Sunday, December 18, 2011

የሕክምናው ዘርፍ ክፍተትና የዲያስፖራው ሚና

(18 December 2011)--በተለያዩ ዘርፎች እንደሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ በሕክምናውም ዘርፍ በአገራችን ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ ይታወቃል፡፡ የባለሙያ እጥረት፣ የአስፈላጊ ሕክምና መሣሪያዎች እጥረት ወይም አለመኖር የታካሚዎች ከአገልግሎት ተቋማት አቅም በላይ መሆን ለአገር ውስጥ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በምክንያትነት የሚቀመጡ ጥቂት ሁኔታዎች ናቸው፡፡

በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ብቻም ሳይሆን በሕክምና ትምህርት ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደ ፒፕል ቱ ፒፕል ባሉ ድርጅቶች አማካይነት ወደ አገር ቤት የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ መንግሥት በዲያስፖራ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ አገር ቤት መጥተው የሚያገለግሉበትን መንገድ መቀየስ፣ አገሪቷም ኅብረተሰቡም ከእነሱ መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል፡፡

በዚህ ረገድ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች በግለሰብ ደረጃ አልያም በቡድን በቀላሉ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ሁሉም ያስኬደኛል ባለው መንገድ እየተጓዘ ዓላማውን ለማሳካት ሲደክም ታይቷል፡፡ ለዓመታት ብቻቸውን ደክመው በመጨረሻ በሚኖሩበት አገር ያሉ የዲያስፖራ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርን በመቀላቀል ህልማቸውን ያሳኩም ጥቂት አይደሉም፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተደረገውን የተለየ የአንገት በላይ ቀዶ ሕክምና ያደረጉት ዶ/ር በላቸው ተሰማ ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የአንገት በላይ ሕክምና ትምህርት እንዲስፋፋ፤ ዲያስፖራዎች የአንገት በላይ ቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት በፈቃደኝነት የሚሰጡበት ፕሮግራም ለመጀመር ለብቻቸው ወጥተው ወርደው ነበር፡፡ በመጨረሻ ነገሩ ለብቻ እንደማይገፋ በመረዳታቸው ፒፕል ቱ ፒፕልን በመቀላቀል ፍላጎታቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ወደ አገር ቤት መጥተው የበጎ ፈቃድ ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርጉና የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ፕሮግራሞች ቢኖሩም እነዚህ ፕሮግራሞችን በተቀናጀ መልኩ የሚያስኬድ አሠራር የመዘርጋቱ ነገር ዛሬም በሒደት ላይ ነው፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሀብት ማሰባሰብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱል ጀሊል ረሻድም ‹‹እነዚህን ፕሮግራሞች የማቀናጀትና መስመር የማስያዝ አሠራር በተቋም ደረጃ አይዘርጋ እንጂ በውጭ አገር የሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ አገር ውስጥ መጥተው የፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ቀደም ሲልም ነበር›› ብለውናል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች በተለያየ መልኩ ለአገራቸው የሕክምና ዘርፍ አገልግሎትና የሕክምና ትምህርት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡበት ተቋማዊ አሠራር የመዘርጋት ሥራ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ረገድ መረጃ ሊገኝባቸው የሚችሉ ድረ ገጾች ዲዛይን በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች እዚህ ያሉ የህክምና ተማሪዎችን በኢንተርኔት ማስተማር የሚያስችል ሲስተም ለመዘርጋት ድጋፍ ማድረጉን ለዚህ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በሚዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ላይ በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ከአቶ አብዱል ጀሊል ተረድተናል፡፡

በጤና አገልግሎት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎችን ማሳተፍ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንደተሰጠው የሚናገሩት አቶ አብዱል ጀሊል ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የአይካሳ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ከውጭ አገር መጥተው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸውልናል፡፡ ለዚህ ጉባዔ ከአሜሪካ መጥተው የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ለአንድ ዓመት ያህል ያሰባሰቧቸውን አንድ ሺሕ የሕክምና መጽሐፎችን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስረክበዋል፡፡

አቶ አብዱል ጀሊል ያሉት ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት በግልም ይሁን በቡድን አገራቸውን በሙያቸው ለማገልገል ወገናቸውን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዲያስፖራዎች በቂ መረጃ እንዲኖራቸው፣ ካለምንም ውጣ ውረድ በፈለጉትና ባሰቡት መልክ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴ ስኬታማነት በተለያዩ አጋጣሚዎች በውጭ አገር ከሚኖሩ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ውይይት መደረጉን በቢሯቸውም በፈቃደኝነት የሚያማክሩ ዲያስፖራዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ለአሠራሩ መዘርጋት ስኬት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በስፋት እንደተሄደበት ይገልጻሉ፡፡

ከስምንት ወራት በፊት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአሜሪካ አገር በሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች የተመሠረተውና ፒፕል ቱ ፒፕል የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር ኤልያስና በድርጅቱ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ላይ የሚሠሩት ዶ/ር አንተነህ ሀብቴ በሕክምና ዘርፍ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት የሕክምና ባለሙያዎች በአገር ውስጥ እንዲቆዩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በውጭ አገር የሚኖሩት የሕክምና ባለሙያዎችም በአገራቸው ሕክምና ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡበት ዕድልን መፍጠር ላይ ሊተኩሩ እንደሚገባ ገልጸው ነበር፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment