Thursday, January 24, 2013

የነብዩ መሐመድ 1 ሺህ 487ኛው ልደት / መውሊድ/ በዓል በመላው አገሪቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ

(አዲስ አበባ ጥር 16/2005)--የነብዩ መሐመድ 1 ሺህ 487ኛው ልደት /መውሊድ/ በመላው አገሪቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ታላቁን አንዋር መስጊድን ጨምሮ በመዲናዋ በተለያዩ ሥፍራዎች በሚገኙ መስጊዶች በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሲከበር ውሏል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት ከንጋቱ 12 ሰዓት በዓሉን ለማብሰር መድፍ ተኩሷል፡፡ 

የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች በተገኙበት በታላቁ አንዋር መስጊድ በተከናወነው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳት ሼህ ኪያር መሐመድ አማን እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት በሰላም የተስፋፋባት አገር ናት፡፡

ሙስሊሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ወዳድና ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚጠብቅ መሆኑን በዓለም ደረጃ ያስመሰከረ መሆኑን ጠቁመው በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች ጋር ተካባብሮና ተቻችሎ በመኖር የሰላም መንፈስ ተምሳሌትነቱን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡ ነብዩ መሐመድ ለሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ በጎ ማድረግን ለተከታዮቻቸው ሁሉ ሲያዙ አጠቃላይ በሆነ መልኩ እንጂ በሙስሊምና ሙስሊም ባልሆኑት በዘመድና በጎረቤት መካከል ብለው ልዩነቶችን አላስቀመጡም ያሉት ፕሬዚዳንቱ የነብዩ መሐመድ መልካምነት ለሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ላልሆኑ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ነብዩ መሐመድ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ሃሳብ የሚያደምጡ ለጥያቄዎቻቸውም በጎ ምላሽ የሚሰጡ እንደነበሩ አስታውሰው ለሁሉም ህዝቦች ፍትህ ይደረግ ዘንድ የታገሉና እጅ ላጠራቸውም እገዛን የሚቸሩ መምህር እንደነበሩም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ኡለማዎች መገኛም ከመሆኗም በላይ ሙስሊሙን ህብዝ በትክክለኛ የእምነት ጎዳና በመምራትና የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆን እስካሁን መዝለቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ራዕይ ዓላማና ተግባራት በመቅረጽ አቅጣጫም በመጠቆም ግንባር ቀደም የመሪነት ሚናውን እየተጫወተ እንደሚገኝ አመልክተው መላውን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ያለ ምንም ልዩነት በመምራት የአገሪቱ የልማት ውጤቶች ተቋዳሽ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖቱን ተከታዮች አንድነት ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረትን በመደገፍ ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ 

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለነብዩ መሐመድ ያለው ውዴታ ወደር ስለማይገኝለት የእምነቱ ተከታዮች ሰኞ መጾምን ማስለምድ የተወደደ ስራ መሆኑን ያስገነዘቡት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ አብዱራህማን ናቸው፡፡ በነብዩ መሐመድ ውዴታ ስር ሙስሊሞች እንዲሰባሰቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 
Source: ENA

No comments:

Post a Comment