Thursday, October 06, 2011

አየር መንገዱ የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ

(መስከረም 25 ቀን 2004 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ቦይንግ 777 የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።


አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን በመግዛት የመጀመሪያው አፍሪካዊ አየር መንገድ ያደረገው ስምምነት አገልግሎቱን በብቃት ለመስጠት እንደሚያስችለው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም አውሮፕላኖቹ በአፍሪካ፣በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የሚሰጠውን አገልግሎት በመጠንና በስፋት ለማከናወን ያስችለዋል ብለዋል።

የአውሮፕላኖቹ በሥራ ላይ ያላቸው ብቃትና ቆጣቢነታቸው አየር መንገዱን በውድድር ዓለም ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመቀጠል እንደሚያስችሉት እምነታቸ ገልጸዋል።

''የአትዮጵያ አየር መንገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ አቪዬሽን መሪነቱን መያዙን እያየን ነው።በዚህም በዓለም አቪዬሽን መሪነቱን ለመያዝ ጎዳና ነው ውስጥ ለመግባት በጥሩ ደረጃ ላይ ነው''ያሉት ደግሞ የቦይንግ ጀርመን፣የአውሮፓ ኅብረት፣ሰሜናዊ አፍሪካና አፍሪካ ፕሬዚዳንት ማርቲን ዳኢሌይ ናቸው።

አየር መንገዱ የአቪዬሽን ደረጃውን በማስጠበቅ በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ ያደረገውን ቦይንግ 787ድሪም ላይነር አውሮፕላን ማዘዙን፣ቦይንግ 777-200 ኤል አር አውሮፕላን መጠቀም መጀመሩንና አሁን ደግሞ የጭነት አውሮፕላኖቹን መግዛቱንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 65 ዓመታት በላይ በዘለቀው አገልግሎቱ የቦይንግ ኩባንያ ምርጥ ምርቶችን በመጠቀም ላይ እንደሚገኝና አሁን ያዘዛቸው የጭነት አውሮፕላኖች ዕቃ የማጓጓዝ አቅሙን እንደሚያሳድጉለት የተናገሩት ሌላው የኩባንያው የሥራ ኃላፊ ቫን ሬክስ ጋላርድ ተናግረዋል።

ቦይንግ 777 የዕቃ ማጓጓዣ በዓለም ረጅሙና ባለ ሁለት ሞተር አውሮፕላን ሲሆን፣102ሜትሪክ ቶን ጭነት ለማጓጓዝ እንደሚችል ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 

No comments:

Post a Comment