Friday, January 18, 2013

«እውነትን ያረጋገጠ ሐቅ» (Written by ፀሐይ ነኝ)

(Jan 18,2013, by ፀሐይ ነኝ, Addis Ababa)--ለአገራችን እድገትን ሳይሆን ውድቀቷን፣ አንድነቷን ሳይሆን መበተኗን፣ ፍቅሯን ሳይሆን ጠቧን የሚመኙላት ከአብራኳ የወጡት ልጆቿን ጨምሮ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ማየትና ማገናዘብ ተስኗቸው ሁሌም ምላሳቸው ሠማን አልሠማንም፤ አየን አላየንም በማለት እውነቱን ለማደብዘዝ ያልሮጡበት ሜዳ፣ ያልቧጠጡት ዳገት የለም፡፡

«ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም» ይላል የአገሬ ሰው፤ እንደ አለመታደል ሆኖ የአገራችን ተቃዋሚዎች ፀሐይ የሞቀውን እውነት በመቀበል ባሉት ክፍተቶች ላይ መሥራት ሲገባቸው የተሠራውን የማጥላላት አባዜ ተጠናውቷቸዋል፤ ይህ አካሄድ ደግሞ ለአገር እድገት ፀር እንጂ የመፍትሔ መንገድ ሊሆን በጭራሽ አይችልም፡፡

ለአገር እና ለህዝብ የሚያስብ ግን ከመንግሥት ጐን በመሆን ክፍተቶች እንዲሞሉ አማራጭ መንገዶችን ለህብረተሰቡ በማሣየት በጋራ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ አብሮ በመሥራት ተወዳዳሪ መሆን ሲገባ የህብረተሰቡን ስስ ስሜት በመነካካት እውነታውን በመሸፈን ለማደናገር ቢሞክርም እውነታው ተሸፍኖ አይቀርም፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ለራሱ ለሚቃወመው አካልም ጠቃሚ አይደለም፡፡ 

አገራችን በእድገት ጐዳና ላይ መሆኗን ለማመን ለረጅም ጊዜ ተስኗቸው ከነበሩት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አንጋፋ ድርጅቶችም ይገኙበት ነበር፡፡ ታዲያ «እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል» እንዲሉ እነሆ የዓለም ባንክ በዚሁ ዓመት በታህሣሥ ወር ኢትዮጵያ ለተከታታይ ሰባት ዓመታት 10ነጥብ6በመቶ እድገት እንዳስመዘገበችና ይህ እድገትም ከሠሀራ በታች ያሉ አፍሪካ አገሮችን እድገት በጥፍ የሚበልጥ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ አካትቶ አቅርቧል፡፡ 

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር የሆኑት ጓንጅ ዚቺን እንደገለጹት የተመዘገበው እድገትም 2ነጥብ5 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢትዮ ጵያ ሕዝቦች ከድህነት መላቀቅ መቻላቸው በሪፖርቱ ላይ የተካተተ ሲሆን የድህነት ወለልም 38 ነጥብ7በመቶ ወደ 29ነጥብ6በመቶ መቀነስ መቻሉን መመስከር ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚሁ በጀት ዓመት ድህነትን ወደ 22ነጥብ2በመቶ ለመቀነስ የያዘውን እቅድ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሣት መሳካት የሚችል እቅድ በማለትም አሞካሽተ ውታል፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ኢኮኖሚስት እንዲሁም ከሪፖርቱ ጸሐፊዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት ሚካኤል ጊገር የኢትዮጵያን የዕድገት ሁኔታ ሲያብራሩ በዋናነት ኤክስፖርት መርህን አጠናክራ መቀጠል በመቻሏ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን የዕድገት አካሄዷንም በቅርቡ ውጤታማ እየሆኑ ከመጡት የምሥራቅ ኤስያ አገሮች ማለትም ከቻይና፣ ኮሪያና ታይዋንን ተሞክሮ እንደወሰደች በሪፖርቱ ላይ አካትተው አቅርበዋል፡፡

የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት እውነታው የተጋረደባቸው አካላት ላይ ብርሃን ይፈንጠቅበት ይሆን ወይስ ሪፖርቱ የወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት አስገድዷቸው ነው በማለት የተለመደ ጥላሸት በመቀባት በክስ ማህደራቸው ላይ ያሰፍሩ ይሆን? በእርግጠኝነት ከአሁን በኋላ ስህተታቸውን ላለመድገም እውነተኛ የሆነ የተቃውሞ መንገድ ይከተላሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በወጣው ሪፖርት ላይ የሚደነቅበት ሁኔታ ባይኖርም እውነቱ ይፋ በመደረጉ «እኔ የምፈልገው ይሄን ነው» የሚል ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም ኢትዮጵያ ማንንም ዋሽታ ወዳጅ፤ ዋሽታ ጠላት ማፍራት የምትፈልግ አገር አይደለችም፡፡ ስለዚህ ህዝቧንም ሆነ ሌላውን አካል ባልተመዘገበ እድገት ላይ ጉንጭ የማልፋት ሥራ መንግሥት አይሠራም፤ ለዚህም ነው በውስጥም በውጭም የሚገኙ አካላት በተመዘገበው እድገት ዙሪያ ትክክል አይደለም ብለው ለማሣመን ሲሞክሩ፤ ትክክል ነው፤ ከፈለጋችሁ ማጣራት ትችላላችሁ የሚለውን ጠንካራ አቋሙን ሊያሣያቸው የቻለበት ምክንያት እውነታው በእጁ ላይ በመሆኑ እና በየትኛውም መንገድ ቢጣራ የተመዘገበውን ዕድገት የሚያከሽፍ የሂሣብ ስሌት እንደማይኖር እርግጠኛ በመሆኑ ነው፡፡

ስለሆነም የአገራችን እድገት ወደፊትም ቀጣይነት እንዲኖረው በተለይ ከአብራኳ የወጡት ልጆቿ ተሳትፎ ከማንም በላይ ወሣኝ ነውና ሁሉም አካል ከመንግሥት ጋር አብሮ በመሥራት ሠላማዊ ውድድር ቢያደርግ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ቸር እንሰንብት፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ        Home

No comments:

Post a Comment