Thursday, October 20, 2011

በአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ግምገማ ከፍተኛ ሹማምንት ከኃላፊነት ተነሱ

(19 October 2011, ሪፖርተር)--የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ አመራር ቡድን ጥቅምት 2 እና 3 ቀን 2004 .. ባደረገው ግምገማ፣ የከተማውን ምክትል ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሌላ የአዲስ አበባ የመዋቅር አባላትና ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊን ከኃላፊነት ማንሳቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የከተማውን ከንቲባንና ሥራ አስኪያጅን ያካተተው የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ አመራር ቡድን ግምገማ፣ ምክትል ከንቲባውና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘን፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ልዑል ሰገድ ይፍሩንና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ የአባላትና ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊውን አቶ ካሚል መሐመድን ከኃላፊነታቸው አንስቷል፡፡

ኃላፊዎቹ የተሰማሩበትን ዓላማና እምነት ወደ ጐን በመተው ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ የቡድን ትስስር (ኔትወርኪንግ) ፈጥረው መገኘታቸውን የግምገማ ቡድኑ ማረጋገጡን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

አላግባብ የሆነ ኔትወርክ በመዘርጋት፣ የጉራጌ ወጣት ማኅበርን ያለምንም ምክክር ብቻቸውን በማቋቋምና ከፍተኛ በሆነ የአቅም ማነስ ምክንያት አቶ ካሚል ሲገመገሙ፣ አቶ ልዑል ሰገድ ደግሞ አደራጅቶ ባለመምራት፣ ማለትም የኢሕአዴግን መዋቅር ባልተከተለ መንገድ መጓዝ፣ ብቁ ተሳታፊዎችን ማሸማቀቅና ምሁራንን አለማቅረብ በሚል መገምገማቸውን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

ግምገማው ሁሉንም የቢሮ ኃላፊዎችና ምክትሎቻቸውን ያካተተ መሆኑን የገለጹት ምንጮቹ በርካቶቹ በማስጠንቀቂያ ሲታለፉ፣ ጥቂቶቹ የሥልጣን ሽግሽግና የመታገድ ዕጣ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደርና ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊው አቶ ከፍያለው አዘዘ ምትክም ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊና በአሁኑ ጊዜ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አባተ ስጦታው መሾማቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ከፍያለው በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ከላይ እስከታች ድረስ ተገቢ ያልሆነ ኔትወርክ በመዘርጋታቸው መገምገማቸውና ለያዙት ቦታ ብቁ እንዳልሆኑ ተገልጿል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹም ለሪፖርተር እንደ ገለጹት፣ ግምገማው የተጀመረው አሁን አይደለም፡፡ ከሰኔ ወር 2003 .. ጀምሮ ለሁለት ጊዜያት የተደረገ ነው፡፡ አሁንም አልተጠናቀቀም፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ግምገማው በአንድ ነገር ላይ ያነጣጠረና ብልሹ አሠራር ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡

ችግር ያለባቸው ራሳቸው አመልክተውና አስታውቀው በሚችሉት ሙያ እንዲመደቡ ጠይቀዋል፡፡ በክፍለ ከተማና በወረዳ እየሠሩ ያሉ፣ ነገር ግን ብቃት ያላቸውና ለማዕከል መመደብ የሚችሉትም እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ሥር ያለው የውኃ፣ የፅዳትና የውበት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩበት አቶ ዓለሙ ዘበርጋ ሁለት ዓመት ሠርተው ‹‹በቃኝ መልሱኝ›› በማለታቸው ቀድሞ ወደነበሩበት የማስተማር ሥራ ተመልሰዋል፡፡

‹‹ምንግዜም ቢሆንም ቀልብ የሚስበው የላይኛው ክፍል ወይም ትላልቁ ሹማምንት ላይ ሲደርስ ብቻ ገኖ ይታያል፤›› ያሉት ሹሙ፣ አስተዳደሩ ተከታታይ ውይይቶችንና ግምገማዎችን በማድረግ ውሳኔዎችን አስተላልፎ በመጨረሻ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
Source: ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment