Monday, November 07, 2011

የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረው የተከራይ ተከራይ መመርያ

(Sunday, 06 November 2011)--የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚያስተዳድሯቸው ቤቶች ተፈጸሙ የተባሉትን ሕገወጥ ተግባራትን ሥርዓት ለማስያዝ እንዲቻል፣ ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. የወጣው መመርያ አከራይና ተከራዮችን እያፋጠጠ ነው፡፡

በመመርያው መሠረት ከመንግሥት የተከራዩትን የንግድ ቤት ለሦስተኛ ወገን ሸንሽነው የሚያከራዩ ግለሰቦች ቤቱን የሚነጠቁ ሲሆን፣ ተከራዮቹም በቀጥታ ከመንግሥት ጋር ተዋውለው ሥራቸውን መቀጠል ይችላሉ፡፡

የተከራይ ተከራይ የነበሩ በርካታ ነጋዴዎች የሚነግዱበትን ቤት መውሰድ የሚችሉበትና በቀጥታ ከመንግሥት ጋር የሚዋዋሉበት ሁኔታ በመመርያው ቢረጋገጥም፣ በተለይ ተሳስበንና ተከባብረን እንኖር ነበር የሚሉ አከራዮችና ተከራዮች፣ የመንግሥትን ዕርምጃ በጥርጣሬ ተመልክተውታል፡፡ በመንግሥት ዕርምጃ የተደሰቱ የተከራይ ተከራዮችም አሉ፡፡

የመንግሥት ቤት እንዴት እንደሚከራይ፣ እንደሚተላለፍና የአገልግሎት ዘርፍን መለወጥ ሲያስፈልግ እንዴት እንደሚከናወን መንግሥት በግልጽ በመመርያው ላይ አስቀምጧል፡፡ መመርያው የንግድና የመኖርያ ቤትን አጠቃሎ የያዘ መሆኑን ገልጾ፣ በ2003 ዓ.ም. ውል የማደስ ሥራው መጠናቀቁን ያስረዳል፡፡

የውል ማደሱ ሥራ ሲሠራ በመንግሥት ቤቶች ላይ ምን ያህል የከፋ ሕገወጥ ተግባር እንደታየ፣ ከመንግሥት በቀጥታ የተከራዩ ሰዎች ባከራዩዋቸው ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ኢሰብዓዊ ድርጊትና ብዝበዛ ገደቡን በማለፉ፣ ይህ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱን የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ይገልጻሉ፡፡

በሕገወጥ መንገድ ከሦስተኛ ወገኖች ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ገቢ የሚሰበስቡ ግለሰቦች የሚያገኙትን የጥቅም ምንጭ በማቋረጥ፣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አረጋግጠናል የሚለው መንግሥት፣ የሕዝብን ሀብት ለማስጠበቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚንቀሳቀሱ ካሉ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው ያስጠነቅቃል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment