Friday, December 09, 2011

ኤርትራና አዲሱ ማዕቀብ

(07 Dece 2011, Reporter)--የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ምሥራቅ አፍሪካን እያተራመሰ ነው ባለው በኤርትራ መንግሥት ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ጥሎ ነበር፡፡ ኤርትራ እየተከተለችው ያለውን የተሳሳተ ፖሊሲ እንድትቀይር ታስቦ የተወሰደው ይህ የፀጥታው ምክር ቤት ዕርምጃ ግን ውጤት ያስገኘ አይመስልም፡፡

ቀድሞውንም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን አሸባሪ ቡድኖችን ትረዳለች በሚል ተደጋጋሚ ውንጀላ ሲቀርብባት የቆየችው ኤርትራ አሁንም ከውግዘት አላመለጠችም፡፡ ውግዘት ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በአገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረው የመሣሪያ ማዕቀብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና በውጭ አገር የሚገኘው ሀብትና ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የተወሰነባቸው ወታደራዊና ፖለቲካ መሪዎች ቁጥርም የሚጨምር መሆኑን የፀጥታው ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ የቦምብ ጥቃት ሊያካሂዱ ሲሉ በኢትዮጵያ የደኅንነት ሰዎች የተያዙ አሸባሪዎች፣ ከኤርትራ የጦር መኮንኖች ሥልጠናና ትዕዛዝ መቀበላቸውን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የወጣው የተመድ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ለአልሸባብና በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች የጦር መሣርያና የፋይናንስ ድጋፍ ይሰጣል በሚል በኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ውንጀላ ሲቀርብበት የቆየው የኤርትራ መንግሥት፣ በተመድ አጣሪ ቡድን በኩልም ‹‹አሸባሪዎችን ይረዳል›› ተብሎ ተመሳሳይ ሪፖርት ሲቀርብበት የተመለከቱ ታዛቢዎች፣ በአገሪቱ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጣል እርግጠኞች ነበሩ፡፡ እርግጠኛ መሆን ያልተቻለው በኤርትራ ላይ ምን ዓይነት ማዕቀብ ይጣላል? በሚለው ጥያቄ ላይ ነበር፡፡

በጋቦንና በናይጄሪያ ስፖንሰር አድራጊነት ተዘጋጅቶ ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ውሳኔ ሐሳብ ኤርትራ ውስጥ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች ምርታቸውን ወደ ውጭ እንዳይልኩ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኤርትራውያንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ከገቢያቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ለኤርትራ መንግሥት እንዳይሰጡ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የፀጥታው ምክር ቤት ግን የሁለቱ አገሮች የውሳኔ ሐሳብ የሚዋጥለት ሆኖ አላገኘውም፡፡ አገሪቱ ወደ ውጭ በምትልካቸው የማዕድን ምርቶች ላይ ማዕቀብ መጣል የኤርትራን ሕዝብ ስቃይ የሚያባብስ መሆኑን በመገንዘብ ማዕቀቡ ተለሳልሶ እንዲቀርብ ለመጠየቅ ተገድዷል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ሊጥለው ባሰበው ተጨማሪ ማዕቀብ ላይ ከትናንት በስቲያ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ስብሰባ ያካሄዱት አምስቱ የኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች፣ ምክር ቤቱ በኤርትራ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡

‹‹ኤርትራ በክልሉ ለሚፈጠረው አለመረጋጋት ዋነኛ ምንጭ ናት፡፡ [ይህ የማተራመስ ስትራቴጂ] አስመራ ውስጥ ያለው የተወሰነ ቡድን ከሽፍትነት ባህሪ ያለመላቀቅ አባዜ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ለዓለም አቀፍ መርህ ተገዥ ያለመሆን የሕገ ወጥነት ችግር ነው፤›› በማለት በምሥራቅ አፍሪካ ለሚፈጠረው ግጭት ዋነኛ ምክንያት የኢሳያስ አፈወርቂ አመራር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በኤርትራ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ እንዲጥል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከኢጋድ አባል አገሮች ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብለት የቆየው የፀጥታው ምክር ቤት፣ ሶማሊያንና ሌሎች የአካባቢው አገሮችን ለማተራመስ ለሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖች ድጋፍ እየሰጠች ነው ባላት ኤርትራ ላይ ሰኞ ምሽት ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል፡፡

ከአሥራ አምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገሮች መካከል አሥራ ሦስቱ አዲሱን ውሳኔ ደግፈዋል፡፡ ቻይናና ሩሲያ ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ 

ምክር ቤቱ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ላይ የጣለውን ማዕቀብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከመወሰኑና አገሪቱን ከማውገዙ ውጭ፣ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥሏል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ኤርትራን በተመለከተ በፀጥታው ምክር ቤት የተፈጠረውን ትርምስ የታዘበ ሰው ‹‹ይኼ ሁሉ ሽር ጉድ ለዚህ ነበር?›› ብሎ ቢጠይቅ አይፈረድበትም፡፡

ኤርትራ አልሸባብን ጨምሮ አካባቢውን ለሚያተራምሱ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች የፖለቲካ፣ የፋይናንስ፣ የሥልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ መስጠቷ እንዳሳሰበው የገለጸው ምክር ቤቱ፣ በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ሰጪነት ባለፈው ዓመት የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ሊፈጸም ታቅዶ የነበረውን የቦምብ ጥቃት ያወገዘ ሲሆን፣ አገሪቱ አካባቢውን በማተራመስ ለአሸባሪዎች የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ጠይቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት ግን ውግዘት በራሱ ትልቅ ጉዳት ያስከትላል፡፡

‹‹ተወገዝክ ማለት ተነጠልክ ማለት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገወጥ ሆነኸል ማለት ነው፡፡ እንደዚህ እየተባልክ ኢንቨስትመንት ወዳንተ አይመጣም፡፡ አገሮችም ከአንተ ጋር አይነግዱም፤›› በማለት፣ ውግዘት በአንድ አገር ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ያስረዳሉ፡፡ አምባሳደር ዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፀጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ለኤርትራ መንግሥት ከባድ ውድቀት ነው፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ሁሉ አሁንም የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር ይገልጻሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ ውሳኔ ማስተላለፍ ሳይሆን የማዕቀቡን ተፈጻሚነት መከታተል መሆኑን በማመልከት፡፡ አምባሳደር ዲና ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡

በአንድ አገር ላይ የሚጣል ማዕቀብ ተግባራዊ እንዲሆን አገሮች በኅብረት የሚሠሯቸው ሥራዎችና የሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች ወሳኝ መሆናቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተፈጻሚ እንዲሆን ከኢጋድ አባላት ጋር ተባብራ የምትሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከኤርትራ የማዕድን ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ምሥራቅ አፍሪካን ለማተራመስ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት ያደረበት ምክር ቤቱ፣ ኩባንያዎቻቸው በኤርትራ ውስጥ በማዕድን ሥራ ላይ የተሰማሩ አገሮች፣ ከዘርፉ የሚገኘው ገንዘብ የሽብር ተግባርን ለመደገፍ እንዳይውል ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በኤርትራ ላይ የተጣለው አዲሱ ማዕቀብ አካባቢውን በማረጋጋት ረገድ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም ምላሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ ኤርትራ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከጐረቤት አገሮች ጋር ሳትናቆር ያሳለፈችው ጊዜ አልነበረም፡፡

በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1994 ከሱዳን ጋር፣ በ1995 ከየመን ጋር፣ ከ1996 እስከ 2008 ከጂቡቲ ጋር፣ ከ1998 እስከ 2000 ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ተጋጭቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አልሸባብ ለተሰኘው አሸባሪ ቡድን ድጋፍ በመስጠት ሶማሊያንና የተቀረውን የምሥራቅ አፍሪካ ክልል እያተራመሰ መሆኑን፣ የሶማሊያና የኤርትራ የተመድ ቁጥጥር ቡድን ሪፖርት አመልክቷል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ምክር ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለውን ውጥረት በማባባስ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራ ነው ሲል አስጠንቅቋል፡፡ ሚኒስቴሩ እንደሚለው ማዕቀቡ በፀረ ሽብር ዘመቻ የዩናይትድ ስቴትስ አጋር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመጥቀም ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው፡፡

ማዕቀቡ ከመጣሉ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ አብዱ በበኩላቸው፣ ኤርትራ እያደገችና እየበለፀገች በሄደች ቁጥር የዩናይትድ ስቴትስን ጥቅምና ፍላጐት መሠረት ያደረጉ ሴራዎችና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች እየተጋረጡባት መምጣቷን ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹የታሰበው ማዕቀብ አጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካን ክልል ያተራምሳል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር፡፡  

አያይዘውም ‹‹እንደዚህ ዓይነት አፍራሽ የሆነ ማዕቀብ ወይም ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚያስቸኩል ምክንያት አለ ብለን አናምንም፡፡ ውሳኔው በኤርትራ ሕዝብ ላይ ስቃይ ለመጨመር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በአካባቢው ሕዝብ ላይም ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፤›› በማለት የማዕቀብ ውሳኔው በችኮላ እንዳይተላለፍ አሳስበው ነበር፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ድምፅ ከሰጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ በበኩላቸው፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሰላምንና መረጋጋትን ስጋት ውስጥ ከሚጥል ተግባሩ እንዲታቀብ ግልጽ መልዕክት አስተላልፈናል፣ ዓላማችን ኤርትራ ለፈጸመቻቸው ድርጊቶች የምትከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ማሳየት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ አህመድ በበኩላቸው ሟቹን የቀድሞ የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊን ሳይቀር በአማላጅነት በመላክ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለአልሸባብ የሚሰጡትን ዕርዳታ ያቆሙ ዘንድ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን ለፀጥታው ምክር ቤት ገልጸዋል፡፡

‹‹ያቀረብኩት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን [ጋዳፊ] አስታውቀውኛል፤ በአገሬ የሚካሄደው ድርድር ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የነገሯቸው መሆኑን [ጋዳፊ] አክለው ገልጸውልኛል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኤርትራ ያለው መንግሥት ሕዝቤን እያሸበረ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ አልሸባብን ከመሳሰሉ እስላማዊ ቡድኖች ጋር መንግሥታቸው ስምምነት ለመፈረም የሚያደርገውን ጥረት ኤርትራ እያደናቀፈች መሆኗን ለፀጥታው ምክር ቤት ገልጸዋል፡፡

ከኤርትራ ድጋፍ እንደሚያገኝ የሚነገርለት አልሸባብ በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጐረቤት አገሮች ጭምር የሽብር ጥቃት በመፈጸም ይወነጀላል፡፡ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሰስ ዋንታንጉላ ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹ኤርትራ የጦር መሣሪያ፣ ጥይትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለአልሸባብ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዋና አባል መሆን በሚገባት በዚህች አገር የሚፈጸመው ድርጊት በጠላትነት የሚፈረጅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አምስቱ የኢጋድ አባል አገሮች ከላይ የተጠቀሱትን ማብራሪያዎች በመስጠት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንዲወስድ ለማድረግ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን የሚሰነዘርበትን ውንጀላ በምክር ቤቱ ተገኝቶ ለማስተባበል አልቻለም፡፡ ጋቦንና ናይጄሪያ ያዘጋጁት የማዕቀብ ውሳኔ ባለፈው ጥቅምት ወር ለፀጥታው ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ጥያቄ አቅርበው የነበሩ ቢሆንም፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከምክር ቤቱ ግብዣ አልተላከላቸውም ነበር፡፡

ተሻሽሎ በቀረበውና ከትናንት በስቲያ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ኒውዮርክ ተገኝተው ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ግብዣ የተላከላቸው አንድ ሳምንት ሲቀረው መሆኑን የኤርትራ ዲፕሎማቶች ይገልጻሉ፡፡

የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ ባሳለፍነው ሳምንት ለፀጥታው  ምክር ቤት በላኳቸው ሁለት ደብደቤዎች ለአንድ ፕሬዚዳንት በአንድ ሳምንት ጊዜ ዝግጅት ወደ ኒውዮርክ መሄድ የማይቻል መሆኑን በመግለጽ፣ የምክር ቤቱ አባላት ለውሳኔ መቸኮላቸውን ተችተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቀደም ሲል በፀጥታው ምክር ቤት ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ያደረጉትን ሙከራ ያደናቀፈችው ዩናይትድ ስቴትስ ነች ሲሉም ወንጅለዋል፡፡

በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ግን ባለፈው ሳምንት ዓርብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ ጥያቄ ላቀረቡ 13 የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት በማግስቱ ቅዳሜ ቪዛ የተሰጣቸው መሆኑን በመግለጽ ውንጀላው መሠረተ ቢስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹እዚህ [ኒውዮርክ] ለመምጣት በቂ ጊዜ ነበራቸው፡፡ እዚህ ላለመገኘታቸው ምክንያት ነው ብለን የምንሰጠው ማብራሪያ የለንም፡፡ ምናልባት ዛሬ የተፈጠረውን ነገር [የማዕቀብ ውሳኔውን] ስላልወደዱት ሊሆን ይችላል፤›› በማለት የኤርትራን መንግሥት ውንጀላ አስተባብለዋል፡፡ 
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment