Friday, August 10, 2012

አየር መንገድ በመጪው አርብ የመጀመሪያውን ቦይንግ 787 ድሪምላይን አውሮፕላን ለመረከብ እየተዘጋጀ ነው

(Aug  10, 2012, ENA)--አየር መንገዱ የፈረንጆቹ ዓመት 2012 ከመጠናቀቁ በፊት ተጨማሪ አራት ድሪምላይን አውሮፕላኖችን ይረከባል አዲስ አበባ ነሐሴ 04/2004 የኢትዮጵያ አየር መንገድበመጪው አርብ የመጀመሪያውን ቦይንግ 787 ድሪምላይን አውሮፕላን ለመረከብ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ። 

ድሪምላይን 787 አውሮፕላን 270 መንገደኞችን የመጫን አቅም ያለው ነው አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳደግ በ2005 በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ለማጓጓዝ አቅዷል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያ የሆነው ድሪምላይን አውሮፕላን ከሰባት ቀናት በኋላ የፊታችን አርብ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ይደርሳል።

ድሪምላይን 787 አየር መንገዱ አሁን ከሚጠቀምባቸው አውሮፕላኖች አንጻር ሲታይ የነዳጅ ፍጆታ እስከ 20 በመቶ ያነሰና አካላዊ ክብደቱም በአንጻራዊነት ቀላልና ፈጣን የሚባል ነው። የአውሮፕላኑ መስኮቶች ሰፋፊ በመሆናቸው በበረራ ወቅት መንገደኞች በቀላሉ ወደ ውጭ አሻግረው ለመመልከት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው ሲሆን ውስጡ ብዙ ብርሃን የሚያስገባ፣ ሙቀትና ቅዝቃዜን ለማስተካከል የሚችል የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት እና ከአካባቢ አየር ጋር ተስማሚ እንደሆነ ዋና ሰራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።


270 መንገደኞችን የመጫን አቅም ያለው ድሪምላይን አውሮፕላን ብዙ ሻንጣዎችን መሸከም የሚችሉ የተለያዩ ክፍሎችም አሉት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን አውሮፕላን ከቦይንግ ኩባንያ ለመረከብ ለረጅም ዓመታት ሲጠባበቅ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ተወልደ ድርጅቱ ከጃፓኑ ኒፖን አየር መንገድ በመቀጠል የአውፕሮላኑ ባለቤት በመሆኑ ለአፍሪካ አህጉር ታላቅ ኩራት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የፈረንጆቹ ዓመት 2012 ከመጠናቀቁ በፊት አየር መንገዱ ተጨማሪ አራት ድሪምላይን አውሮፕላኖችን ይረከባል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ቀሪዎቹን እኤአ እስከ 2014 ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚረከብ ተናግረዋል።

አቶ ተወልደ እንዳሉት የመጀመሪያው የድሪምላይን ጉዞ ሚኒስትሮችን፣ አምባሳደሮችን፣ ጋዜጠኞችንና ሌሎች የአየር መንገዱ ደንበኞችን ያካተተ የሽርሽርና የጉብኝት ፕሮግራም ወደ ኪሊማንጃሮ ይደረጋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2004 በጀት አመት ያስመዘገበውን አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢና የተጣራ ትርፍ በተመለከተ የሂሳብ ስራው ባይጠናቀቅም 33 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 24 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር በ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ድርጅቱ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን መንገደኞችንም አጓጉዟል። አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳደግ በ2005 በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ለማጓጓዝም አቅዷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት 47 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን 69 አለም አቀፍና 17 የአገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች አሉት።

Source: ENA

No comments:

Post a Comment