Wednesday, October 12, 2011

«ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት እ.አ.አ በ2025 የበካይ ጋዝ ልቀትን ዜሮ ለማድረግ እየሰራች ነው» ጠ/ሚ መለስ

(እሮብ, 12 ጥቅምት 2011)--በአለም ላይ 1.4 ቢሊዮን ሰዎች ኤሌክትሪክ አያገኙም፡፡ 2.7 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለጤና ጎጂ የሆኑና ባህላዊ የኃይል አማራጮችን ይጠቀማሉ፡፡

በኖርዌይ ኦስሎ የተካሄደው አለም አቀፍ መድረክ ታዲያ የኃይል አቅርቦትን ለሁሉም ለማዳረስ እነዚህ ዜጎች የሚገኙባቸውን ታዳጊ ሀገራት በፋይናንስ መደገፍ የሚል ጭብጥ የነበረው ነው፡፡

በማግስቱ ኮፐንሀገን ዴንማርክ የተካሄደው አለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ፎረም ደግሞ የከባቢ አየር ለውጥ አስገዳጅ ባደረገው የሀገራት አረንጓዴ ልማት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው፡፡

በእነዚህ 2 መድረኮች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷን በታዳሽ ንጹህና አረንጓዴ ልማት ላይ የመሰረተችው ኢትዮጵያ ስኬቶች በተደጋጋሚ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

በመድረኮቹ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ አረንጓዴ ልማት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ወቅቱ የጠየቀው አስገዳጅ ሁኔታ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃይል አቅርቦት ማህበራዊ ፍትህን የማረጋገጥ ጉዳይ ቢሆንም በአፍሪካ ይህን ለማድረግ በፋይናንስ በመሰረተ ልማትና በመፈጸም አቅም ረገድ ያሉ ችግሮች ያማያፈናፍኑ ናቸው፡፡

እናም የግሉ ሴክተር ተገቢ ሚና ሊኖረው ቢገባም ለአህጉሪቱ ህዝብ ኃይል በተገቢው ዋጋ ለማቅረብ የመንግስታት የመሪነት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

5 ዓመት ውስጥ ንጹህና ታዳሽ የኃይል አቅርቦቷን 5 እጥፍ ለማሳደግ እየሰራች ባለችው ኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይህ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ያለው 7 ቢሊዮን ገደማ የአለም ህዝብ 30 ዓመት በኋላ 9 ቢሊዮን ይደርሳል ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙንም ያለ ታዳሽና በቂ የኃይል አቅርቦት ቀጣይነት ያለው አድገት የማይታሰብ ነው ብለዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት ድህንነትና ባህላዊ አጠቃቀም በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ዜጎች የሚያደርሰው ሁለንተናዊ እክልም በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ስኬት ስጋት የደቀነ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በታዳሽ የኃይል ልማት በኢትዮጵያና ኬንያ የተገኙ ስኬቶች ከብክለት በጸዳ የኃይል አቅርቦት ቀጣይና አረንጓዴ ልማት ለማረጋገጥ ምሳሌ የሆኑ ብለዋቸዋል፡፡

በመድረኮቹ የተለያዩ ሀገራት ባለስለጣናት ሳምሰንግን የመሳሰሉ ታላላቅ ኩባንያዎች የአለም አቀፍ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑባቸው ናቸው፡፡
Source: ERTA

No comments:

Post a Comment