዲሄዱ ያስገደዳቸው ነገር በአገራቸው ሰርተው የመለወጥ ፍቃደኝነት ያለመኖርና ካሉበት ዝቅተኛ ኑሮ ተላቅቀው የተሻለ ጥቅም ማግኘት መፈለግ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። በእዚህ መካከል በርካታ ችግሮች ይገጥማቸዋል። ለአብነትም የሚሄዱባቸው የመጓጓዧ አማራጮች በአደጋ የተሞሉ መሆን፣ በመንገድ ላይ የሴቶች መደፈር፣ የጉዞ መረጃ ስለማይኖራቸው በድንበር አሻጋሪ ነን ባዮች ላይ ጥገኛ መሆን፣ በእነርሱም መደብደብና ንብረት መዘረፍ ከሚታዩ ችግሮች መካከል በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

በተለይም ባህር አቋርጦ ድንበር ለመሻገር የሚደረገው ሙከራ እጅግ አስከፊ ከሚባሉት የጉዞ አማራጮች መካከል ተጠቃሹ ነው። ጀልባዎቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁና የዓሣ ማጥመጃ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ በማዕበል የመመታት ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው። በእዚህ ወቅት ደግሞ «ነገ ያልፍልንና የራሳችንን እንዲሁም የቤተሰቦቻችንን ሕይወት እንቀይራለን» የሚል ተስፋ ያነገቡትን ተጓዞች ይዛ ትሰጥማለች። ለምስክር የሚሆን ሰው እንኳን በማይገኝበት መልኩ ሁሉም ነገር በባህር ውስጥ ከንቱ ሆኖ ሊቀር ይችላል።

ይህንን ሁሉ መከራም አልፎ እንኳን የታሰበበት አገር የመድረስ ዕድሉ ቢገኝ በድንበር ላይ ያሉ ሌሎች አሻጋሪ ነን ባይ ህገ ወጦች ተደራጅተው መጠበቃቸው አይቀርም። እነዚህም ከስደተኞቹ ገንዘብ ለመንጠቅ ተዘጋጅተዋልና ልክ እንደደረሱ «እጅህ ከምንየሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ያለው ይከፍላል። የሌለው ወደ ቤተሰቡ ስልክ ደውሎ ገንዘብ እንዲላክ ያደርጋል። «ይህንን አላደርግም» ያለ በግፈኞች እጅ የሞትን ጽዋን ሊጎነጭ ይችላል።

ድብደባ፣ በእሳት ማቃጠል፣ አስገድዶ መድፈርና ረሃብ እንዲሁም መሰል ኢ ሰብአዊ ድርጊቶችን መፈጸም የህገወጦቹ የዕለት ተዕለት ሥራ ሲሆን «ነገ ያልፍልኛል» ያለው ወገን ደግሞ ሕይወቱ እስክታልፍ ድረስ መጋፈጥ ግዴታው ነው።

የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መረጃን ተንተርሰን በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያውያንን ሁኔታ ብንመለከት ወደ ሳውዲ አረቢያ መሸጋገሪያ በሆነችው ሰሜን ምሥራቅ የመን 4 ሺ የሚጠጉ ዜጎች በቀን ለአንድ ጊዜ ብቻ እየተመገቡ በጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል። እነዚህ ሰዎች የምግብ ማጣታቸውና ለረዥም ሰዓት መስራታቸው ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው ይልቁንም ተፋፍገው በመኖራቸው በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተያይዘው ማለቃቸው እንጂ።

አሁንም ይህ ዓይነቱ አሰቃቂ የሰው ልጆች ኑሮ እየተባባሰም ማብቂያ የለሹ ፍልሰት ግን ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ብዙ ሺ ዎች በየዕለቱ በህገወጥ ደላላ አማካኝነት ከአገር የመውጣት ሙከራ ያደርጋሉ። እስከ አሁን የተሳካለት አለ የሚል መረጃ ለጆሯችን ቢናፍቀንም የሞቱና የጠፉ ሰዎች ዜና ግን ዘወትር የሚደመጥ ሆኗል።

በሰዎች መነገድ እንዲሁም በሕገ ወጥ መልኩ ከአገር ወደ አገር ማሸጋገር በአገሪቱ ሕግ ፍፁም የተከለከለ ቢሆንም አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች በማሸጋገር ሥራ ላይ ተሰማርተው ብዙዎችንም ከንቱ ተስፋና የህልም እንጀራ እየመገቡ ለስቃይና መከራ እየዳረጉ ይገኛሉ።

በተለይም በየቀኑ በርካታ ሴቶች የሚሄዱባቸው የአረብ አገራት አሁን አሁን የስቃይና የዋይታ ምድር እየሆኑ የመጡ ይመስላል። ብዙዎች «ያልፍልናል» ብለው ቢሄዱም በተቃራኒው አካላቸውንና ሕይወታቸ ውን ይገብራሉ። ከዚህ አሰቃቂ አደጋ ተርፈው ለአገራቸው መሬት ሲበቁም መልሰው የአገርና የቤተሰ ብም ሸክም ስለሚሆኑ የሚከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ቀላል አይደለም። 

በሰው ቤት ሠራተኝነት ለመቀጠር ከአገር የመውጣት በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገው ጉዞ በኢትዮጵያ የተጀመረ አይደለም። የበርካታ አገር ዜጎች ይህንን የሥራ ዕድል ለመጠቀም ከአገራቸው ይወጣሉ። በተለይ ደግሞ እንደ ፊሊፒንስ የመሳሰሉ አገሮች ዜጎች በብዛት ወደ አረብ ሀገራት ለሥራ ይጓዛሉ። ጉዟቸው በመከራ እንዳይሞላ የአገራቸው መንግሥትና ኃላፊነት የሚሰማቸው አካላት የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ነው።

እነዚህ ዜጎች ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት ከሚደረጉላቸው ነገሮች አንዱና ዋናው ስለሚሄዱበት አገር ባህል፣ቋንቋና መሰል ሁኔታዎች እንዲረዱ ስልጠና መስጠት ነው። ስልጠናውን ማግኘታቸው ደግሞ ከኢትዮጵያውያን በተሻለ መልኩ ከአሰሪዎቻቸው ጋር እንዲግባቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። 

በእዚህ ምክንያትም የሚደርስባቸው ችግር እዚህ ግባ የማይባል ሊሆን ችሏል። ኢትዮጵያውያን ግን በመጀመሪያም ቢሆን በስነ ልቦናና በክህሎት ዝግጅት አድርገው ስለማይሄዱ በደመወዝ፣ በሥራ ይዘትና ጥራት እንዲሁም ከአሰሪዎች ጋር በሚኖር የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ አለመግባባት ይፈጠራል። በእዚህ ደግሞ ስነ ልቦናቸው ይጎዳል፤ የቋንቋና የባህል አለመገናኘቱ ሲጨማመር ደግሞ ችግሩ ይባባሳል። በመሆኑም በሕገ ወጥ መንገድ ብቻ ሳይሆን በሕጋዊው መንገድ ሄደው ሊቸገሩ ይችላሉ።

ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደውጭ የሚሄዱ ሠራተኛ ዜጎች መለስተኛ ስልጠና አግኝተው ለሥራ ከአገራቸው የሚወጡበትን መንገድ ለመቀየስም ይፋ ያደረገው ሰነድ አለ። አንዳንድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችም በመጀመር ላይ ናቸው። ይህ ጅምር መልካምና የብዙ ዜጎቻችንን ስቃይ ሊያቃልል የሚችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። አልያ ግን ችግሩ እየተባባሰ ዜጎቻችንም የአሞራ ቀለብ እየሆኑ ይቀራሉ።

በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይ ኦ ኤም)መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትና በሰዎች የመነገድ ወንጀል መከላከል ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት አቶ ታገል ሰለሞን ጉዳዩን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ። «በአሁኑ ወቅት በተለይም ሴቶች ለሥራ በሚል ሰበብ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት በብዛት ይጓዛሉ፤ ሆኖም መድረሻቸው ሳይታወቅ የሚቀሩትም በርካቶች ናቸው። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይም ወደ ደቡብ ሱዳን የሚደረግ ስደት ትክክለኛ አሀዙን መግለጽ ባይቻልም እየተበራከተ መጥቷል። ይህም በጊዜ እልባት ካላገኘ እጅግ አስቸጋሪና ውስብስብ የማይሆንበት ምክንያት የለም። ለምሳሌ በአለፈው ዓመት ብቻ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ በመቶ ሺ ዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ የመን ገብተዋል። ከዚህ መካከልም 75 ሺዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተረጋግጧል።»

በእዚህ ዓመትም ቢሆን በርካቶች ወደ ተለያዩ አገራት እየተሰደዱ ነው። በመሆኑም መንግሥት በብዛት ከሚያመቻቻቸው የሥራ ዕድሎች ባሻገር የኅብረተሰቡን ብሎም የቤተሰብን ግንዛቤ ማስፋትና ስለ ጉዳዩ አስከፊነት እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል የአቶ ታገል የማጠቃለያ ሀሳብ ነው። «ስደት አንዳንድ መልካም ጎኖች ያሉት ቢመስልም የሚያመዝነው አስከፊው ገጽታው ነው። ሆኖም በየጊዜው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤተሰባቸው፣ ከትዳር አጋራቸው እንዲሁም ሕፃናት ልጆቻቸውን ትተው ይሰደዳሉ። ይህ ደግሞ በአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ጫናን ማሳደሩ ግልጽ ነው። 

በመሆኑም ይህንን ሁኔታ በአግባቡ በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ቤተሰብ ተባብረው መስራት አለባቸው። በተጨማሪም የሚሄዱት ሰዎች ቢያንስ ስለሚሄዱበት አገር በቂ መረጃ እንዲይዙ፣ ቋንቋ እንዲማሩና መሰል ጉዳዮችን እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን አሁንም ሞት፣ የአካል ጉዳትና መሰል አስከፊ ነገሮች መታየታቸውና መሰማታቸው አይቀርም»
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment