Friday, November 23, 2012

የግብፅ መንግሥት በዓባይ ጉዳይ ባለሥልጣናቱ የሚሰጡት መግለጫ እንደማይመለከተው አስታወቀ

(Nov 23, 2012, Reporter)--የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገር ውስጥና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዓባይ ወንዝን በተመለከተ በግብፅና በኢትዮጵያ ወቅትታዊ ሁኔታ ላይ በተከታታይ የሚሰጡት መግለጫ እንደማይመለከተው የግብፅ መንግሥት  ለኢትዮጵያ መንግሥት አረጋገጠ፡፡ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ለኢትዮጵያ መንግሥት በደብዳቤ ማብራሪያ ልኳል፡፡ 

በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኙ አንዳንድ የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መግለጫዎች በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰውን ፖለቲካዊ መግባባት፣ የዓባይን ወንዝ በጋራ አልምቶ ለመጠቀም የተጀመረውን ጥረት የማደፍረስ አቅም ያላቸው እንደሆነ በመታወቁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ማብራሪያ መጠየቁ ታውቋል፡፡

ግብፅ ውስጥ በዓረብኛ ቋንቋ ለሚታተመው ሳምንታዊው አል አህራም የተባለ ጋዜጣ የፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ አማካሪ የሰጡት አስተያየት ለማብራሪያው መጠየቅ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡

አማካሪው የሰጡትን አስተያየት የአሜሪካው ሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎም ከሳምንት በፊት በዓባይ ፖለቲካ ዙሪያ ባወጣው ዘገባ ውስጥ አካቶታል፡፡

“ግብፅ ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ያላትን የግንኙነት ደረጃ የያዘ ሪፖርትን ከተመለከተ በኋላ ሰውዬው [ፕሬዚዳንቱ] በእጅጉ ነው የደነገጠው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የፕሬዚዳንት ሙባረክ መንግሥት የግብፅን ትልቅ ስትራቴጂያዊ ፍላጎት ቸል በማለቱ ሊጠየቅ ይገባል፤” በማለት የፕሬዚዳንት ሙርሲ አማካሪ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አል አህራም ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ስተዲስ ለተባለ የግብፅ ተቋም በዓባይ ጉዳይ በከፍተኛ ባለሙያነት የሚያገለግሉት ሃኒ ራስለን የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ “ለኃይል ማመንጫ ተብሎ በዓባይ ወንዝ ላይ እየተሠራ ያለው ግድብ ተጠናቀቀ ማለት ኢትዮጵያ የግብፅ ጠላት መሆኗን አረጋገጠች ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የግብፅን ደኅንነት፣ ልማትና የሕዝቦቿን የገቢ ምንጭ የሚፈታተን ነው፤” በማለት ገልጸዋል፡፡

በማከልም “ግብፅ ይህንን የተጋረጠ አደጋ ለመከላከል እስከ ጦርነት የማንሳት ዕርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ መብት አላት፤” ብለዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ እነዚህንና ሌሎች የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚጎዱ መግለጫዎችን የሰጡበት ምክንያት ያልገባቸው የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ ከግብፅ መንግሥት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በይፋ መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ባለሥልጣናቱ ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ ከሁለቱ አገሮች የትብብር መንፈስና ፖለቲካዊ መግባባት ጋር ይጋጫል፤” ያሉት ተጠባባቂ ሚኒስትሩ፣ ላቀረቡት የማብራሪያ ጥያቄ ከግብፅ አቻቸው ባለፈው ሳምንት ደብዳቤ እንደተላከላቸው አረጋግጠዋል፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት የሰጡት መግለጫ የግብፅን አቋም ፈጽሞ እንደማያንፀባርቅና ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ መግለጫዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት እንደማይሰጡ የደብዳቤው ይዘት ይገልጻል ሲሉ አምባሳደር ብርሃነ አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ በግብፅ ባለሥልጣናት በኩል የተሰጠውን ዓይነት መግለጫ በኢትዮጵያ በኩል እንደሌለ ገልጸው፣ ወደፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች የሁለቱን አገሮች በጋራ የመሥራትና የመተባበር መንፈስ የሚያደፈርስ አስተሳሰብ አያንፀባርቁም ብለዋል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment