Wednesday, September 19, 2012

ኢሕአዴግ የመንግሥት ኃላፊዎችን የሥልጣን ዘመን በአሥር ዓመት ገደበ

(Sept 19, 2012, Reporter)--በኢሕአዴግ በወጣው የመተካካት ፖሊሲ መሠረት የመንግሥት ኃላፊዎች የሥልጣን ዘመን በአሥር ዓመት መገደቡ ተገለጸ፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው የመተካካት ፖሊሲው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች የሥልጣን ዘመን ሁለት የምርጫ ዘመን መሆኑ ታውቋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የኢሕአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን እንዳስታወቁት፣ የመተካካቱን መርሆች መነሻ በማድረግ በኢሕአዴግ የተወሰኑ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ‹‹የፓርቲ አመራር ሆኖ ለመቀጠል ዕድሜ ነው ከፍተኛ ጣሪያ የተደረገው፡፡ በፓርቲው ፖሊሲ መሠረት አንድ ሰው እስከ 65 ዓመት ድረስ ቢሠራ ብዙ ችግር የለም ብለን እንስማማለን፤›› ብለዋል፡፡

አንድ የመንግሥት ኃላፊ ሁለት የምርጫ ዘመን የማገልገል ዕድል ቢያገኝ ይጠቅማል ብለን እናምናለን ያሉት አቶ በረከት፣ በሕዝብ ቢመረጥም እንኳን ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ በሥልጣን ላይ መቆየት የለበትም የሚል የፓርቲ ውሳኔ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን ገደብ ባይመቀጥለትም፣ ኢሕአዴግ በመተካካት ፖሊሲው መሠረት ለመንግሥት የሥልጣን ኃላፊነቶች የሥልጣን ዘመን አስቀምጧል፡፡ በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን ከአሥር ዓመት በላይ እንዳይዘል ኢሕአዴግ መስማማቱን አስታውቋል፡፡ ሆኖም ግን ስምምነቱ ወደፊት በሕግ ደረጃ ስለመውጣቱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ አቶ በረከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን በተጨማሪ የሌሎች ሚኒስትሮች የሥልጣን ዘመን በተመሳሳይ በአሥር ዓመት እንዲገደብ ኢሕአዴግ መስማማቱን ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ የመተካካት ሐሳቡን ሲጀምረው ብዙ ጥናት ማካሄዱንና አገሮች እንዴት መሪዎቻቸውን ይተካሉ የሚለውን ማየቱን የገለጹት አቶ በረከት፣ ‹‹ከበርካታ አገሮች የወሰድናቸው በጐ ተሞክሮዎች ቢኖሩም፣ በራሳችን የነደፍናቸው መርሆችም አሉ፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሌሎች አገሮች የመሪዎቻቸውን ዕድሜ የማይገድቡ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ለመሪዎች የዕድሜ ገደብ ማስመቀጡን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የመሪዎች የዕድሜ ጣሪያ የሃምሳዎቹ መጨረሻ ወይም የስልሳዎቹ መጀመርያ መሆን አለበት የሚል ፅኑ አቋም አለን፡፡ አንድ ሰው እስኪደክም ድረስ መጠበቅ የለብንም፡፡ አቶ መለስ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ በስልሳ ዓመታቸው ሥልጣን ይለቁ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ባለፈው ቅዳሜ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በመሆን በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ምትክ የተመረጡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በመጪው ዓርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው በይፋ ይፀድቅላቸዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሥልጣንን ለማፅደቅ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን ለሪፖርተር የገለጹት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ናቸው፡፡

የአቶ መለስ ሕልፈትን ተከትሎ ምክር ቤቱ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን በድረ ገጻችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ለስብሰባው መራዘም ከመንግሥት የተሰጠው ምክንያት የአቡነ ጳውሎስ የቀብር ሥነ ሥርዓት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢሕአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በድርጅቱ ልምድ መሠረት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ ሆኖም ሙሉ ሥልጣናቸውን ምክር ቤቱ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ያፀድቅላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Source: Reporter
 Home

No comments:

Post a Comment