Wednesday, December 28, 2011

የሆስተስ አበራሽን ዓይኖች ያጠፋው ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ

(28 Dec 2011, Reporter)--የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስተናጋጅ (ሆስተስ) የነበረችውን አበራሽ ኃይላይን ሁለት ዓይኖች ማጥፋቱ የተረጋገጠበት የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ በሞት እንዲቀጣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በቅጣት ማክበጃ አስተያየቱ ከትናንት በስቲያ ጠየቀ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን ያቀረበው ክሱን ሲመረምር ቆይቶ  ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም በተከሰሰበት ሁለት የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን በሰጠው ፍርድ ላረጋገጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግና የተከሳሽ ጠበቆች የቅጣት ማክበጃና የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ በጠየቀበት ወቅት ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ እንደገለጸው፣ ‹‹በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 117 በተደነገገው መሠረት ወንጀሉ ፍፃሜ አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት አንፃር በሞት መቀጣት አለበት፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለጠየቀው የሞት ቅጣት ሰባት የቅጣት ማክበጃዎችን ከወንጀል ሕጉ አንቀጾች እየጠቀሰ አቅርቧል፡፡ ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ራሱ ሄዶ ፖሊስ የጠራ ቢሆንም፣ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ክዶ ተከራክሯል፡፡

ድርጊቱንም የፈጸመው ወራዳነቱን በሚያሳይ ሁኔታ በቀድሞ ባለቤቱ ላይ በመሆኑ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ጨለማን ተገን በማድረግ በዕድሜ ታናሹ በሆነች ሴት ልጅ ላይ በመሆኑ፣ ጥቃቱን ሲፈጽምባት ሆን ብሎ ደም ወደ አዕምሮዋ እንዲፈስና ጉዳት እንዲደርስባት በማድረጉ፣ ሆስተስ ሆና እየሠራች ቤተሰቦቿን እንዳትረዳና እስከ መጨረሻው ሥራ እንዳይኖራት በማድረጉ፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ስለነበር ቢፋቱም በእሷ ላይ ወንጀል ይፈጽማል የሚል እምነት የሌላት በመሆኑ፣ ከፍቺ በኋላ ሳትጠራጠር በመቅረቧ ከባድ የመግደል ሙከራ ፈጽሞባታል፤›› በማለት ሌሎችንም ዝርዝር ጉዳዮች በማቅረብ ቅጣቱ ከብዶ በሞት ወይም በእድሜ ልክ እንዲቀጣ ጠይቋል፡፡

የተከሳሹ ጠበቆች የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣ ‹‹ባለፈው ቀጠሮ አቤቱታችንን በጽሕፈት ቤት በኩል አስገብተን ስለነበር ዛሬ የመጣነው መልስ ለመስማት በመሆኑ አልተዘጋጀንም፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጠበቆቹን አስተያየት ካደመጠ በኋላ፣ አቤቱታ የተባለው ከማስረጃ ጋር ግንኙነት የሌለው ከሆነ ነው፡፡ ከማስረጃ ጋር ግንኙነት ያለው አቤቱታ አልተባለም፤ ቢሮ የቀረበው አቤቱታ የችሎቱን ሒደት ሊያቋርጥ የሚችል አይሆንም፡፡ እናንተም ስትሠሩበት የቆያችሁበት ነው እንጂ አዲስ አሠራር አይደለም፡፡ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ቀጠሮ የሚሰጠው ለቅጣት ውሳኔ እንጂ አስተያት ለመቀበል አይደለም፡፡ ተመካከሩና የቅጣት ማቅለያ አስተያየታችሁን ስጡ ብሏል፡፡

ጠበቆቹ፣ ‹‹የእኛ ስህተት ነው ከተባለ እንቀበላለን፡፡ ግን አልተዘጋጀንም፤ ፍርድ ቤቱ አልተረዳችሁም ሊለን ይችላል፤›› ካሉ በኋላ ከተከሳሹ ጋር በመመካከር የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች በሰጡት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ጥፋተኛ የተባለው በወንጀል ሕጉ 27(1) እና 539(1) መሠረት ነው፡፡ በግድያ ሙከራ በማንኛውም የሕግ ደረጃ በሞት ይቀጣ አይባልም፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግን በሞት ይቀጣ ጥያቄን ተቃውመዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የቅጣት ማክበጃ ሐሳቦች በክሱ ላይ የተጠቀሱና ክሱን ያቋቋሙ በመሆናቸው በማክበጃነት ሊቀርቡ አይገባም ብለዋል፡፡ ተጎጂዋ በተከሳሽ ላይ የነበራት እምነት መባሉ አቻ ሆነው የሚኖሩ ስለነበሩ፣ አንዱ ባንዱ ላይ የሚኖር ዓይነት ሆኖ የቀረበውንም እንቃወማለን ብለዋል፡፡

ተከሳሹ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የለበትም፡፡ በዚህም ፀባዩ መልካም እንደነበር ይገመታል፡፡ በሠራው ድርጊት ተፀፅቷል፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በተጎጂዋ ላይ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ፖሊስ ሄዶ ባይናገር የበለጠ አደጋ ይደርስ ነበር፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚ ነው፡፡ ከአሥር በላይ የሚሆኑ ረዳት የሌላቸውን ወገኖቹን እንደሚረዳ በመግለጽ (ማስረጃ ሰነድ እናስገበለን) ቅጣቱ ቀሎ እንዲወሰንለት ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡  

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሐሳብ ከሰማ በኋላ፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለታኅሣሥ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የቀጠሮ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ ተከሳሹ አቤቱታ አለኝ አለ፡፡

አቤቱታውን በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቢነግረውም፣ ‹‹በጽሕፈት ቤት በኩል ተብሎ ባመለክትም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ እኔ የምናገረው እዚህ ነው፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ካልሰማኝ የት ልናገር? ሚዲያዎች ‹የምንፈራው ውሸትን ብቻ ነው› እያሉ ስለእኔና ተጎጂዋ በሌሎች ሰዎች የተሰጠ ዘገባ እያስተላለፉ ነው፡፡ ‹የሚዲያዎቹን ስም ጠቅሷል›  ለእኔም ዕድል ይሰጠኝና ልናገር፡፡ ያልተናገርኩት ብዙ ጉድ አለ፡፡ እኔ ስለቅጣቱ ችግር የለብኝም፡፡ የሴቶች ጥቃት በእኔ መቀጣት የሚቆም ከሆነ ችግር የለም፤›› በማለት ተናገረ፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በማስቆም አቤቱታውን በጽሕፈት ቤት በኩል ማቅረብ እንደሚችል፣ ከውሳኔ በኋላ በይግባኝም ቢሆን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችልና መጠየቅ ያለበት አካል ካለ እንደሚጠየቅ በመግለጽ ችሎቱ አበቃ፡፡

ሆስተስ አበራሽ ኃይላይ በቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ተከራይታ በምትኖርበት ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶባታል፡፡ ራሱ ባመጣቸው የአካባቢው ፖሊሶችና ግቢውን በሚጠብቁ ጥበቃዎች ዕርዳታ በራሱ ወጪ ኮሪያ ሆስፒታል፣ በሪፈራል ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል፣ ከዚያም ቤተዛታ ሆስፒታል ጊዜያዊ ዕርዳታ ተደርጎላታል፡፡ መስከረም 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ ባንኮክ ለሕክምና ሄዳ ሁለቱም ዓይኖቿ ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ እስካሁንም በሕክምና ላይ ትገኛለች፡፡ ዓቃቤ ሕግ በአቶ ፍስሐ ታደሰ ላይ በከባድ የሰው መግደል ሙከራና በሕግ የተከለከለን የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የወንጀል ክሶችን መሥርቷል፡፡

የሰዎች ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ካሰማና ካሳየ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ፍስሐን ተከላከል ብሎ በይኖበታል፡፡ አቶ ፍስሐም የሰዎች መከላከያ ምስክሮችና የሕክምናና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች ያቀረቡትን ማስረጃዎች ከሕጉ ጋር በማመሳከር መርምሯል፡፡ ሆኖም አቶ ፍስሐ ያቀረባቸው ምስክሮች ሁለቱ ባልና ሚስት ሆነው ሲኖሩ ይከባበሩ፣ ያስቀኑና መልካም ትዳር እንደነበራቸው ከማስረዳት ውጭ ስለተፈጠረው ሁኔታ የሚያስረዱ ሆነው አለማግኘቱን፣ የሰነድ ማስረጃውም ከደረሰው የወንጀል ድርጊት ጋር እምብዛም ዝምድና ስለሌለው፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ሊከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ 
Source: Reporter

Related topics:

No comments:

Post a Comment