Thursday, November 29, 2012

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት ሚኒስትሮች ሹመትን አጸደቀ

(አዲስ አበባ ህዳር 20/2005)--የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ኃላፊዎች ሹመትን አጸደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው የ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ስብሰባ የሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የንግድ ሚኒስትርና የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮችን ሹመት አጽድቋል።

በዘህም መሰረት አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዘርፍ አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር፣ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን መገናኛና ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል። ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲኖሯት ያስቻለ ሹመት ሆኗል፡፡

እንዲሁም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የንግድ ተጠባባቂ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ የንግድ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። 

ተሿሚዎቹ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በፖለቲካ አመራር ብቃታቸውና ባላቸው የስራ ልምድ ለኃላፊነቱ የተመረጡ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሁን የተካሄደው ሹመት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ለማጠናከር፣ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብና የመተካካት ሥርዓቱን ለማጎልበት ነው። 

ሹመቱ በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ የጸደቀ ሲሆን ተሿሚዎቹም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ ተገኔ ጌታነህ አማካይነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪ ምክር በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካካል 4ኛውን የመንገድ ዘርፍ ልማት ለሚደግፈው የትራንስፖርት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። 

በኮቶኑ የተፈረመውን የአፍሪካ ካሪቢያን ፓስፊክ (አካፓ) አገሮችና የአውሮፓ ኅብረት ትብብር ስምምነት ሁለተኛ ማሻሻያ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅም ለዝርዝር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና የዕጽዋት ዘር ረቂቅ አዋጅን ደግሞ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን ኢዜአ ዘግቧል። 
Source: ENA

1 comment:

Anonymous said...

what is the educational stage of the ministers in ethiopia

Post a Comment