Thursday, February 13, 2020

ፍቅረኞች ሁልጊዜም ቀናቸው ነው (በዳንኤል ወልደኪዳን)

(Feb 13, 2020, (አዲስ አበባ))--በአንድ ወቅት የሮም ንጉሥ አንድ አዋጅ አወጣ። ወቅቱ የጦርነት ስለነበር ለጦርነት የሚመለመሉ ወንዶች ትዳር የሌላቸው እንዲሆኑ ፈለገ። ምክንያቱ ደግሞ ትዳር የሌላቸው ወንዶች ወታደር ሲሆኑ ደፋር ይሆናሉ።

ትዳር ያላቸው ወንዶች ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ስለሚያስቡ በጦርነት ወቅት በድፍረት መዋጋት አይፈልጉም የሚል ነበር። በመሆኑም ማንኛውም የሮማ ግዛት ወጣት ትዳርም ሆነ ፍቅረኛ እንዳይኖረው የሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሮማው ንጉሥ እንዲወጣ ሆነ። 

የንጉስ አዋጅን ማስፈጸም የተለመደ ቢሆንም ቄስ ቫላንታይን ግን አዋጁን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም። እናም የንጉሡን አዋጅ ሽረው በድብቅ ፍቅረኞችን ያጋቡ ጀመር። ድብቁ ነገር ሲቆይ የአደባባይ ምስጢር ሆነና ገሀድ ወጣ። ንጉሡም በድብቅ ሲያጋቡ የቆዩት ቄስ ቫላንታይን ተይዘው እሥር ቤት እንዲወረወሩ አደረጉ። 

ቄስ ቫላንታይን የንጉሡን አዋጅ ሽረው ፍቅረኞችን በማጋባታቸው ለእሥር ሲዳረጉ ወጣት ፍቅረኛሞች አይተውና ሰምተው ዝም አላሏቸውም። በድብቅ እየሄዱ ይጠይቋቸውና ያጽናኗቸው ነበር። በእሥር ቤት ቆይታቸው ከሚጠይቋቸው ቆነጃጅት መካከል የእሥር ቤቱ ተቆጣጣሪ ልጅ አንዷ ነበረች። 

ቄስ ቫላንታይን በእስር ቤት ቆይታቸው ከእሥር ቤት ተቆጣጣሪው ልጅ ፍቅር ይዟቸው እንደነበር ይነገርላቸዋል። ቄሱ በእሥር ቤት ቆይታቸው ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ለፍቅረኛቸው የፍቅር ደብዳቤ ጽፈው ነበር። በደብዳቤው መጨረሻ ላይ «ያንችው ቫላንታይን» የሚል አረፍተ ነገር ጽፈውና ፈርመውበት ነበር። 

ይህ ነው እንግዲህ ለቫላንታይን ቀን ወይም ለፍቅረኞች ቀን መከበር ምክንያት በአፈታሪክ የሚነገረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት መከበር ጀመረ። በሕንድ እ..አ ከ1960 ጀምሮ የሚያዋህድ ቀን በማለት ያከብሩት እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጂ እ..አ ከ2004 ጀምሮ የምዕራባውያን ባህል ነው በማለት እንዳይከበር አድርገዋል። ያም ሆኖ ብዙዎች በዓሉን ተቀብለውት ስለነበር በአንድ ጊዜ ለማስቆም እንዳልተቻለና እንዳንድ ወጣቶች ዛሬም ድረስ እያከበሩት እንደሆነ ይነገራል። 

ሳውዲ አረቢያና ፓኪስታንም እየተቃወሙት እንደሆነ ነው የሚነገረው። በዕለቱ ቀይ አበባና ሌሎች ቀያይ ነገሮች እንዳይሸጡ መከልከላቸውም እየተዘገበ ነው። ኢራን ውስጥም ቀደምት ባህሎቻቸው የሆኑ የፍቅር ጓደኝነት ቀንና የምድር ቀን የሚባሉት በዓላት እየተዘነጉ በመምጣታቸው ምክንያት የቫላንታይንስ ዴይ እንዳይከበር እያደረጉ ነው። ይህንኑ ቀን ብሔራዊ በዓል አድርገው ከራሳቸው በዓል ጋር አስተሳስረው ለማክበርም ጥረት እያደረጉ መሆኑ ነው የሚነገረው። 

የቫላንታይንስ ዴይ ወይም የፍቅረኞች ቀን በፊኒላንድ «ፍሬንድስ ዴይ» በሚል ፍቅረኛሞች ብቻ ሳይሆኑ ወዳጅ ዘመዶችና ጓደኞቻቸውን ጨምረው ያከብሩታል። በሜክሲኮ፣ በጓቲማላ፣ በኤልሳልቫዶር «ዴይ ኦፍ ላቭ ኤንድ ፍሬንድስ» በማለት እለቱን ያከብሩታል።

በቀይ ቀለሞች የሚደምቀው የፍቅረኞች ቀን በአገራችንም እየተዘወተረ መጥቷል። በከተሞች እለቱን የሚዘክሩ ዝግጅቶችን በማካተት የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅት ይደረጋሉ። በልብስና በስጦታ መሸጫ ሱቆች በሙሉ ቀያይ ነገሮች ለገበያ ይቀርባሉ። ቀያይ ጽጌረዳ አበቦችም በብዛት የሚቸበቸቡበት በእዚሁ ወቅት ነው።

የፍቅረኞች ቀን በሀገራችን መከበሩ እስከአሁን ተቃውሞ አላጋጠመውም። ምክንያቱም በግሎባላይዜሽን ዘመን እንደዚህ ዓይነት መልካም ነገሮች ወደ ማኅበረሰቡ የመዳረሳቸው ነገር የማይቀርና የሚጠበቅ ነው። የከፋ ነገር እንኳ ባልተጠበቀ ፍጥነት የኅብረተሰቡን አመለካከት መበረዙ አልቀረም። በመሆኑም ማኅበራዊ ድረ ገጾች በበዙበትና ተጠቃሚዎቻቸውም የትየለሌ በሆኑበት ወቅት ከእውነታው ጋር መጋፈጥ የግድ ነው። ለመልካም ነገሮች ቅድሚያ መስጠቱ ከጉዳቱ ጥቅሙ ነው የሚያመዝነው።

የፍቅረኞች ቀን መልካም ነገራቸው አመዝኖ ፍቅረኛሞች ስለ ፍቅራቸው የሚወያዩበትና የፍቅር ስጦታዎችን የሚለዋወጡበት ወቅት በመሆኑ ፈጥነን ልንቀበለው እንችላለን። በተቃራኒው አቅጣጫ ተጉዞ የፍቅረኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ መልካም ላልሆኑና ባህልን ለሚበርዙ አስተሳሰቦች የምናውለው ከሆነ ደግሞ «እዚያው በጠበሉ» ልንለው ይገባል። ምክንያቱም የሌሎችን ባህል እንዳለ ወስዶ የሚቀበል ማኅበረሰብ ከራሱ ነገሮች ጋር የሚጣላበት መንገድ ብዙ ነውና። እኛ ልንቀበለው የሚገባን የሚጠቅመንንና የሚያስፈልገንን ብቻ ቢሆን ነው የሚበጀው። 

ፍቅርን የሚጠላ የለም። የሁሉም ነገር ማሰሪያው ፍቅር ነው። ፍቅር ያለው ሰው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት አይቸገርም። የሚያንኳኳቸው በሮች ሁሉ ይከፈታሉ። ስለዚህ ለፍቅር አንድ ቀን ሰጥቶ ማክበሩ ክፋት አይኖረውም። ብንችል በዓመት አንድ ቀን ጠብቀን ሳይሆን እለት ከእለት ስለፍቅር እያሰብንና ስለፍቅር እያወራን ብናሳለፈው መልካም ነበር። 

ፍቅረኞችም ሁል ጊዜ ቀናቸው ነው። ስለዚህ ስጦታዎች የምናበረክተውና እንደምናፈቅራቸው የምንነግራቸው የፍቅረኞችን ቀን ጠብቀን መሆን የለበትም። ፍቅር ጊዜና ቦታ የማይወስኑት ለነገሮች ሁሉ የማይንበረከክና እጅ የማይሰጥ አልፎም በአሸናፊነትን የሚጐናፀፍ ነው። ለእዚህም ነው አንላንደርስ የተባለው ምሑርም «ሕይወትህ ፍቅር ካለው ያጣኸውን በርካታ ትላልቅ ነገሮች ያካክስልሃል። ፍቅር ከሌለህ ግን የፈለገው ነገር ቢኖርህ እርካታ አይኖርህም» በማለት ሃያልነቱን የገለጸው። ሁልጊዜም የፍቅር ሰው ያድርገን። 
ዳንኤል ወልደኪዳን
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment