Tuesday, February 26, 2013

ለፓትርያርክነት ከተጠቆሙት ሊቃነ ጳጳሳት አምስቱ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቀረቡ

(Feb 26, 2013 አዲስ አበባ)--የስድስተኛው የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ለፓትርያርክነት የተሰጡትን ጥቆማዎች በዕድሜና በሌሎች መመዘኛ መስፈርቶች መሠረት በማጣራትና ሰፊ ውይይት በማድረግ አምስት ሊቃነ ጳጳሳትን ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቀረበ።

ኮሚቴው ሰፊ ጊዜ ወስዶ ባደረገው ማጣራት የተለዩት አምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዕድሜ 71፣ የሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዕድሜ 75፣ የባሌ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ዕድሜ 61 ፣የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ፣ የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ፣ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ዕድሜ 59እና የወላይታና ዳውሮ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ዕድሜ 50 ናቸው።

ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የተሰጠውን መግለጫ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ና የአርሲ አገረ ስብከት በፀሎት ያስጀመሩ ሲሆን፣ የጅማ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መግለጫውን ሰጥተዋል። 

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ካህናትና ምዕመናን ለስድስተኛው ፓትርያርክነት ይሆናሉ የሚሉትን በምርጫ ህገ ደንቡ መሰረት ጠቁመዋል። በህገ ደንቡ መሰረት ዕድሜያቸው ከ75 በላይና እና ከ50 በታች የሆኑት አባቶች በምርጫው እንዳይገቡ ተደርጓል። በተደረገውም ማጣራት 2 791 ጥቆማዎች ለኮሚቴው ደርሶታል። ለፓትርያርክነት የተጠቆሙ ብፁዓን አባቶች ቁጥር 36 ሲሆኑ 15ቱ የጥቆማ ወረቀቶች በአግባቡ ባለመሞላታቸው ኮሚቴው ሳይቀበላቸው ቀርቷል።

19ኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ በተደረገው ማጣራት አስመራጭ ኮሚቴው የለያቸው ስምንቱን ሲሆን፣ በተጨማሪ በተደረገው ማጣራት ደግሞ አምስቱን ለይቶ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በማቅረቡ ይሁንታን ማግኘቱን ሰብሳቢው ተናግረዋል። 

እንደእርሳቸው ገለፃ በቀረቡት ብፁዓን አባቶች ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ ከ53 አህጉረ ስብከት የሚወከሉ የካህናት፣ የምዕመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ተወካዮች ፣ የማህበረ ቅዱሳን ተወካይ፣ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉ መራጮች ምርጫውን የሚያከናውኑ ይሆናል። ምርጫውም ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2005 .ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ይከናወናል። መራጮችም በመግባት ላይ ናቸው።

ሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እግዚአብሄር አምላክ የወደደውንና የፈቀደውን አባት ይጠብቅና ያሰማራ ዘንድ በመንበሩ እንዲያስቀምጥ ከትናንት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተገኙ ፀሎት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።መላው ካህናትና ምዕመናንም በእጩነት ከቀረቡት አባቶች ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ እንዲሰጥ ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ በፆምና በፀሎት ፈጣሪያቸውን እንዲጠይቁም አሳስበዋል።

ምርጫው ህገ ደንቡን ተከትሎ መካሄዱን ለመታዘብ የአራቱ እህት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ሦስት የመንግሥት ተወካዮችና ሦስት የአገር ሽማግሌዎች ደብዳቤ ደርሷቸዋል ሲሉም ገልፀዋል።ምርጫውም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጥያቄዎች የቀረበ ሲሆን፣ በተለይም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በምርጫው መሳተፍ ምክንያቱ ምንድን ነው ለተባለው ከቀድሞ ፓትርያርክ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ከዚህ ቀደም ግብፅ ባካሄደችው ምርጫ ተሳታፊ እንደነበረች ሰብሳቢው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን 

Related topics: 
 Home

No comments:

Post a Comment