Friday, January 18, 2013

ወደ ዓረብ ሀገራት ስደት የስቃይ ፅዋ መጐንጨት (by አልማዝ አያሌው)

(Jan 18, 2013, አልማዝ አያሌው)--ጀማል የሱፍ የ10 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ ዛሬ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ አይቦርቅም። አይጫወትም። በቤት ውስጥ ኩርምት ብሎ ተቀምጧል። በእጁ ደግሞ መሬት ይቆረቁራል። አጠገቡ መሬት ላይ በተነጠፈ ኬሻ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምታቃስተውን እናቱን ዓይን ዓይን እያየ።

እናቱ ወይዘሮ ዘውዴ መሐመድ ወደ ሳውዲ ዓረቢያ የሄደችው የ10 ዓመቱን ጀማልንና የአምስት ዓመቱን ታናሽ ወንድሙን ትታ ነው። ትንሹ ዕድሜው ባለመፍቀዱ የትምህርት ቤት ደጃፍ ባይረግጥም ጀማል ግን ሦስተኛ ክፍል ደርሷል። የእናቱ ወደ ዓረብ ሀገር መሄዷ ግን የጀመረውን ትምህርት እንዲያቋርጥ አስገድዶታል። 

«ቤት የሚጠብቅ፣ ከብት የሚያግድ ሰው ስለሌለ አንድ ጊዜ ስሄድ ሌላ ጊዜ ስቀር ከዛን ጭርሱኑ ተውኩት» የሚለው ጀማል አሁን ደግሞ እናቱን የማስታመም ስትሰቃይ አብሮ የመሰቃየት አልፎ አልፎም ለቤተሰቡ የብስጭት መብረጃ ሆኗል። 2004 .ም ለእርሱ እጅግ የመከራ ለቤተሰቦቹም የፀፀት ዓመት ሆኖ አልፏል።

ወይዘሮ ዘውዴ ትዳርና ልጆቿን በትና ወደ ዓረብ አገር ያቀናችው ከባለቤቷ ጋር «ኑሮአችንን ለማሻሻል» በሚል ተስማምተውና ተመካክረው ነው፡፡ በሄደችበት ቦታም ችግር እንዳይገጥማት በሚል በዕውቅ ደላላ (በባለቤቷ ወንድም አማካይነት) ነው ወደ ሳውዲ ዓረቢያ ያመራችው።

«ከመንግሥት ከብት ለማድለብ በሚል አምስት ሺ ብር ተበድሬ ነበር፡፡ ከብቶችም ብዙ አልጠ ቀሙኝም። ከተለያየ ሰው አንድ ሺ ሁለት ሺ እያልኩ ገንዘብ ተበደርኩና ለባለቤቴ ወንድም ስድስት ሺ ብር ከፈልኩ። አዲስ አበባ አንዳንድ ነገር ሳስጨርስም በአጠቃላይ አሥር ሺ ብር አውጥቻለሁ። «ሁሉንም ዕዳ ሠርታ ለመክፈል ያደረገችው የዓረብ ሀገር ጉዞ ሌላ የማትወጣውን ዕዳ ውስጥ ከተታት።

ወይዘሮ ዘውዴ አልተማረችም፡፡ የምትሄድበትን ሀገር ቋንቋና ባህልም አታውቅም፡፡ «በምልክት የነገሩኝን እሠራለሁ» በሚል ድፍረት ነው ከሀገር ለመውጣት የቆረጠችው። ጐረቤት ያሉ ወጣቶች ወጣት ሚስቶች ሁሉ ሀገር እየጣሉ ሲሄድ እርሷም ተነሳች። ሆኖም ግን ሁሉ ነገር እንዳሰበችው ሆኖ አላገኘችውም።

በተቀጠረችበት ቤት ዘጠኝ ክፍሎችና አራት ክፍል መፀዳጃ ቤቶች ማጽዳት፣ ዕቃ ማጠብ፣ ልብስ ማጠብና መተኮስ የየዕለት ተግባሯ ነው። ይህንኑ ሥራ በምልክት ትታዘዛለች፡፡ ይብዛም ይነስ፣ ይርኩም አይርኩም የዕውቀቷን ያህል ትሠራለች። ይሄ ግን አሰሪዋን አላስደሰታትም። በየጊዜው ጭቅጭቅ ተፈጠረ። «ምን እንደምትለኝ ባልሰማም ቁጣ መሆኑን በደንብ እረዳለሁ፡፡ ከጭቅጭቅም በላይ ምግብ ከለከለችኝ። በተራበ አንጀቴ ሥራውን መወጣትም ከበደኝ። ይሄ ደግሞ የበለጠ ችግር ፈጠረ» ትላለች የገጠማትን መጥፎ ነገር ስታስታውስ።

ወይዘሮ ዘውዴ የገጠማትን ችግር የምታማክረው፣ ጓደኛ በደሏን የምትገልጽበት የተቀበላት ኤጀንሲ የለም። በሄደችበት ሀገርም ከአየር መንገዱ መጥቶ የተረከባት ዓረብ ነው። ስለእዚህ ከማልቀስ እና በዕድሏ ከማዘን ያለፈ የምታደርገው ነገር አልነበረም። ሆኖም ግን አንድ ቀን በእንግድነት ለመጣው ለቀጣሪዋ ልጅ «ምግብ አትሰጠኝም ተራብኩ» ስትል በምልክት ትነግረዋለች፡፡ እርሱም ምግብ አንስቶ ሲሰጣት ቀጣሪዋ ምግቡን ከእጁ በመንጠቅ እንደወሰደችበት አጫውታናለች። በሁኔታው የተናደደው ልጅም ከቤቱ ምግብ አምጥቶ እንደሰጣት ትናገራለች፡፡ «ለልጇ ስሞታ ስለተናገርኩኝ የበለጠ ተናደደች ትዝትብኝም ጀመር» ትላለች። 

«የተቀጠርኩት በ800 ሪያድ ነው። ሆኖም በቆየሁበት ሁለት ወራት ምንም አልተከፈለኝም። ጥላቻዋም እየጨመረ እያመናጨቀችና እያስራበች ስላስቸገረችኝ ለልጇ በድጋሚ ስሞታ ተናገርኩ። እናቱን በጣም ተቆጣት ። በኋላ ግን እርሱ ወደ ቤቱ ሲሄድ መኝታ ክፍሌ ድረስ ቢላዋ ይዛ ገባች። ልታርደኝ ስትተናነቀኝ ላመልጣት ብሞክርም ሁሉንም ክፍሎች ቆልፋዋለች። አንድ መስኮት ክፍት ሳገኝ «ነፍሴን ላድን» በሚል ብቻ ዘለልኩ የምትለው ወይዘሮ ዘውዴ ከመስኮት ዘልላ በመፈጥፈጧ ለወገብ አጥንት መሰበር ተዳረገች።

« ከወደቅኩ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላወቅኩም። ብቻ ልጇ ሆስፒታል ወስዶኛል። እዛ አንችልም ሲባል እርሷ መጥታ ወደ ሌላ ሆስፒታል ወሰደችኝ፡፡ እዛም ለሃያ ቀናት ተኝቼ የአንድ ወር ደመወዝ ተሰጥቶኝ በዊልቸር እየተገፋሁ «ኤጀንሲ» የተባለ አንድ ሰው ከመንገድ ላይ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰደኝ፡፡ አንድ ቀን አሳድሮም ወደ ሀገር ቤት አሳፈረኝ። «ለረመዳን ለአንቺም ሆነ ለቤተሰቦችሽ ብዙ ነገር እልክልሻለሁ፡፡ አይዞሽ ብሎ አታሎ ሸኘኝ» በማለት የገጠማትን ሁሉ ዘረዘረችልኝ።

ወይዘሮ ዘውዴ ዛሬ ሁለት እግሮቿ አይራመዱም። የወገቧ አጥንት ደቆና ወጥቶ በሦስት የብረት ድጋፍ ነው ያለችው። ሽንቷንም በካቲተር ነው የምትጠቀመው። ባለቤቷ የሱፍ ሰይድ «ይህን ሁሉ መከራ አለማየቱን እመርጣለሁ» በሚልም ሕይወቱን ለማጥፋት የፀረ ተባይ መድኃኒት መጠጣቱን ነው የመረጠው። የአካባቢው ሰዎች ሆስፒታል አድርሰው በማሳከምም «የፈጠራችሁት ሕፃን ማን ያሳድጋቸው» በማለት እንዳረጋጉት ይናገራል።
 
በቤት የቀረችውን ባለቤቱን ቁስል ለማስቀየርና ከሐይቅ ከተማ ደሴ ድረስ ኮንትራት መኪና በመያዝም በግል ሆስፒታል በየሦስት ቀኑ በማመላለስ ሕክምና ትከታተላለች። በቤት ውስጥ ያፈሩትን ንብረት እና ከብቶች ሁሉ ሸጠዋል። «የሌሊቱ ሳይሆን የቀን ጅብ በላን፡፡ አተርፍ ብለን » ሲል ይቆጫል፡፡ ይህን እያየ አንጀቱ አልችል ያለው የሀገሬው ሰውም ገንዘብ በማዋጣት፣ እርሷን በሸክም ወደ ሆስፒታል በመውሰድ እያገዟቸው ይገኛል። ' አቶ የሱፍ 'ያቺ ቀን' እያለም ይቆጫል። ባለቤቱ ወደ ዓረብ ሀገር ከሄደችበት ዕለት ጀምሮ በቤቱ ውስጥ የተፈጠረውን ምስቅልቅል ሲያስብ «ከዛሬ ነገ ሕይወቷ ይተርፍ ይሆን? በሚል ሩጫ ላይ ነኝ።» ወንድሙም የኤጀንሲውን ስልክና አድራሻ ስጠኝ ቢለው ከዛሬ ነገ እያለ ሊሰጠው አልቻለም።
ወደ ዓረብ ሀገራት የሚሄዱ ሴቶች ብዛት ከዕለት ዕለት ጨምሯል... ትምህርት አቋርጠው፣ ትዳራቸውን በትነው ከማን አንሼ በሚል የሚጓዙ በርካቶች ናቸው። ይሄ በተለያየ አካባቢ የሚታይ ጉዳይ ቢሆንም በተለይ በደቡብ ወሎ ዞን ከሌላው የከፋ ነው።

ወይዘሮ ከድጃ መሐመድ በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ ቀንዲ ሜዳ ነዋሪ ናቸው። ሦስት ሴት ልጆቻቸው ወደ ተለያዩ የዓረብ ሀገራት መላካቸውን ይናገራሉ። የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ከድጃ ሁለቱ ዱባይ አንዷ ቤይሩት የሄዱት ትምህርታቸውን አቋርጠው በእምቢተኝነት መሆኑን ነው ያጫወቱን፡፡ ሁሉም የሄዱት ትምህርታቸውን አቋርጠው ነው፡፡ አንደኛዋ ከዘጠነኛ ክፍል፣ ሁለተኛዋ ያገባችውን ባለቤቷን ትታና ትምህርቷን ከ10ኛ ክፍል አቋርጣ እንዲሁም ሦስተኛዋ ስምንተኛ ክፍል ወደቅኩ በማለት አሻፈረኝ ብላ።» 

ወይዘሮ ከድጃ ደረሱልኝ ያሏቸው ልጆቻቸው ከአጠገባቸው በመለየታቸው ትልቅ ኀዘን ላይ ናቸው። « ዛሬ ምን ይሆኑ ይሆን?» « ነገ ምን ይገጥማቸው ይሆንበሚል የሃሳብ ሰቀቀን ውስጥ ገብተዋል። «ሌት ተቀን እያለቀስኩ ነው ያለሁት» ብለውኛል፡፡ 
 
ወይዘሮ ከድጃ ከሁሉም በላይ የሚያሳስባቸው የደላሎቹና የኤጀንሲዎቹ አለመታወቅ ጉዳይ ነው። እስከአሁን ድረስ የኤጀንሲዎችን አድራሻ የሚያውቁበት መንገድ የላቸውም። ልጆቻቸው ቢጠፉባቸውም ሆነ ጉዳት ቢደርስባቸው የሚጠይቁትን አካል አያውቁም። ሁሉም ነገር የተፈጸመው በደላሎች አማካይነት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አንደኛዋ ልጃቸው (ትንሿ) ዱባይ ተቀጥራ አምስት ወራት ብታስቆጥርም አሰሪዋ ግን ምንም ዓይነት ደመወዝ እንዳልከፈለቻት ለእናቷ ነግራቸዋለች። እርሳቸውም « ይለፍልሽ ካለ ያልፍልሻል ዋናው ነገር ሕይወት ደህና ይሁን፣ በጤና ተመለሺ። ለገንዘቡ አትጨነቂ» ብለው አጽናንተዋታል።
ምክትል ኢንስፔክተር ምስጋናው ኃይሉ የተንታ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ከዞኑ አንፃር «በጣም ሰፊና ከፍ ያለ ነው» ሲሉ ያለውን ችግር ስፋት ይጠቅሳሉ። በየአካባቢው በየጐጡ በመዘዋወር ኅብረተሰቡን ለማስተማር ቢሞከርም አሁንም በተለይ ወጣት ሴቶች ትምህርታቸውን እያቋረጡ በመፍለስ ላይ ናቸው።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ዙሪያ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ቢሆንም አሁንም ፍልሰቱን ማቆም አልቻለም። በቅርቡ አንድ ደላላ በዕድሜ እጅግ ልጆች የሆኑ ዘጠኝ ሴቶችን በሚኒባስ አሳፍሮ ሲያጓጉዝ አግኝተው በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ያስታውሳሉ።

ለሕገወጥ ፍልሰቱ አንዱ ተጠያቂው የቀበሌው አመራር አካላት መሆናቸውን ያነሳሉ ኃላፊው። የቀበሌ አመራሩ መታወቂያ መስጠት የሚገባው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጐች ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ወጣት ሴቶች የመታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አልሸሸጉም። ይሄ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ መሆኑን ይገልጻሉ። በእዚህ ዙሪያ በማስረጃ የተያዙ አመራሮች የተከሰሱበት ሌሎች ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የተሰጠበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።

የወረዳው ፖሊስ በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር በተጨባጭ ተሰማርተው ያገኛቸውን ሁለት ደላሎች በቁጥጥር ስር አውሏል። በቀጣይነት ደግሞ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የፀጥታ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አመራር የችግሩን አስከፊነት ሊረባረብበት ይገባል የሚል ሃሳብ አላቸው።
የደቡብ ወሎ ዞን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ይማም እሸቱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በእግርና በባህር በመጓዝ የተለያዩ ሀገራትን ድንበር ያለሕጋዊ ፈቃድ ጥሶ መግባትን እንደሚያካትት አስታውሰዋል። ከግል ቅጥር ጋር ተያይዞ በኤጀንሲ አማካይነት የሚደረግ የሰዎች ዝውውር መኖሩንም ይጠቅሳሉ። በሁሉም መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ይናገራሉ። «የሚደበደቡ፣ የሚታሰሩ፣ ገንዘብ የሚነጠቁ ፣ የሚገደሉ ፣ የሚደፈሩ ሰዎች አሉ» በማለት የችግሩን ክብደትና ስፋት ይገልጻሉ። ከሁሉም የከፋው ደግሞ በባህርና በእግር የሚደረግ ሕገወጥ ጉዞ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም። « ብዙዎች ባህር ገብተዋል። በረሃ ላይ ሞተው ቀርተዋል» በማለት የአስከፊነቱን ደረጃ ያነሳሉ።

«ፈቃድ አላቸው በሚባሉ ኤጀንሲዎች አማካይነት በ2004.ም ከዞኑ ከሄዱት መካከል 26 ሰዎች ሞተው ከ10 በላይ የሚሆኑት አስከሬናቸው መጥቷል» ብለዋል። ከሞቱት ውጪም በሕይወት ያሉትም በትልቅ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ነው አቶ ይማም የተናገሩት። «ተቀጣሪዎቹ ገና ዓረብ ሀገራት ሲደርሱ መጀመሪያ ፓስፖርታቸው በዓረቦቹ ይወሰዳል። በባዶ ቤት እንዲቀመጡ ይደረጋል። ከሰዎች ጋር መገናኘት አይችሉም። ስልክ መደወል ይከለከላሉ። ደመወዛቸው ይነጠቃል። ይደበደባሉ፡፡ አልፎ አልፎም መጥፎ ነገር ይደረግባቸዋል» በማለት ነው እስከአሁን ከሰበሰቡት 150 አቤቱታ በመነሳት የችግሩን ስፋት ያስረዱት።
 
አቤቱታ ካቀረቡት መካከል 26 የሞቱ፣ ገሚሶቹ የአዕምሮ ሕመም የገጠማቸው ቀሪዎቹ ደግሞ ታስረናል ያሉ የሥራ ጫና የበዛባቸውና ድብደባ ተፈጸመብን በማለት አቤቱታ ያቀረቡ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመነጋገር መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ዞኑ በ2004 .ም ባደረገው ክትትል ከተለያዩ ክልሎች በደላሎች አማካይነት የወጡ አራት ሺ አምስት መቶ ሰዎች ወደ የክልላቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ነው የተናገሩት። «በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ላይ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ቤተሰቦች ናቸው» የሚል እምነት አላቸው አቶ ይማም። እናት የ15 ዓመት ልጇን 20 ዓመቷ ነው የሚል መታወቂያ ታወጣላታለች። አባት እንድትሄድ ገንዘብ ተበድሮ ይከፍልላታል ሲሉ ወላጆችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
 
«ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በዞኑ የከፋ ነው» የሚሉት ኃላፊው፣ አንዳንዱ አባወራ የልጆቹን እናት« ሄዳ ገንዘብ ታምጣ» በሚል እየሸኘ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ባለቤታቸውን እንደእነ እገሊት.. ልሂድ ልሥራና ገንዘብ ላምጣ በማለት ትዳራቸውን የሚበጠብጡና የሚረብሹም አሉ» በማለት ችግሩ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለቀጣይ የልማት ዕድገትም ትልቅ ስጋት መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም።

No comments:

Post a Comment