Saturday, September 22, 2012

አቶ ኃይለማርያም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጸሙ

(አዲስ አበባ መስከረም 11/2005)--አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ቃለ መሃላውን የፈጸሙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የአራተኛ ዓመት ሁለተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡



ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ እንደተናገሩት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ከኢህአዴግና ከሕዝቡ ጋር በመሆን በጽኑ መሠረት ላይ ያስቀመጡትን የግንባታ ሂደት አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ የጋራ አመራር መርህን በማጎልበትም የተጀመሩትን የልማትና የዴሞክራሲ ድሎች በተነደፈው ፖሊሲና ስትራቴጂ መሠረት በየወቅቱ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሄ በማፈላለግና በመስጠትም የሕዝቡን ትግል እንደሚያስተባብሩ ገልጸዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሩን የዘመናዊ ግብርና ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ሥራ አመለካከቱን ለመለወጥ፣ ክህሎቱንና በተግባራዊ የጎልማሶች ትምህርት በመታገዝ ዕውቀቱን ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ 

''የሰብል ልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፤ ለዘላቂ ግብርና ልማት መሠረት የሆነውን የተፋሰስ ልማትና በመስኖ ውሃ የታገዘ ግብርና ልማት የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡ 

ትምህርትና ስልጠናን አስመልክቶ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና የሙያ ማህበራት ለልማትና የዴሞክራሲ ባሕልን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት በፖሊሲ ጥናትና ምርምር የማይተካ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አቶ ኃይለማርያም አሳስበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረትና የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የተጀመሩት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድና የከተማ ባቡር መሠረተ ልማት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሚቻለው ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡ 

በአገር ውስጥ ያለው የንግድ ሥርዓት ቀልጣፋ ባለመሆኑና በሌሎችም ተጓዳኝ ምክንያቶች ከፍ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት ቢቀንስም፤ የሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ይህንኑ የሚያስተካክሉ እርምጃዎች እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ የመልካም አስተዳደርን አስመልክቶ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ እንግልቶችንና ከዚሁ የሚመነጩ እሮሮዎችን ለመቀነስና በሂደት ለማስወገድ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተጀመረው የለውጥ ሠራዊት ግንባታ ሕዝቡን በማሳተፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡ 

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ባህል መጎልበት የማይተካ ሚና የሚጫወቱት ነፃ የብዙሃን፣ የሙያ ማህበራትና ሌሎች የሕዝብ አደረጃጀቶች ጋር በቅርበት ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ "ማንኛውንም አይነት ቀቢፀ-ተስፋ በመያዝና በተለያዩ ሽፋኖች ፀረ-ሠላምና የሽብር ተግባራትን ለማከናወን የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ዛሬም እንደወትሮው ከሕዝባችን ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋችና ሠላማዊ አገር መሆኗን አስመስክረን እናረጋግጣለን" በማለት ተናግረዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈጣን፣ ዘላቂና በየደረጃው ሕዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እምብርት የሕዝቡ ሁለንተናዊና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የተደራጀ ተሳትፎ በመሆኑ የመላው የአገሪቱ ሕዝቦች የተጠናከረ ተሳትፎ እንዳይጓደል አበክረው ጠይቀዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቶ ደመቀ መኮንንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አድርገው በመሾም ለምክር ቤቱ አቅርበው አስጸድቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ በመጨረሻም በየዓመቱ መስከረም 14 ቀን ይከበር የነበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ምክንያቶች ስለማይከበር ጥቅምት 14 ቀን እንዲተላለፍ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ተቀብሎ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ስብሰባውን ማጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡  
Source: ENA

No comments:

Post a Comment