Tuesday, September 20, 2011

የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ተጠቅመው ሙዓለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ሚኒስትሩ ጠየቁ

(መስከረም 9 ቀን 2004 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጠቅመው ሙዓለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡

የሚኒስትሩ አቶ መኮንን ማንያዘዋል በሚኒስቴሩ አዳራሽ ዛሬ ከቻይና የንግድ ልዑካን ቡድን ጋር ባካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት፣ በቂ የሰው ጉልበትና ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም ቻይናውያን ባለሃብቶች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ የአፍሪካ አገሮች መካከል ዋነኛ ተጠቃሽ መሆኗን ገልጸው፣ ይህንኑ ፈጣን ዕድገቷን ለማስቀጠልም የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፋ እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በዕቅዱ መሠረትም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ 20 በመቶ ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የቻይና ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን የተመቻቸ ሁኔታ ተገንዝበው በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በኬሚካልና ብረታ ብረት እንዲሁም በፋርማስቲዩካል ኢንዱስትሪ መስኮች ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

ዘርፉ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ለማሟላትም በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትና በዩኒቨርሲቲዎች የሰለጠኑ ወጣት ባለሙያዎችን እያፈራች ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት እሴት ጨምረው የሚያመርቱና ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት የሚያደርጉ የግል ባለሃብቶችን እንደሚያበረታታ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል፡፡
 
በተጨማሪም ቻይናውያን ባለሃብቶች በሚሰማሩበት የኢንቨስትመንት መስክ አስፈላጊውን የመሠረተ ልማት ተቋማት ለመዘርጋት ዝግጁ ነው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የቻይና የንግድ ልዑካን ቡድን መሪ ዛሃንግ ሁዋ ሮንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድልና ከፍተኛ የሰው ኃይል ያላት አገር መሆኗን ቡድኑ ተገንዝቧል ብለዋል፡፡

የቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በፈጣን የዕድገት ጉዞ እየተጓዘች እንደምትገኝ መገንዘብ እንደቻሉም የቡድን መሪው አመልክተዋል፡፡
 
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ቻይና 30 ዓመታት በፊት ከነበረችበት ገጽታ ጋር እንደሚመሳሰል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ልማትን ለማፋጠን ያለው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ይህም የአገሪቷን በር ለውጭ ባለሃብቶች ይበልጥ ክፍት በማድረግ ቢታጀብ እስከ 20 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገብ ያስችላታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያደርጉት ቆይታም ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ሙዓለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የመጨረሻ ውሳኔ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በቻይና ጓንዡ ክልል የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል አቶ ገብረሚካኤል ገብረጻዲቅ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት ቻይናውያን ባለሃብቶች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኩባንያዎች ባለቤቶች ናቸው፡፡

ኩባንያዎቹ በአብዛኛው የጫማ ኢንዱስትሪ፣ የምግብ ማቀናበሪያ የባዮ ሜዲካል ኤሌክትሮኒክስ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ማካተታቸውን አመልክተዋል፡፡
 
ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት በሼንዘን ከተማ በመገኘት የከተማዋ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደረጉ በጠየቁት መሠረት መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment